1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እስራኤል፤ የተኩስ አቁም ስምምነት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 19 2006

በእስራኤል እና በሃማስ ቡድን መካከል ለዛሬ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተከብሮ የዋለ ይመስላል። የነፍስ አድን ሠራተኞችም ይህንን የ12 ሠዓታት የተኩስ አቁም ስምምነት ተጠቅመው ሌሎች 35 አስክሬኖችን ከጋዛ ሰርጥ ፍርስራሾች እንዳወጡ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/1CjOy
ምስል DW/S. al Farra

ቆይቶ በደረሰን ዜና መሰረት ደግሞ እስራኤል የተኩስ አቁሙን ለቀጣይ 4 ሰዓታት ለማራዘም ተስማምታለች። ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ ሠርጥ ድንብር አቅራቢያ በሚገኘው የግብጽ የሲናይ በረሃ ውስጥ በወተነጨፈ ሮኬት ሰበብ ሁለት ህፃናት መገደላቸውን መና የተሰኘው የግብፅ ዜና አገልግሎት ድርጅት ጠቅሷል። በእዚህ ወር መጀመሪያ በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል ዳግም በተከፈተው ጦርነት የሞተው የፍልስጤማውያን ቁጥር ከ 1000 ከፍ ብሏል። ከሟቾቹ አብዛኞቹ ሲቪል ማህበረሰብ እንደነበሩ ተገልጿል። በእስራኤል በኩል ደግሞ ወደ 40 የሚጠጉ ወታደሮች እና 3 ሲቪሎች መገደላቸው ተመልክቷል።

Gaza Offensive 24.07.2014
ምስል Reuters

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ጊ ሙን እና የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ባደረጉት ጫና ነበር የእስራኤል ጦር እና የሃማስ ቡድን ከጠዋቱ ሁለት ሠዓት የሚጀምር፣ 12 ሰዓት ቆይታ ያለው የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ትናንት ምሽት የተስማሙት። የተኩስ አቁሙ እንደ ሀገሪቱ አቆጣጠር እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ይቆያል ተብሎ ይታመናል።

በሌላ በኩል የአዉሮጳ ኅብረት የዉጭ ጉዳዮች ተጠሪ ወ/ሮ ካትሪን አሽተንን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ ፓሪስ ተገናኝተው በእስራኤል እና በሃማስ ቡድን መካከል የተጀመረውን የተኩስ አቁም እንዴት ዘላቂ ማድረግ እንደሚችል ተወያይተዋል።

ምንም እንኳን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለአራት ሠዓታት ቢራዘምም የእስራኤል ጦር የሐማስ ታጣቂዎች እየተሽሎኮሎኩ ጥቃት ያደርሱባቸዋል ያለቻቸውን የመሬት ውስጥ ለውስጥ መተላለፊያዎችን በሚቀበሩ ፈንጂዎች ማውደሜን አላቋርጥም ማለቷም ተደምጧል።

ማንተጋፍቶት ስለ

ልደት አበበ