1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ሳምሰንግ ጋላክሲ ኖት 7

ረቡዕ፣ ጥቅምት 30 2009

ግዙፉ ሳምሰንግ ኩባንያ፦ ጋላክሲ ኖት 7 የተሰኘውን ዘመናዊ ስልክ አምርቶ ገና ከማከፋፈሉ ነበር ደምበኞች ምርቶቹን እንዲመልሱ ጥሪ ያስተላለፈው። ኩባንያው ስልኮቹ ከደምበኞች እጅ እንዲሰበሰቡ ያደረገው ባትሪያቸው የመንደድ ባሕሪ ስላላቸው ነው። እነዚህ ስልኮች በማንኛውም በረራ ላይ እንዳይገቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አግዷል።

https://p.dw.com/p/2SQNK
Samsung Galaxy Note 7
ምስል picture-alliance/AP Photo/A. Young-joon

እሳት ፈጣሪው የእጅ ስልክ

እጅግ ግዙፎቹ የሳምሰንግ እና የአፕል ኩባንያዎች በዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ምርት የአንገት ለአንገት ትንቅንቅ ከጀመሩ ወዲህ የተከሰተ ዱብ ዕዳ። አፕል ኩባንያ፦ አይፎን 7 የተባለውን ዘመናዊ ስልክ ለገበያ ሲያቀርብ፤ ወዲያው ተቀናቃኙ ሳምሰንግ ኩባንያ ደግሞ ጋላክሲ ኖት 7 የተሰኘውን ስልክ ይዞ በኩራት ብቅ አለ። ለዐይን ማራኪ፤ ለእጅ ቀለል ተደርገው የተሠሩት የሳምሰንግ ጋላክሲ ኖት 7 ስልኮች ግን ብዙም ሳይቆዩ ለኩባንያው ከባድ መከራ ነው ያሸከሙት።

በዓለም የተንቀሳቃሽ ስልኮች ገበያ ሽያጩ በከፍተኛ ፍጥነት እየተመነደገ የመጣው ሳምሰንግ ኩባንያ በጋላክሲ ኖት 7 ስልኮች መዘዝ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን አጥቷል። ኩባንያው በስነ-ቴክኒኩ ዘርፍ እጅግ ሲበዛ የተጠበበት ይኽ ዘመናይ ስልክ አድናቆትን ሳይኾን ለዓመታት ተጣብቶት የሚዘልቅ ጥቁር ጥላ ነው ያተረፈበት። 

የደቡብ ኮሪያው ሳምሰንግ ኩባንያ፦ ጋላክሲ ኖት 7 የተሰኘውን ዘመናዊ ስልክ ለገበያ ሲያቀርብ በስነ-ቴክኒኩ ዘርፍ እጅግ ተጨንቆ እና ተጠቦ የሠራው ምርቱ እንደኾነ በመግለጥ ነበር። በእርግጥም የኩባንያው ኢንጂነሮች አዲሱ ስልክን ከቀዳሚው ምርት በብዙ መልኩ የተለየ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ከስልኩ ጋር ተጣብቆ የተሠራው ባትሪ ግን መዘዝ አስከተለና ጠበብቱን እጀ-ሰባራ አደረጋቸው። 

የጋላክሲ ኖት 7 ባትሪ 3500 ሜሊ አምፒር አውር ሊትየም አዮን የሚባል ነው። ይኽ እጅግ ቀጭን ተደርጎ የተመረተው ባትሪ ነው እሳት በማስነሳት ለሳምሰንግ ኩባንያ መዘዝ ያስከተለው። የኮምፒውተር እና የኤሌክትሮኒክ እቃዎች ባለሞያው ንጉሡ ሰለሞን የጋላክሲ ኖት 7 ባትሪ እሳት የሚነሳበት ምክንያት «ስልኩ በእርግጥ ቴክኒካዊ ኅጸጽ» ስላለበት አይደለም ሲል ያብራራል። 

defektes Samsung Galaxy Note 7 Smartphone
ምስል Picture-Alliance/Shawn L. Minter via AP

እንደ ንጉሡ ማብራሪያ  ሳምሰንግ ኖት 7 የተባለውን የመጨረሻ ስሪት ስልኩን ነው የሰበሰበው። «ባትሪው ኃይል ለማግኘት ሙሊት ሲያከናውን ገደብ አልባ በመኾኑ ነው።» ባትሪው እጅግ ቀጭን ተሰርጎ የተሠራ በመኾኑ አስፈላጊው ኃይል «ከሞላ በኋላ የሚያደርገው መጠን አልባ ሙሊት ባትሪው ላይ ሙቀት በመፍጠር ሙቀቱ ከፍ እንዲል እና እሳት እንዲፈጠር ያደርጋል።» ሳምሰንግ ካመረታቸው ከ90 በመቶ በላይ ስልኮች «የዚህ የባትሪ ችግር ያለባቸው ነበሩ። ስለዚህ ሳምሰንግ ያለው ያለው አማራጭ ገቢውን አጥቶ ስልኮቹን በሙሉ መሰብሰብ ነበር። ስለዚህ ያንን እያደረገ ነው» ሲል የኮምፒውተር ሳይንስ ባለሙያው ንጉሡ ሰለሞን ገልጧል።

ሳምሰንግ ጋላክሲ ኖት 7 ባትሪው እየጋለ እሳት ማስነሳቱ መዘዝ አስከተለ እንጂ ለአያያዝ የሚመች እና ከቀዳሚው ምርትም በመጠን ከፍ የሚል ተደርጎ ነበር የተሠራው። ቀደም ሲል ሲቀርብበት የነበረውን ቅሬታ በማሻሻልም ምስሎችን፣ ቪዲዮዎችን አለያም ሠነዶችን በብዛት ለማቀፍ ተጨማሪ ካርድ እንዲቀበል ተደርጎ ነበር የተፈበረከው። ድረ-ገጾች በሚታሰሱበት ወቅት ከሌላው ጊዜ በተሻለ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅም ተደርጓል። 

ጋላክሲ ኖት 7ን ከሌሎች ስልኮች ለየት ካደረጉት ነጥቦች መካከል ስማርትፎን የሚባሉት ዘመናዊ የእጅ ስልኮች እና ወደ ኮምፒውተር የሚያዘነብሉ ታብሌቶች ቅይጥ መኾኑ ዋነኛው ነበር። እንደው በቀላሉ የሳምሰንግ መሀንዲሶች ብዙ ማሻሺያዎችን ለማድረግ እጅግ ሲበዛ ተጠበው ነበር ማለት ይቻላል። ጠበብቱ ጥረታቸው ውኃ ስለበላው ግን ኩባንያው ጋላክሲ ኖት 7 ምርቶቹን በአጠቃላይ ማምረት፣ መሸጥም ኾነ ማከፋፈል እንዳቋረጠ መስከረም 10 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. ለማወጅ ተገዷል። ኩባንያው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰውም ለደንበኞቹ ደኅንነት በሚል እንደኾነ ገልጧል። ሳምሰንግ፦ ጋላክሲ ኖት 7 ስልኮቹን ለመሰብሰብ ጥሪ ሲያስተላልፍ ሁለት አማራጮችን በመስጠት ነው።  

USA Apple Phil Schiller präsentiert das iPhone 7 Wasserdicht Feature
ምስል picture-alliance/ZUMA/G. Reyes

«የባትሪ ችግር ያለባቸውን ስልኮች ለማወቅ ‘ከስልኮቹ ጀርባ የሚገኙትን መለያ ኮዶች  ከሳምሰንግ ድረ-ገጽ ጋር በማመሳከር ከገዛችሁበት ቦታ ብቻ ሄዳችሁ እንድትመልሱ፤ አለያም ስትመልሱ ሁለት አማራጮች አሉ’ ብለዋል» ሲል ያብራራው ንጉሡ ሰለሞን ነው «አንደኛው ሙሉ ለሙሉ የተገዛበትን ገንዘብ መመለስ» እንደኾነ ገልጧል። ሁለተኛው አማራጭን ሲያብራራ ደግሞ እንዲህ ይላል። «ሁለተኛው ሌላ አይነት ስልክ ቅያሪ እንሰጣለን ብለው ነው  ማስታወቂያ ያስነገሩት።»

ኩባንያው በመግለጫውም ማንኛውም የሳምሱንግ ደንበኛ የግል ሠነዶቹን ከጋላክሲ ኖት 7 ስልኮች ወደ ሌሎች ማዕቀፎች አሸጋግሮ ስልኮቹን ሙሉ ለሙሉ በማጥፋት ከእንግዲህ እንዳይጠቀም  አሳስቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ ጥቅምት 11 ቀን፣ 2009 ዓም ባወጣው መግለጫ  የሳምሰንግ ጋላክሲ ኖት 7 የእጅ ስልኮች በማንኛውም በረራው ወቅት አውሮፕላኖቹ ውስጥ እንዳይገቡ ማገዱን አሳውቋል።  ቀደም ሲል ከሉዊስቪሌ ወደ ባልቲሞር ሊበር የተዘጋጀ የአሜሪካው የሳውዝዌስት የበረራ አገልግሎት አውሮፕላኑ ውስጥ ሳምሰንግ ስልክ ባትሪው ግሎ ጢስ በመፍጠሩ 75 ተሳፋሪዎቹን በፍጥነት ማስወጣቱን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ምንች መዘገቡ ይታወሳል። 

የሳምሰንግ ስልኮችን «ደንበኞቻችን በብዛት ለጥገና ወደ እኛ ያመጣሉ» ያሉት አዲስ አበባ በሚገኘው ዮናስ ሞባይል  የጥገና ክፍል ሠራተኛው አቶ ዘሪሁን ላቀው እስካሁን ለጥገና የመጣ ጋላክሲ ኖት 7 እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል። 

«የባትሪ ችግር ያለባቸው [ጋላክሲ ኖት 7] ስልኮች የአጋጣሚ ነገር ኾኖ እኛ ጋር አልመጡም። መረጃው አስቀድሞ ስለደረሰን ግን እኛም ስልኮቹ ሲመጡ ሰዎቹን በማስጠንቀቅ አንቀበልም። አንዳንድ ሰዎች ግን ስልኩን ይዘው መግባት አትችሉም ተብለው ከአየር ማረፊያ የተመለሱ እኛጋ መጥተው የጠየቁን አሉ። ከዛ ውጪ ባትሪው እሳት የማስነሳት ችግር ያለበት ስልክ እኛ ጋር አልመጣም። ኖት 7 አዲስ ምርት ስለኾነ አይመጣም። እኔ ራሴ የሚሠሩ ኖት 7 ስልኮች ያየሁት ሁለት ብቻ ነው።»

Südkorea Samsung Zentrale in Seoul
ምስል Getty Images/AFP/E. Jones

የደቡብ ኮሪያው ግዙፍ ኩባንያ ሳምሰንግ በጋላክሲ ኖት 7 የባትሪ ችግር የተነሳ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንዳጣ ይነገራል። ሳምሰንግ ኩባንያ ከደረሰበት ጉዳት ለማገገም ረዥም ጊዜ ሊወስደበት እንደሚችል ተገምቷል። ሳምሰንግ የጋላክሲ ኖት 7 ስልኮቹ እንዲመለሱለት ጥሪ ባስተላለፈበት ወቅት ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዳጣ የገበያ አጥኚዎች በክትትል ደርሰውበታል። 

ኩባንያው በገበያ ላይ ተሰራጭተው የነበሩ 2,5 ሚሊዮን የጋላክሲ ኖት 7 ስልኮቹ በሙሉ እንዲሰበሰቡ ጥሪ በማስተላለፉ የደረሰበት ኪሳራ በ2 ቢሊዮን ዶላር ብቻ አይወሰነም ሲል ፎርቢስ ጽፏል። ሳምሱንግ በምርቱ ላይ ያጠላበት መጥፎ ጥላ ለበርካታ ዓመታት እንደሚከተለው የዩናይትድ ስቴትሱ የንግድ መጽሄት ፎርቢስ በድረ-ገጽ እትሙ ገልጧል። ለኩባንያው የበለጠ ስጋት የኾነው ደግሞ አሰፍስፈው የሚጠብቁ የኩባንያው ተቀናቃኞች ናቸው። በሂዩንዳይ ተቋም ተመራማሪው ሊ ያንግ ጊዮን ያብራራሉ።

«ሳምሰንግ፦ በጋላክሲ ኖት 7 የተከሰተበት አጋጣሚ አፕል ኩባንያ የሳምሰንግን ደምበኞች ለማደን ምቹ ኹኔታ የፈጠረለት ያልጠበቀው ሲሳይ ነው። እጅግ አደገኞቹ ደግሞ የቻይና ኩባንያዎች ናቸው። ኩባንያዎቹ ሳምሰንግን እግር በእግር መከተል ከጀመሩ ሰነባብተዋል። እናም በቴክኒክ ለመላቅ እንዲህ አይነቱን አጋጣሚውን ሲጠብቁ ነበር። ይኼ መቼም ለሳምሰንግ ከባድ ምት ነው። ኩባንያው አሁን የተጋፈጠውን ጉዳት በጊዜ ለመገደብ ይቻለው ዘንድ አስተማማኝ እና ረቂቅ የኾኑ አዲስ ምርቶቹን ወደ ገበያው በቶሎ ማምጣት አለበት።»

ኩባንያው ላይ የደረሰው ጉዳት ገቢ በማጣት ብቻ አልተወሰነም። አንዳንድ ከሳምሰንግ ኩባንያ ጋር ይሠሩ የነበሩ የስነ-ቴክኒክ ተቋማት በጋራ መሥራታቸውን በማቋረጣቸው ደግሞ ወደ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ግድም ገቢ ለማጣት ይገደዳል ተብሎ ተገምቷል። 

Samsung Galaxy Note 7 verkohlt explodiert
ምስል picture- alliance/AP Photo/A.Zuis

ሳምሰንግ በዕቅዱ መሠረት ከተጓዘ ከገበያ የመከነው ጋላክሲ ኖት 7 ተከታይ የሚኾነውን ጋላክሲ ኤስ 8ን የካቲት ወር ላይ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ይኽን አዲስ ዘመናይ የእጅ ስልክ ለመፈብረክ ረቂቅ ማስተናበሪያዎችን የማበልጸግ ሥራ ላይ የተሰማሩት ባለሙያዎቹ እጅግ ከባድ ፈተና ነው የገጠማቸው። የመጀመሪያው ከባዱ ፈተና የጋላክሲ ኖት ባትሪ በእሳት መያያዝ የፈጠረውን ስጋት ቀንሶ ደምበኞችን መልሶ ማምጣቱ ነው። 

ሌላኛው ትልቁ ፈተና ደግሞ ከዋነና ተቀናቃኙ አፕል ኩባንያ የሚደርስበት ጫና ነው። በጋላክሲ ኖት 7 ውድቀት እጅግ ተጠቃሚ በመኾን ከፍተኛ ትርፍ ያጋበሰው አፕል የአይፎን 7 ተከታይ ምርቱን ሲያቀርብ ሌሎች ማሻሺያዎችን ስለሚያደርግ ከዛ ጋር ፉክክር ማድረጉም ሌላው የሳምሰንግ ጫና ነው። እነዚህን ጫናዎች ተቋቁሞ ሳምሰንግን ከገባበት ከፍተኛ ውጥረት ለማውጣት የኩባንያው መሥራቾች የልጅ ልጅ የኾኑት ሊ ያዬ ዮንግ የኩባንያውን አመራር ተረክበዋል። የሐርቫርድ ምሩቁ ሊ ግን ይኽን ሁሉ ጫና ተቋቁመው የደቡብ ኮሪያ ኩራት የሆነው ግዙፉ የሳምሰንግ ኩባንያን ከገባበት ማጥ ያወጡት እንደሆን ጊዜ የሚፈታው ነው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ