1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እነአቶ በረከት ኮምፒዩተር ይግባልን ሲሉ ጠይቁ

ዓርብ፣ የካቲት 1 2011

እነ አቶ በረከት ዛሬ የ14 ቀናት ቀጠሮ ተጠየቀባቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸዉ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮውን ተቃውመዋል። ፍርድ ቤት ስንገባም ሆነ ስንወጣ ህገ-መንግስታዊ መብታችን ተጥሶ ክብራችንና ሰብኣዊ መብታችን የሚነካ ስድብ እየተሰደብን በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ይህን ያስቁምልን ፤ መንግስት ጠበቃና የህግ አማካሪም ያቁምልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

https://p.dw.com/p/3D0dx
Äthiopien Gerichtshof in Bahir Dar
ምስል DW/A. Mekonnen

መብታችን የሚነካ ስድብ እየተሰደብን በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ይህን ያስቁምልን

እነአቶ በረከት ኮምፒዩተር ይግባልን ሲሉ ጠይቁ

እነ አቶ በረከት ዛሬ እንደገና የ14 ቀናት ቀጠሮ ተጠየቀባቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ደግሞ በባሕር ዳርና አካባቢው ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ሆነ የአማራ ክልል ሥነ- ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን የተጠረጠርንበትን ጉዳይ የማየት ስልጣን የለውም፣ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮውንም ተቃውመዋል። ፍርድ ቤት ስንገባም ሆነ ስንወጣ ህገ-መንግስታዊ መብታችን ተጥሶ ክብራችንና ሰብኣዊ መብታችን የሚነካ ስድብ እየተሰደብን በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ይህን ያስቁምልን ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ፍርድቤቱ የአማራ ክልል ሥነ-ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀበትን ምክንያትና ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን አቤቱታ ከተመለከተ በኋላ የአማራ ክልል ስነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን መርማሪ ያቀረበውን የ14 ቀናት ቀጠሮ ተቀብሎ ተጠርጣሪዎች የካቲት 15/2011 ዓ ም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ሲወስን ሌሎች ግለሰባዊ ጉዳዮችን በተመለከተ አቤቱታቸውን ለማረሚያ ቤት አስተዳደር በማመልከት ጉዳዩን አይቶ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይሰጣል ብሏል።ዛሬም የባሕር ዳርና አካባቢው ከፍተኛው ፍርድ ቤት በጠዋቱ ነበር የተሰየመው፡፡ አቶ በረከት ስምዖን ወደ ፍርድ ቤቱ ሲገቡ ከባለፈው አለባበሳቸው ብዙም አልተለዩም፣ አቶ ታደሰ ካሳም እንዲሁ። የአማራ ክልል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እነ አቶ በረከት  “ ህዝባዊ ድርጅትን በማያመች መንገድ መምራት” በሚል የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ለመመርመር የተለያዩ ቀሪ የምርመራ ስራዎች ስለሚቀሩኝ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠየቀ፡፡ ኮሚሽኑ ባለፉት 14 ቀናት ያደረጋቸውን የምርመራ ሂደቶች ካስረዳ በኋላ  ቀሪ የምርመራ ሥራዎች ያላቸውንም ለፍርድ ቤቱ  አብራርቷል፡፡ ከጉዳዩ ጋር ተያያዣ የሆኑ ሰነዶችን ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች በደብዳቤ ጠይቀን የአንዳንዶቹን ምላሽ በጊዜ ማግኘት አልችልንም፣  ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ዲዮት ባሰሪ ለተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ በ90 ሚሊዮን ዶላር ሲሸጥ ሰነዶቹ እንዳገኑ ሆን ተብሎ በተለያዩ ቦታዎች የተበተኑ በመሆኑና ያን ለማሰባሰብ ጊዜ በመጠየቁ፣ ጉዳዩን የሚያስረዱ ምስክሮች በሀገር ውስጥና ከአግር ውጭም በመሆናቸውና እነሱን ለማግኘት ጊዜ በማስፈለጉ፣ ዳሽን አክሲዮን ማህበር የኦዲት ስራው ያላለቀ በመሆኑና 50% የአክሲዮን ድርሻ ባርክሌይ በሚባል የውጭ አገር ባንክ በግለሰብ ስም በመገኘቱ፣ ይህን ሰነድ ለማግኘት ጊዜ በመጠየቁና የወንጀሉ ድርጊት ውስብስብ በመሆኑ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ነው የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ፍርድ ቤቱን የጠየቀው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው የዳሽን አክሲዮን ማህበር በአማራ ክልል ያልተመዘገበ በመሆኑና በፌደራሉ መንግስት የተመዘገበ በመሆኑ የተጠረጠርንበት ወንጀል በፌደራል ደራጃ መታየት አለበት፣ አጣርተን እናስራለን በሚባልበት በዚህ ወቅት አስሮ ማጣራት ትክክል አደደለም በሚል የዳሽን አክሲዮን ማህበር የኦዲት ስራ ባለመጠናቀቁ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጥ የሚለውን የአማራ ክልል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ያቀረበውነ አቤቱታ ተጠርጣሪዎቹ ነቅፈውታል፡፡ በተጨማሪም ይህ ፍርድ ቤትም ሆነ የአማራ ክልል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የእኛን ጉዳይ የመመልከት ስልጣን የለውም በሚል የተለያዩ የህግ አንቀፆች እየጠቀሱ ተከራክረዋል፡፡ሁለቱም የቀድሞዎቹ የኢህዴን መስራቾች፣ የብአዴን መሪዎችና የአዴፓ ተሰናባቾች የተጠረጠሩበት ጉዳይ ጥቅል ስለሆነም በዝርዝር እንዲቀርብላቸው  ጠይቀዋል፡፡ ተጨማሪ የ14 ቀናት መጠየቁም እኛን ለማጉላላት አንጂ ማረሚያ ቤት የሚያቆይ ጉዳይ የለብንም በማለት የአማራ ክልል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ያቀረበውን ጥያቄ አልተቀበሉትም፡፡

አቶ በረከት ጠበቃና የህግ አማካሪ መንግስት እንዲቆምላቸውም ጠይቀዋል፡፡ የታሰርንበት ማረሚያ ቤት ኮምፒዩተር የሌለው በመሆኑ እንተርኔት ማየት አልቻልሁም፣ በተጠረጠርኩበት ዙሪያም ፅሁፎችን ማዘጋጀት አልቻልሁም በመሆኑም ኮምፒዩተር ይግባልን እንዲሁም ፍርድ ቤት ስንገባም ሆነ ስንወጣ ህገመንግስታዊ መብታችን ተጥሶ ክብራችንና ሰብኣዊ መብታችን የሚነካ ስድብ እየተሰደብን በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ይህን ሊያስቆምልን ይገባል ሲሉም በተለይ አቶ በረከት ጠይቀዋል፡፡ ተጠርታሪዎቹ ላቀረቧቸውን አቤቱታዎች  የአማራ ክልል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ መልስ ሰጥቶባቸዋል፡፡ ኮሚሽኑ አሁን እያደረገ ያለው “የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ” በመሆኑ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች በመደበኛ ክርክር ወቅት የሚመለሱ እንደሆኑ፣ ኮሚሽኑ የህዝባዊ ድርጅቶችን ጉዳይ የማየት ስልጣን እንዳለውና ሌሎች የቀረቡ ጥያቄዎች ደግሞ በመጀመሪያው የፍርድ ቤት ውሎ መልስ ያገኙ ናቸው ሲል አስረድቷል፡፡የግራ ቀኙን አሰተያቶች የተመለከተው የባሕር ዳርና አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኮሚሽኑ መርማሪ ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ በመሆኑ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮውን በመፍቀድ ተጠርጣሪዎቹ ለየካቲት 15/2011 ዓም እንዲቀርቡ ወሰኗል፡፡ በመጨረሻም ግለሰባዊ መብቶችን በተመለከተ ተጠርጣሪዎቹ አቤቱታቸውን ለማረሚያ ቤት አስተዳደር እንዲመለክቱና  ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ ችሎቱ አስረድቷል፡፡

 

 ዓለምነው መኮንን 

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ