1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤውሮ 2012 ና የጀርመን ግስጋሴ

ሰኞ፣ ሰኔ 11 2004

በፖላንድና በኡክራኒያ የጋራ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ጀርመን የምድቡን ዙር በሙሉ ዘጠን ነጥቦች በማጠቃለሉ ረገድ ብቸናዋ ተሳታፊ አገር ሆናለች።

https://p.dw.com/p/15HMJ
ምስል Reuters

በፖላንድና በኡክራኒያ የጋራ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ጀርመን የምድቡን ዙር በሙሉ ዘጠን ነጥቦች በማጠቃለሉ ረገድ ብቸናዋ ተሳታፊ አገር ሆናለች። ጀርመን ለዚህ የበቃችው ታዛቢዎች «የሞት» ብለውት በነበረው ጠንካራ ምድብ-ሁለት ውስጥ ባለፈው ምሽት ዴንማርክን በሶሥተኛ ግጥሚያዋ 2-1 ካሸነፈች በኋላ ነው። ከዚሁ ቀደም ሲል በመጀመሪያ ፖርቱጋልን 1-0 መርታቷና ኔዘርላንድንም 2-1 ማሸነፏ አይዘነጋም።

የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በዚሁ ከሶሥት ግጥሚያዎች በተገኙ ሶሥት ድሎቹ በፍጹም የበላይነት ወደ ተከታዩ ጥሎ ማለፍ ዙር ሊሻገር በቅቷል። ከምድቡ በሁለተኛነት ወደ ሩብ ፍጻሜው የተሻገረው የፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድን ነው። ቡድኑ በጀርመን ለጥቂት 1-0 ከተሸነፈ በኋላ በተከታይ ግጥሚያዎቹ ዴንማርክን 3-2፤ እንዲሁም ባለፈው ምሽት ኔዘርላንድን 2-1 መርታቱ ተሳክቶለታል። በትናንቱ ግጥሚያ ቡድኑን ለድል ያበቃው በተለይ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ድንቁ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነበር።

UEFA EURO 2012 Dänemark Deutschland
ምስል Reuters

ዴንማርክ በሶሥት ነጥቦች በሶሥተኝነት ተወስና ስትቀር ኔዘርላንድ ደግሞ ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ በዜሮ ነጥብ ነው ከውድድሩ ስንብት ያደረገችው። የኔዘርላንድ ድክመት ምንም እንኳ በተናጠል ግሩም ተጫዋቾች ቢኖራትም እንደ ቡድን ጠንካራ አለመሆኗ ነበር። ዴንማርክ በፊናዋ ጀርመንን ማሸነፍ ሲኖርባት የጨዋታውን ሁለተኛ አጋማሽ በመከላከል ማሳለፏ ትልቅ ስህተት እንደነበረ በመጨረሻ በግልጽ ታይቷል። የጀርመኑ የመሃል ሜዳ ተጫዋች ሤሚ ኬዲራ እንደሚለው እርግጥ ይህ የዴኖች የአጨዋወት ስልት ለቡድኑ ቀላል አልነበረም።

«እርግጥ ሁልጊዜም ተጋጣሚው ቡድን አብሮ ሲጫወት ይቀላል። የዴንማርክ ቡድን ጨዋታውን ማሸነፍ ቢኖርበትም ይህን በማድረግ ፈንታ መከላከልን መምረጡ ስልቱ በመሆኑ ነው። እና ግን ይህን መታገል ነበረብን። በሩብ ፍጻሜው ዙር ከግሪክ ጋር የምናደርገው ግጥሚያም ከዚህ የተለየ አይሆንም። ስለዚህም ይህን ሃቅ መቀበልና ከማማረር መቆጠብ ግድ ነው»

ለጀርመን ትናንት ቀደም እንዳሉት ሁለት ግጥሚያዎች ሁሉ ጎሎቹን ያስቆጠረው አጥቂው ማሪዮ ጎሜስ አልነበረም። ከፖላንድ የመነጨው ሉካስ ፖዶልስኪ በመቶኛ ጨዋታው የመጀመሪያዋን ግሩም ጎል በማስገባት ራሱን ሲሸልም ሁለተኛዋን የድል ጎል ያስቆጠረው ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ጨዋታ የተጫወተው የ 23 ዓመቱ ወጣት ላርስ ቤንደር ነበር። በቢጫ ካርዶች የተነሣ ለአንድ ጨዋታ ታግዶ የነበረውን ቋሚውን የቀኝ ክንፍ ተከላካይ ጄሮም ብዎቴንግን በመተካት የተሰለፈው ተቀያሪ ተጫዋች ቤንደር በትናንት አቀራረቡ በብሄራዊው ቡድን ውስጥ ቋሚ ቦታ የማግኘት ዕድሉን ከፍ ያደረገ ነው የሚመስለው። ሉካስ ፖዶልስኪ በበኩሉ በመቶኛ ጨዋታው ባስቆጠራት ጎሉ በጣሙን ነው የተደሰተው።

«ጨዋታው ለኔ የተለየ እንደነበር ጥያቄ የለውም። እና ለዚያውም ባልተለመደ በቀኝ እግሬ ጎል ማስገባቴ ደግሞ ግሩም ነው። ይሄ ዘወትር የተለመደ ነገር አይደለም። ጎል በማግባቴና ቡድኑን ለማገዝ በመቻሌ በጣም ነው የተደሰትኩት። አሁን ለማንኛውም ለሩብ ፍጻሜው ደርሰናል፤ ጠቃሚው ነገርም ይሄው ነው»

በጥቅሉ ጀርመን ምንም እንኳ የምድቧን ግጥሚያዎች በሙሉ በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው ብታልፍም በአጨዋወት ረገድ እስካሁን 90 ደቂቃዎች ሙሉ ጥንካሬ ለማሳየት አለመቻሏ ታይቷል። ምናልባት ይህ ድክመት ለግሪክ ካወቀችበት በሩብ ፍጻሜው ግጥሚያ የሚረዳ ሊሆን ይችላል። የዴንማርክ ብሄራዊ ቡድንም ትናንት መሃል ሜዳውን ለቆ ወደ ኋላ ባያሸጋሽግ ኖሮ በአሸናፊነት ከሜዳ ሊወጣም በቻለ ነበር።

UEFA EURO 2012 Fans
ምስል Reuters

ለማንኛውም ጀርመንና ፖርቱጋል ከምድብ-ሁለት ወደ ሩብ ፍጻሜው ሲያልፉ ፖርቱጋል ከቼክ ሬፑብሊክ ትገናኛለች። ቼክ ሬፑብሊክ በምድብ-አንድ ፖላንድን 1-0 አሸንፋ ከውድድሩ ስታስወጣ ግሪክም ወደ ሩብ ፍጻሜው የተሻገረችው ሩሢያን በተመሳሳይ ውጤት ረትታ በማሰናበት ነበር። የፖላንድ እንደ አስተናጋጅ አገር ቀድሞ መውጣት የአገሪቱን ሕዝብ በጣሙን ሲያሳዝን በምድቡ መክፈቻ ግጥሚያ በሩሢያ 4-1 ተሸንፋ የነበረችው ቼክ ሬፑብሊክ አገግማ ወደፊት መራመዷም ብዙዎችን አስደንቋል።

ኢትዮጵያዊ ምንጭ ያለው ድንቅ ተከላካይዋ ቴኦዶር ገብረ ሥላሴም ለዚህ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉ የግድ ሊጠቀስ ይገባል። በነገራችን ላይ ቴኦ ከቼኩ ቡድን ከስላቫን ሊበሬትስ ወደ ጀርመኑ ታላቅ ክለብ ወደ ቬርደር ብሬመን በመቀየር በመጪው የውድድር ወቅት የቡንደስሊጋ ተጫዋች እንደሚሆን የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያን በተዘዋዋሪም ቢሆን በታላቁ የአውሮፓ ሊጋ ውስጥ ሕያው የሚያደርግ ነው።

የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምድቦች የመጀመሪያ ዙር ትናንትና ከትናንት በስቲያ በዚህ መልክ ሲጠቃለል ዛሬና ነገ ደግሞ የምድብ-ሶሥትና አራት ዕጣ የሚለይበት ነው። በዛሬው ምሽት ምድብ-ሶሥት ውስጥ ያለፉት የአውሮፓና የዓለም ዋንጫ ውድድሮች አሸናፊ ስፓኝ ከክሮኤሺያ እንዲሁም ኢጣሊና ከአየርላንድ ይጋጠማሉ። ስፓኝና ክሮኤሺያ እያንዳንዳቸው አራት ነጥብ ሲኖራቸው ኢጣሊያ ሁለት ነጥብ አላት፤ አየርላንድ ደግሞ በዜሮ ነጥብ ቀደም ብላ ከውድድሩ ተሰናብታለች።

የተቀሩት ሶሥቱ ክለቦች በሙሉ ወደ ሩብ ፍጻሜው የማለፍ ዕድል አላቸው። በምድብ-አራት ውስጥም ሁኔታው ከሞላ-ጎደል ተመሳሳይ ሲሆን ፈረንሣይና እንግሊዝ በእኩል አራት ነጥብ መሪዎቹ ናቸው። ሌላዋ የውድድሩ አስተናጋጅ ኡክራኒያ አንዲት ነጥብ ወረድ ብላ ሶሥተኛ ስትሆን ስዊድን ያላንዳች ነጥብ ከወዲሁ አልቆላታል። ለመሆኑ ኡክራኒያስ እንደ ፖላንድ ቀድሞ የመሰናበት ዕጣ ነው የሚገጥማት ወይስ እንግሊዝን አሸንፎ በውድድሩ መቀጠሉ ይቀናት ይሆን? መልሱን እስከነገው ምሽት ጠብቆ መረዳቱ ግድ ይሆናል።

Flash-Galerie Leichtathletik Weltmeisterschaft 2009 Berlin
ምስል picture-alliance/ dpa

አትሌቲክስ

በአትሌቲክሱ ዓለም የለንደን ኦሎምፒክ እየተቃረበ ሳለ የአትሌቶቹ ዝግጅትም የዚያኑ ያህል በየቦታው እየቀለጠፈ ነው የሚገኘው። ኢትዮጵያዊው የአሥርና የአምሥት ሺህ ሜትር የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ቀነኒሣ በቀለ በፊታችን አርብ በርሚንግሃም ላይ በብሪታኒያ የኦሎምፒክ ማጣሪያ የአሥር ሺህ ሜትር ሩጫ ይሳተፋል። ከርሱ ሌላ ወንድሙ የቀድሞው የአዳራሽ ውስጥ የዓለም ሻምፒዮን ታሪኩ በቀለና የቀድሞው የአገር አቋራጭ ሩጫ የዓለም ሻምፒዮን ገብሬ ገ/ማርያምም የውድድሩ ተካፋዮች ናቸው።

ቀነኒሣ በቀለ ዝግጅቱ ከጠንካሮቹ የረጅም ርቀት ሯጮች ጋር ለመወዳደር ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆንለት ሲጠቅስ ዋና ዓላማውም በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ ቦታ ለማግኘት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መሆኑን ገልጿል። በሌላ የአትሌቲክስ ዜና የኬንያው የ 800 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ዴቪድ ሩዲሻ በለንደኑ ኦሎምፒክ ከተፈቀደለት ከተለመደ ርቅቱ ባሻገር በአራት ጊዜ አራት መቶ ሜትር የዱላ ቅብብል ለመወዳደርም በመዘጋጀት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ከዚሁ ሌላ ኬንያዊቱ የአሥርና የአምሥት ሺህ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ቪቪያን ቼሩዮት ኬንያ ውስጥ በተካሄደ የአሥር ሺህ ሜትር ሩጫ በማሸነፍ በለንደኑ ኦሎምፒክ ውድድር ድርብ ተሳትፎ ለማድረግ ወዳላት ተሥፋ ይበልጥ ተቃርባለች። ቼሩዮት ካለፈው ነሐሴ ወር የዴጉ የዓለም ሻምፒዮና ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረገችው የአሥር ሺህ ሜትር ረጫ አንደኛ የወጣችውጆይስ ቼፕኪሩዊንና ሤሊይ ኪፕየጎን በማስከተል ነው። የቀድሞይቱ የዓለም ሻምፒዮን ሊኔት ማሣይ በአንጻሩ ሩጫውን በመጨረሻው ዙር ላይ ማቋረጡ ግድ ሆኖባታል።

David Nalbandian Tennis Schläger Flash-Galerie
ምስል AP

ቴኒስ

በለንደን የኩዊንስ ክለብ ፍጻሜ ግጥሚያ ትናንት የታየው ጉድ በቴኒሱ ዓለም ምናልባትም ለረጅም ጊዜ የማይረሣ ነው። ለዚህም ተጠያቂው ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት መምቻውን በመሰባበር አንድ መስመር ጠባቂን እስከማቁሰል የደረሰው አርጄንቲናዊው ዴቪድ ናልባንዲያን ነው። በዚሁ የተነሣ የመጀመሪያውን ምድብ አሸንፎ የነበረውን ናልባንዲያን ከማገድና የክሮኤሺያ ተጋጣሚው ማሪን ቺሊችን አሸናፊ ከማድረግ ሌላ ምርጫ አልተገኘም። ናልባንዲያን በበኩሉ ዛሬ ሁለተኛ የይቅርታ መግለጫ በማውጣት በድርጊቱ መጸጸቱን አሳይቷል።

በርሚንግሃም ላይ ዛሬ በተካሄደ የዓለም ቴኒስ ማሕበር የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ አሜሪካዊቱ ሜላኒ አውዲን የሰርቢያ ተጋጣሚዋን የለና ያንኮቪችን በለየለት ሁኔታ 6-4,6-2 በማሸነፍ ለመጀመሪያ የውድድር ድሏ በቅታለች። ጨዋታው ትናንት በዝናብ የተነሣ ወደ ዛሬ መሸጋሸግ ግድ ሆኖበት ነበር። በዚያው በእንግሊዝ በኖቲንግሃም ደግሞ የአውስትራሊያዋ ወጣት የ 16 ዓመት ተጫዋች ኤሽሌይ ባርቲይ ታቲያና ማሌክን 6-1,6-1 በማሸነፍ ለዊምብልደን ተሳትፎ በር ለማስከፈት በቅታለች።

ከዚሁ ሌላ የቀድሞዋ የዓለም አንደኛ የቤልጂጓ ኪም ክላይስተርስ በኔዘርላንድ-ሄርሶገንቦሽ የስዊሷን ሮሚና ኦፕራንዲን በማሸነፍ ወደ ውድድሩ መድረክ በስኬት ለመመለስ ችላለች። በአውስትሪያ-ጋስታይን በተካሄደ ዓለም አቀፍ የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ፈረንሣዊቱ አሊዝ ኮሜት የቤልጂግ ተጋጣሚዋን ያኒና ቪክማየርን አሸንፋለች። በጀርመን-የሃለ ፍጻሜ ግጥሚያም ቶሚይ ሃስ የዓለም ሶሥተኛውን ሮጀር ፌደረርን በማሸነፍ ታዛቢዎችን አስደንቋል።

ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቅርቡ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ባሳየው ብርታቱ በመቀጠል ባለፈው ሰንበት ለ 2013 የአፍሪቃ ዋንጫ ዋና ማጣሪያ ዙር ለማለፍ ችሏል። ብሄራዊው ቡድን ለዚህ የበቃው ከቤኒን ጋር ቀደም ሲል በሜዳው 0-0 ከተለያየ በኋላ በመልሱ ጨዋታ 1-1 ውጤት አስመዝግቦ በመመለሱ ነው። ለቡድኑ ወሣኟን ጎል ያስቆጠረው አሉላ መኮንን ነበር። ለዋናው ማጣሪያ ዙር ያለፉት ሰላሣ ሃገራት በፊታችን መስከረምና ጥቅምት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለሚካሄደው ፍጻሜ ውድድር ለማለፍ ይታገላሉ።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ