1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቡሩንዲ የቀጠለው ውዝግብ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 16 2008

በቡሩንዲ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ከተካሄደ አንድ ዓመት ሆኖታል። የሀገሪቱ የተቃዋሚ ቡድን መሪዎች የራቁበት ባልተካፈሉበት በዚሁ ምርጫ ተፎካካሪ ያልቀረበባቸው ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን አሸንፈዋል። የተቃዋሚው ቡድን «ድራማ» ያለው ምርጫ ከተጠናቀቀ ዛሬ ከአንድ ዓመትም በኋላ ግን የቡሩንዲ ፖለቲካዊ ውዝግብ እንደቀጠለ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/1JURd
Burundi Wahlen Präsident Nkurunziza
ምስል Reuters/E. Benjamin

[No title]

በቡሩንዲ ሁኔታዎች እየተበላሹ መሄድ የጀመሩት ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ባለፈው ዓመት፣ እጎአ ሚያዝያ ፣ 2015 ዓም ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን እንደገና ለፕሬደንታዊው ምርጫ በተወዳዳሪነት እንደሚቀርቡ ባስታወቁበት ጊዜ ነበር። ይሁንና፣ በቡሩንዲ ሕገ መንግሥት መሰረት አንድ የሀገር መሪ ከሁለት የስልጣን ዘመን በላይ በዚሁ ከፍተኛ ስልጣን ላይ መቆየት አይፈቀድለትም፣ በዚህም የተነሳ፣ ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ የቡሩንዲን የርስበርስ ጦርነት ባበቃው እና እጎአ በ2000 ዓም በአሩሻ፣ ታንዛንያ በተፈረመው የሰላም ስምምነት በወጣው የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት ጥሰዋል በሚል ትልቅ ተቃውሞ ተነስቶባቸው ነበር።

ይሁን እንጂ፣ በምህፃሩ « ሲ ኤን ዲ ዲ - ኤፍ ዲ ዲ» ገዢው ፓርቲ፣ የአምናው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለንኩሩንዚዛ ሁለተኛው ነበር በሚል የተቃዋሚ ወገኖችን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በእቅዱ ቀጥሎበት፣ ንኩሩንዚዛም ሀምሌ፣ 2015 ዓም እንደገና ተመርጠዋል። በዚሁ ሰበብ የተቀሰቀሰውን ግዙፍ ተቃውሞ መንግሥት ይህን ተቃውሞ በኃይል የደመሰሰበት ርምጃው ሀገሪቱን እንደገና ወደጎሳው ግጭት ውስጥ እንዳይመልሳትም ማስጋቱን የመብት ተሟጋቾች ገልጸዋል። ሂደቶችን በቅርብ በመከታተል ላይ የሚገኙት የአፍሪቃ ህብረት፣ የተመድ እና የአውሮጳ ህብረት ተቀናቃኝ ወገኖች ልዩነታቸውን በውይይት እንዲያስወግዱ ከማሳሰብ ወደኋላ አላሉም። ሆኖም፣ የቡሩንዲ ቀውስ እስካሁን እልባት አላገኘም።
ይህ የተቃዋሚ ቡድን እና ሕዝብ ለሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ያሳዩት ደንታ ቢስነት ከአራት ዓመት በኋላ፣ እጎአ በ2020 በሚደረገው ምርጫ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል የቀድሞው የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ሲልቬስትር ንቲባንቱንጋንያ ይገምታሉ።
« በቡሩንዲ አምና በተፈጠረው ውዝግብ ሰበብ ወደ ጎረቤት ሀገራት የሸሹ ወደ 300,000 ስደተኞ፣ በየወህኒ ቤት የሚማቅቁት ፖለቲካ እስረኞች እና የተፈፀሙ ግድያዎች ጉዳይ መፍትሔ ሳያገኝ እና ሳይጣራ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ብሎ ማሰብ ትክክለኛ አይመስለኝም። እና ለሕዝቡ ጥያቄዎች መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ ነው። እንደኔ አስተያየት፣ በቡሩንዲ የሚያስፈልገው ከምርጫ ውጤት በኋላ ማንም ፓርቲ ሊቃወመው የማይችል ጥያቄ የማያስነሳ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ማካሄድ ነው ። »
በቡሩንዲ ከተቃዋሚው ቡድን ባለፈ የሀገሪቱ ሲቭል ማህበረሰብም የፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ 3ኛ የስልጣን ዘመንን ለማከላከል ያደረገው ግዙፍ እንቅስቃሴ ውጤት አልባ የሆነበትን ድርጊት አንዳንድ ታዛቢዎች ለሀገሪቱ የወደፊት ሂደት ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ ተመልክተውታል። ይሁንና፣ ሌላው የቀድሞ የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ዶሚሲየን ንዳይዚዬ ይህንን የተንታኞችን አስተያየት አይጋሩትም።

Burundi Ex-Präsident Domitien Ndayizeye
የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶሚሲየን ንዳይዚዬምስል Getty Images/AFP/S. Maina
Burundi Gewalt und Tote - Polizist
ምስል Reuters/J.P. Aime Harerimana

« ዴሞክራሲ ማለት የወደፊቱን አርቆ መመልከት ማለት ነው። ስለዚህ፣ ክሽፈትን ወይም ሽንፈትን ተቀብሎ መቀመጥ ትክክል አይደለም። ብቸኛ መፍትሔ የሚሆነው ፣ ለአወዛጋቢ ጥያቄዎች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ፣ ዴሞክራሲያዊውን ስርዓት በመከተል፣ በውይይት መልስ ለማስገኘት መሞከር ነው ብዬ አስባለሁ። »
ባደረጉት የመጨረሻው ጉባዔ አንዳንድ የ «ሲ ኤን ዲ ዲ - ኤፍ ዲ ዲ » በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ፣ በተለይም፣ የፕሬዚደንቱን የስልጣን ዘመን የሚገድበው አንቀጽ እንዲሻር በመጠየቅ ማሻሻያ እንዲደረግ ሀሳብ አቅርበዋል። ይህ ሀሳባቸው ተቀባይነት ካገኘ፣ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛን በ2020 ዓም በሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንደገና መወዳደር ያስችላቸዋል ነው የሚባለው።

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ