1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እርግዝና እና ህመም የነፃነት መንገዶች

ዓርብ፣ የካቲት 9 2004

መቼም ርዕሱን ስትመለከቱ በውስጣችሁ በርካታ ጥያቄዎች እንደሚመላለሱ እገምታለሁ። አዎን ለጊዜውም ቢሆን እርግዝና እና ህመም ማልታ በተሰኘችው ሐገር ላይ የነፃነት መንገዶች ሆነው ተገኝተዋል። እንዴትነቱን ማልታ ከሚገኘው የስደተኞች መጠለያ

https://p.dw.com/p/1452O
የማልታ ደሴትምስል DW

መቼም ርዕሱን ስትመለከቱ በውስጣችሁ በርካታ ጥያቄዎች እንደሚመላለሱ እገምታለሁ። አዎን ለጊዜውም ቢሆን እርግዝና እና ህመም  ማልታ በተሰኘችው ሐገር ላይ የነፃነት መንገዶች ሆነው ተገኝተዋል።  እንዴትነቱን  ማልታ ከሚገኘው የስደተኞች ጣቢያ ከቀናት በፊት ነፃ የወጡ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ያብራሩልናል።

ማልታ በደቡባዊ አውሮጳ ከኢጣሊያዋ ሲሲሊ ከተማ  93 ኪ ሜትሮች ርቀት ላይ ነው የምትገኘው። መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጧ በአንፃራዊነት ለቱኒዚያና ሊቢያ የቀረበ  ቢሆንም በ3 ደሴቶች የተዋቀረችው ማልታ አውሮጳዊት ሐገር ናት። በዚህች አውሮጳ ደቡብ ወሽመጥ ላይ በምትገኝ ትንሽዬ ሐገር ውስጥ በስደት የሚገኙ ኢትዮጵያውያት እና  ኢትዮጵያውያን  እንደሚሉት በሕመምና በእርግዝና ከሆነ ብቻ ነው እንደ እስር ቤት ከሚቆጠረው መጠላያ ጣቢያ መውጣት የሚቻለው። ወጣት ብርቱካን አንከለ ከዚህ የመጠለያ ጣቢያ በእርግዝና ሰበብ ከወጣች ጥቂት ቀናት ነው የተቆጠሩት።

የ26 ዓመቱ ወጣት ሚኪያስ ጌታቸውም ከ11 ወራት በላይ ማልታ  በሚገኘው እስር ቤት መሰል መጠለያ ጣቢያ ውስጥ እንደቆየ ነው የሚናገረው። ያቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ እንደ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያት  እና ኢትዮጵያውያን  ስደተኞች በተደጋጋሚ ውድቅ እንደተደረገበት ገልፆልናል። ከዚያ መጠለያ ከወጣ ሳምንት ገደማ ቢሆነው ነው።

አፍሪቃውያን ስደተኞች ባህር ውስጥ
አፍሪቃውያን ስደተኞች ባህር ውስጥምስል picture-alliance/dpa


ሚኪያስ ከእስር ቤት መሰሉ መጠለያ ጣቢያ ነፃ የወጣው በባለቤቱ ህመም ምክንያት እንደሆነ ገልፆልናል። በእርግጥ ባለቤቴ መጠለያ ጣቢያ ከገባች ጀምሮ በተደጋጋሚ ለመታመሟ ሀኪም ማስረጃ ቢፅፍላትም ከጣቢያው የወጣችው ከወራቶች እስር በኋላ በቅርቡ ነውም ብሏል። ወጣት ሂወት አምዴ በስደተኝነት ማልታ ውስጥ ነው የምትገኘው። በህመም ምክንያት ነው ከሳምንት በፊት  ከመጠለያ ጣቢያው የተለቀቀችው። ወጣት ሂወት ከዚህ በላይ መቀጠል አልቻለችም። እምባ ተናነቃት እና ስልኩን ለባለቤቷ አቀበለችው። ባለቤቷ ወገኔ ከተማ ይባላል። እንደ ሂወት ሁሉ የ23 ዓመት ወጣት ነው።


በእስር ቤት የሚገኙ ሌሎች ወጣቶችን ለማግኘት ሞክረን ነበር። ስልካቸው ዝግ አለያም ከአገልግሎት ውጪ በመሆኑ ልናገኛቸው አልቻልንም። ከመሀከላቸው በከፍተኛ ህመም የሚሰቃዩ ወጣቶችም አንዳሉ ከእስር ቤት የወጡ ጓደኞቻቸው ገልፀውልናል። ወደፊት እስር ቤት የሚገኙትን ወጣቶች ማግኘት ከቻልን በሌላ ዝግጅት ልናቀርባቸው እንሞክራለን። «እርግዝና እና ህመም የነፃነት መንገዶች» በሚል ማልታ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያት እና ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ወጣቶችን የኑሮ ሁኔታ ያስቃኘንበት ዝግጅታችን በዚህ ይደመደማል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ