1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እስራኤል፤ የኢትዮጵያ አይሁዳዉያንን የመዉሰድ እቅድ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 15 2010

የእስራኤል መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ቀርተዋል ያላቸዉን ቤተ እስራኤላዉያን በተቻለ ፍጥነት ወደ ሀገሩ እንደሚወስድ ገለፀ። በኢትዮጵያ ጉብኝታቸዉ ትናንት አዲስ አበባ የሚገኝ አንድ ምኩራብ የተገኙት የእስራኤል የፍትህ ምኒስትር አይሌት ሻከድ እንደገለፁት ሀገራቸዉ ቤተ እስራኤላዉያኑን ወደ መሬቷ የመመለስ ተግባርዋ ቀላል እንደማይሆን ጠቁመዋል።

https://p.dw.com/p/2wWkz
Äthiopien Israel Justice Minister Ayelet Shaked
ምስል picture-alliance/dpa/AP Photo/M. Ayene

መንግሥት ቢፈልግ አጠቃሎ መዉሰድ ይችል ነበር።

ኢትዮጵያን የጎበኙት የእስራኤል የፍትህ ምኒስትር በቆይታቸው ወቅት እንደተናገሩት ሀገራቸዉ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ አይሁዳዉያንን በተቻለ ፍጥነት እንደምትወስድ ቃል ገብተዋል። ምኒስትሯ ወደ ስምንት ሺህ ግድም የሚሆኑ የኢትዮጵያ አይሁዳዉያን አሁንም በኢትዮጵያ እንደሚኖሩ ተናግረዋል። በቴልአቪቭ ዩንቨርስቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ዶክተር አንበሴ ተፈራም የኢትዮጵያዉያን አይሁዳዉያኑ ቁጥር ወደ ስምንት ዘጠኝ ሺህ  እንደሚሆን ነዉ የጠቆሙት። ከነዚህም መካከል እስከባለፈዉ የአዉሮጳዉያን ዓመት ማለቂያ ድረስ ወደ አንድ ሺ የሚሆኑቱ እስራኤል መግባታቸዉንም ያስረዳሉ።  

« በኢትዮጵያ የሚገኙት የአይሁዳዉያን ማኅበረሰብ አባላት እንደሚሉት በኢትዮጵያ የሚገኙት ቤተ እስራኤላዉያን ቁጥር ወደ ዘጠኝ ሺህ ይደርሳል። አብዛኞቹም የሚኖሩት ጎንደር ዉስጥ ነዉ በእርግጥ አብዛኞች መጥተዋል እንደ አዉሮጳዉያኑ 2017 ዓመት መጨረሻ ድረስ ወደ አንድ ሺህ የሚሆኑት ወደ እስራኤል መጥተዋል። ግን ከነሱ ዉጭ ከ 20 ዓመታት በላይ አዲስ አበባ የተቀመጡና ወደ እስራኤል ለመጓዝ እየተጠባበቁ ያሉ አይሁዳዉያን አሉ። »

Äthiopien Israel Justice Minister Ayelet Shaked
ምስል picture-alliance/dpa/AP Photo/M. Ayene

በአዲስ አበባ የሚገኙት የኢትዮጵያ አይሁዳዉያን ወደ እስራኤል ለመምጣት ስማቸዉ በመዝገብ ይኑር አይኑር በርግጥ አላዉቅም ያሉት የሥነ- ልሳንና የታሪክ ምሁሩ ዶክተር አንበሴ ተፈራ፤ ቤተ እስራኤላዉያኑን ወደ እስራኤል ለማምጣት ከልብ ከተፈለገ ቀላል መሆኑን የከዚህ ቀደሙን የአጓጓዝ ታሪክ በማነጻፀር አመልክተዋል። 

«መንግሥት ቢፈልግ በአንድ ጊዜ አጠቃሎም  መዉሰድ ይችል ነበር። ለምን ቢባል የዛሬ 26 ዓመት ኦፕሬሽን በተባለዉ ዘመቻ በ 36 ሰዓታት ዉስጥ 14 ሺህ ሰዎች ነዉ ከኢትዮጵያ የተጓጓዙት፤ ይህ ማለት ሁለት ቀን በማይሞላ ጊዜ ማለት ነዉ። አሁን እነዚህን አስቀምጠዉ በየዓመቱ አንድ አንድ ሺህ እንወስዳለን እያሉ እንደሚያሰቃዩ አይገባኝም። ሁሉም የተመዘገቡና ይሁዲ እንደሆኑ የተረጋገጠላቸዉ ናቸዉ። ችግሩ ግን ምንድነዉ መንግሥት ቶሎ ብሎ በአንድ ዓመት በሁለት ዓመት ካልወሰደ እነዛ ሰዎች ይወልዳሉ አዲስ ልጅ ይመጣል ሌላ ለምዝገባ ለማረጋገጫ ሌላ ችግር ይፈጠራል። በዚህ ምክንያት ያለዉ ችግር እንዲቆይና መፍትሄ ሳያገኝ እንዲጓተት ነዉ የሚደረገዉ። ኢትዮጵያም ያለስራ በጥበቃ ላይ ቁጥብለዉ በሚጠብቁበት ጊዜ በረሃብ የሚሞቱ በበሽታ ሁሉ የሚሞቱ አሉ። እዚህም ያለ ዘመድም እየተሰቃየ ነዉ ። ኑሮዉ ከዝጅ ወደ አፍ ነዉ ከዝያ ላይ ደግሞ ቆንጥሮ ኢትዮጵያ ለቀረዉ ዘመዱ በመላክ ይቸገራል። »   

በሳምንቱ መጨረሻ አዲስ አበባ ላይ የነበሩት የእስራኤሏ የፍትህ ምኒስትር አይሌት ሻከድ ቤተ እስራኤላዉያኑን ከቤተሰቦቻቸዉ መቀላቀሉ ቀላል አለመሁኑን ተናግረዋል ። እንደ እኔ ግምት ገሚሱ ሃይማኖታቸዉን በመተዋቸዉ ሊሆን ይችላል ያሉት ዶክተር አንበሴ የዘረኝነት ሁኔታም እንዳለ ሊካድ አይገባም ሲሉ ተናግረዋል።

«እዉነት ለመናገር  አንዳንድ ጊዜም የዘረኝነት ሁኔታም ይታያል። አሁን ለምሳሌ ከራሽያ ከሌሎች ሃገሮች የሚመጡት ይህ አይነት ችግር የለባቸዉም። እኔ እንደምሰማዉ ከሆነ ከራሽያ አካባቢ የሚመጣ ስለሌለ መንግሥት ወደዝያ እየሄደ ምናልባት አያትህ ይሁዲ ይሆን እንዴ እያሉ እነዛን እነዛን እየጠየቁ ወደ እስራኤል ያመጣሉ።​​​​​​​ እና የቆዳ ቀለም ችግርም አለ ይህን ዝም ብሎ መሸፋፈን አይቻልም። ሁለተኛዉ ደግሞ ከራሽያ የሚመጣዉ ተምሮ ነዉ የሚመጣዉ እዚህ ሲመጣ ስራ ይይዛል በየቦታዉ ይገባል፤ ግን ከኢትዮጵያ ከሆነ ያን ሰዉ ለማስተማር ቦታ ለማስያዝ ብዙ ገንዘብ ወጭ ማድረግ ያስፈልጋል። የኤኮኖሚዉንም ሸክምን በመፍራትም ይሆናል። ግን እስራኤል ከዓለማችን በኤኮኖሚ በጣም ጠንካራ ከሚባሉት ሃገራት መካከል አንድዋ ናት። ከኢትዮጵያ ስምንት ሰዎችን ማምጣት ለእስራኤል ከባድ አይደለም። በ 90ዎቹ ዓመታት መጀመርያ ከኢትዮጵያ ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ዉስጥ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ አይሁዳዉያን ከኢትዮጵያ መጥተዋል። »  

Äthiopien Israel Justice Minister Ayelet Shaked
ምስል picture-alliance/dpa/AP Photo/M. Ayene

ከእስራኤል ነዋሪዎች መካካከል ሁለት በመቶዉ የኢትዮጵያ አይሁዳዉያን መሆናቸውንም የታሪክ ተመራማሪዉ ዶክተር አንበሴ ተፈራ ገልጸዋል። እንደ አሶሺየት ፕሬስ ዘገባ ደግሞ ከስምንት ሚሊዮን እስራኤላዉያን መካከል 140 ሺህ የሚጠጉት ከኢትዮጵያ የመጡ አይሁዶች ናቸዉ።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ