1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤውሮ 2012 ፖላንድ/ኡክራኒያ

ሰኞ፣ ሰኔ 4 2004

ሰሞኑ የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የዓለምን ትኩረት ስቦ የሚገኝበት ቢሆንም ለኢትዮጵያም ተሥፋ ሰጭ ታሪክ መጻፍ የጀመረ እየመሰለ ነው።

https://p.dw.com/p/15CFU
ምስል picture-alliance/dpa

ሰሞኑ የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የዓለምን ትኩረት ስቦ የሚገኝበት ቢሆንም ለኢትዮጵያም ተሥፋ ሰጭ ታሪክ መጻፍ የጀመረ እየመሰለ ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ብራዚል ውስጥ ከሁለት ዓመት ጊዜ በኋላ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ለማለፍ በሚደረገው የአፍሪቃ ማጣሪያ በምድብ-አንድ ውስጥ የሚያቆመው አልተገኘም። ቡድኑ በቅርቡ ከአገር ውጭ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ግጥሚያ 1-1 በመለያየት ብዙዎችን ሲያስደንቅ ትናንት ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ማዕከላዊት አፍሪቃ ሬፑብሊክን 2-0 በመርታት የምድቡን አመራር ይዟል።

የኢትዮጵያ ቡድን አሁን በአራት ነጥቦች ምድቡን የሚመራ ሲሆን ማዕከላዊት አፍሪቃ ሬፑብሊክ በሶሥት ነጥቦች ሁለተኛና ከቦትሱዋና በእኩል ለእኩል ውጤት የተወሰነችው ደቡብ አፍሪቃ በሁለት ነጥቦች ሶሥተኛ ስትሆን ቦትሱዋና ደግሞ በአንዲት ነጥብ የመጨረሻዋ ናት። ለኢትዮጵያ በሁለቱም ግጥሚያዎች ጎሎቹን በማስቆጠር የቡድኑ የስኬት ዋስትና የሆነው ድንቁ አጥቂ ሣላዲን ሰይድ ነበር።

ቡድኑ በዚሁ ከገፋ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዚያውም በብራዚል ለዓለም ዋንጫ ተሳትፎ የሚያበቃ ሲሆን ይህም በእርግጥ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት አያጠራጥርም። እርግጥ ከዚህ ለመድረስ ገና ብዙ ትግል መደረግ እንዳለበት መዘንጋት የለበትም። ለማንኛውም ተጫዋቾቹን ዕጹብ-ድንቅ ቀጥሉበት እንላለን።

በፖላንድና በኡክራኒያ የጋራ አዘጋጅነት በሚካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ላይ እናተኩርና የምድቡ ዙር መክፈቻ ግጥሚያዎች በዛሬው ምሽት ይጠናቀቃሉ። ውድድሩ ባለፈው አርብ በዋርሶው ብሄራዊ ስታዲዮም በተካሄደ መክፈቻ ስነ ስርዓት ሲጀመር ፖላንድና ግሪክ 1-1 በሆነ ውጤት መለያየታቸው የሚታወስ ነው። በዚሁ ምድብ-አንድ ውስጥ ጠንካራዋ ሆና የተገኘችው ሩሢያ ደግሞ ቼክ ሬፑብሊክን በፍጹም የበላይነት 4-1 ስትረታ ወደፊት ለመዝለቅ ከጅምሩ ጥሩ ሁኔታን ነው ያመቻቸችው።

Fußball EM 2012 Public Viewing
ምስል picture-alliance/dpa

ለቼክ ሬፑብሊክ በአንጻሩ በነገው ዕለት ከግሪክ ጋር የሚደረገው ግጥሚያ እጅግ ወሣን ይሆናል። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያዊ ምንጭ ያለው ቴኦዶር ገ/ሥላሴ ለቼክ ሬፑብሊክ ተሰልፎ በመጫወት ጥቂትም ቢሆን ኢትዮጵያ በአውሮፓው ዋንጫ ውድድር ላይም ሕያው እንድትሆን ማድረጉ አልቀረም። አንድ ኢትዮጵያዊ ምንጭ ያለው እግር ኳስ ተጫዋች በዚህ ከፍተኛ ደረጃ ተሰልፎ ሲገኝም ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ለማንኛውም ቼኮች ወደፊት ለመራመድ ከፈለጉ እርግጥ ተከላካዩ ሚሻል ካድሌትስ እንደገለጸው በመጪው ግጥሚያ ተሻሽለውና ተጠናክረው መቅረባቸው ግድ ነው።

«ከልብ ተጫወት አትጫወት በመጨረሻ 4-1 ከተሸነፍህ ይህ መሪር ነገር ነው። እርግጥ ስህተታችንን መርምረን በመጪው ግጥሚያ እንዳይደገም ማድረግ አለብን። ገና ሁለት ጨዋታዎች ይቀሩናል። አሁን ዋናው ነገር አንገታችንን አለመድፋት ነው። ለምሳሌ በ 1996 በመጀመሪያው ዙር በጀርመን ከተሸነፍን በኋላ እስከፍጻሜ ለመድረስ ችለን ነበር። እናም ያለፈውን ጨዋታ ከአዕምሯችን በማስወጣት በዚህ ማመን አለብን»

ፖላንድም ቢሆን እንደ አስተናጋጅ አገር በጅምሩ እንዳትቀር በነገው ምሽት ከሩሢያ ጋር በምታካሂደው ግጥሚያ ቢቀር አንዲት ነጥብ ለማገኘት ጠንክራ መገኘት ይኖርባታል። እጅግ ከባድ በሆነው በምድብ-ሁለት ውስጥ በመጀመሪያዎቹ ግጥሚያዎች ጀርመን ፖርቱጋልን 1-0 ስትረታ ዴንማርክም ኔዘርላንድን በተመሳሳይ ውጤት አሸንፋለች። ያስደንቃል፤ የኔዘርላንድ በዴንማርክ መሸነፍ ብዙም የተጠበቀ ነገር አልነበረም።

Fussball Irland Kroatien UEFA EURO 2012
ምስል dapd

ጀርመንም ቢሆን ፖርቱጋልን አሸንፋ ውድድሩን በስኬት ለመጀመር በመቻሏ በዕድሏ በጣሙን ልታመስግን ይገባል። ምክንያቱም በጨዋታው ብዙ የጎል ዕድል የነበረውና ግሩም ቢጫወትም ዕድል የራቀው የፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድን ነበር። የጀርመኑ ብሄራዊ ቡድን አሠልጣን ዮአኺም ሉቭም ከዚህ አንጻር በተገኘው ውጤት በጣሙን ነው የተደሰተው።

«ቡድናችን በአጠቃላይ ባሳየው ጨዋታ ረክቻለሁ። ምክንያቱም እንደሚታወቀው የመጀመሪያው ግጥሚያ ሁሌም ከባድ ሲሆን ከዚህ አንጻር ጥሩ ነው የተጫወትነው። ማሪዮ ጎሜስ ያስገባት ጎል የቡድኑን መንፈስ እንዳነቃቃችም አምናለሁ። በጥቅሉ 1-0 አሸንፈናል፤ ዋናውም ነገር ይሄው ነው»

እርግጥ እንደቀድሞው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች እንደ ኦላፍ ቶን ጥሩ የተጫወተው የፖርቱጋል ቡድንም ከጥቂት ዕድል ጋር ቢቀር እኩል ለእኩል ቢወጣ በተገባው ነበር።

«የጀርመን ቡድን በጨዋታው ያለመው ጥሩ ውጤት በማግኘቱ ላይ ብቻ ነበር። ምክንያቱም ቀደም ሲል የኔዘርላንድ ሳይጠበቅ ጥሩ በተጫወቱት በዴኖች መሸነፍ ለሁሉም ማስጠንቀቂያ ነበር የሆነው። የፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድንም ግሩም ነው የተጫወተው። እናም ከጥቂት ዕድል ጋር እኩል ለእኩል ሊያደርጉም በቻሉ ነበር። ከዚህ የተነሣ ድሉ ለጀርመን በጣም ጠቃሚ ነው»

በዚህ ከባድ ምድብ ውስጥ እያንዳንዱ ግጥሚያ የፍጻሜን ያህል ሲሆን ኔዘርላንድና ፖርቱጋል በአጭሩ እንዳይቀሩ በፊታችን ረቡዕ ጠንክረው መገኘታቸው ግድ ነው። ካለፈው የዓለም ዋንጫ ወቅት ጥንካሬው ቀዝቀዝ ብሎ ለታየው ለጀርመን ብሄራዊ ቡድን የመጀመሪያው ድል ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ከነገ በስቲያ ከኔዘርላንድ ጋር በሚደረገው ግጥሚያ የሚታይ ይሆናል። ለኔዘርላንድ በአንጻሩ ግጥሚያው የሞት-የሽረት ሲሆን የጀርመን ቡድን ቀላል ትግል አይጠብቀውም። የፖርቱጋልም ዕጣ እንዲሁ ከኔዘርላንድ የሚመሳሰል ነው።

EURO 2012 Spanien gegen Italien (Andres Iniesta)
ምስል picture-alliance/dpa

በምድብ-ሶሥት ውስጥ ባለፈው ምሽት የአውሮፓና የዓለም ሻምፒዮን ስፓን ከኢጣሊያ 1-1 ስትለያይ የኢጣሊያ ቡድን ያልተጠበቀ የታክቲክና የቴክኒክ ጥንካሬ ብዙ ታዛቢዎችን አስደንቋል። ጎሎቹን በሁለተኛው አጋማሽ ያስቆጠሩት አንቶኒዮ-ዲ-ናታሌና ሤስክ ፋብሬጋስ ነበሩ። በዚሁ ምድብ ሁለተኛ ግጥሚያ ክሮኤሺያ አየርላንድን 3-1 በማሸነፍ ጥሩ ጅማሮ አድርጋለች።

ክሮኤሺያ በፊታችን ሐሙስ የኢጣሊያ ተጋጣሚ ስትሆን ስፓኝ ደግሞ የምትጫወተው ከአየርላንድ ጋር ነው። ክሮኤሺያ ምንም እንኳ ስፓኝንና ኢጣሊያን የመሳሰሉ ታላላቅ ቡድኖች የሚጠብቋት ቢሆንም ተጫዋቿ ኢቫን ራኪቲች ወደ ሩብ ፍጻሜው የማለፍ ብቃት አይጎለንም ባይ ነው።

«በዛሬው ግጥሚያ በሚገባ እንዳሸነፍን ነው የማምነው። ዋናው ነገርም ይሄው ነው። ነገር ግን ኢጣሊያንና ፈረንሣይን የመሰሉ ሁለት ሃያል ተጋጣሚዎች፤ ሁለት ከባድ ጨዋታዎች እንዳሉብን እናውቃለን። እናም ጠንክረን መጫወት ይኖርብናል። በበኩሌ ይህን ለማድረግ ብቃቱ እንዳለን እርግጠኛ ነኝ። ወደ ሩብ ፍጻሜው ለማለፍ እንደምንፈልግ ግልጽ ነው»

የምድብ-አራት መክፈቻ ግጥሚያዎች የሚካሄዱት በዛሬው ምሽት ሲሆን ዕለቱ የአብሮ አስተናጋጇ የኡክራኒያ ብሄራዊ ቡድንም ትርዒቱን የሚጀምርበት ይሆናል። በወቅቱ ፈረንሣይና እንግሊዝ እየተጫወቱ ሲሆን ዘግየት ብሎም ኡክራኒያና ስዊድን ይጋጠማሉ።

ብራዚል ውስጥ ከሁለት ዓመታት በኋላ ለሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ለማለፍ በሚደረገው ማጣሪያ ውድድር ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ኢትዮጵያ ምድብ-አንድን በመምራት በአስደናቂ ሁኔታ እየተራመደች ሲሆን ምድብ-ሁለትን ቱኒዚያ፤ እንዲሁም ምድብ -ሶሥትን አይቮሪ ኮስት ይመራሉ። ሱዳን፣ጋቡን፣ ናይጄሪያ፣ ቤኒን ግብጽ፣ ሊቢያና ሤኔጋልም በወቅቱ ከሁለት ግጥሚያዎች በኋላ የተቀሩት ምድቦች ቁንጮዎች ናቸው።

በደቡብ አሜሪካው ማጣሪያ ትናንት ኡሩጉዋይ ከፔሩ 4-2 እንዲሁም ኤኩዋዶር ከኮሉምቢያ 1-0 ሲለያዩ ቺሌ ከስድሥት ግጥሚያዎች በኋላ የምድቡ መሪ ናት።ኡሩጉዋይ፣ አርጄንቲናና ኤኩዋዶርም አንድ ጨዋታ ጎሏቸው በቅርብ ይከተላሉ። የሚቀጥሉት ግጥሚያዎች የሚካሄዱት በፊታችን መስከረም ወር ውስጥ ነው።

Rafael Nadal French Open
ምስል Reuters

ቴኒስ

በፍሬንች-ኦፕን የቴኒስ ውድድር ትናንት በዝናብ ሳቢያ ተቋርጦ የነበረው የወንዶች ፍጻሜ ግጥሚያ በዛሬው ዕለት ቀጥሎ በስፓኙ ኮከብ በራፋኤል ናዳል አማካይነት ተፈጽሟል። ናዳል ለድል የበቃው በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነውን የሰርቢያ ተጋጣሚውን ኖቫክ ጆኮቪችን ከአራት በሶሥቱ ምድብ በማሸነፍ ነው። ጨዋታው ትናንት በሶሥተኛው ምድብ ላይ ነበር የተቋረጠው። ለናዳል የዛሬው ድል በፍሬንች-ኦፕን ላይ ሰባተኛው ይሆናል። በሴቶች ፍጻሜ ደግሞ ትናንት ሩሢያዊቱ ማሪያ ሻራፖቫ የኢጣሊያ ተጋጣሚዋን ሣራ ኤራኒን በማሸነፍ ለከፍተኛ ድል በቅታለች። ድሉ ሻራፖቫን በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ወደ ቀደምቱ ስፍራ ከፍ የሚያደርግም ነው።

Lewis Hamilton Formel 1
ምስል Reuters

ፎርሙላ-አንድ

በትናንትናው ዕለት ካናዳ-ሞንትሬያል ላይ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የብሪታኒያው ዘዋሪ ሉዊስ ሃሚልተን አሸናፊ ሆኗል። ለሃሚልተን ድሉ ካለፈው ሕዳር ወር ወዲህ የመጀመሪያው መሆኑ ነበር። የስፓኙ ተወላጅ ፌርናንዶ አሎንሶ ሁለተኛ ሲወጣ ሶሥተኛ የሆነው ደግሞ ጀርመናዊው ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል ነው። ከስባት እሽቅድድሞች በኋላ በአጠቃላይ ነጥብም ሃሚልተን በ 88 የሚመራ ሲሆን አሎንሶ በ 86 እንዲሁም ፌትል በ 85 ነጥቦች በቅርብ ይከተላሉ።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ