1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እነ አቶ በረከት በአራት ጭብጦች ክስ ተመሰረተባቸው

ሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2011

እነ አቶ በረከት ስምዖን በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው። የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ ፈጽመዋቸዋል በተባሉ የሙስና ወንጀሎች ዛሬ ክስ ተመሰረተባቸው። ተከሳሾቹ በአጠቃላይ ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ አባክነዋል በሚል ተጠርጥረዋል።

https://p.dw.com/p/3HEMS
Äthiopien Regierungsvertreter
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

2.2 ቢሊዮን ብር በላይ አባክነዋል በሚል ተጠርጥረዋል

አቶ በረከት እና አቶ ታደሰ ባህር ዳር በሚገኘው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ የቀረቡት አብረዋቸው ከተከሰሱት አቶ ዳንኤል ይግዛው ከተባሉ ተጠርጣሪ ጋር ነበር። በክስ መዝገብ ላይ በሶስተኛ ተከሳሽነት የተመዘገቡት አቶ ዳንኤል “ዱቬንቱስ ዊንድ” የተባለ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።

የእነ አቶ በረከትን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 3ኛ ምድብ ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበውን ክስ ለመመልከት እና የተከሳሾቹን የእምነት ክህደት ቃል ለመስማት ነበር። በቀድሞዎቹ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ምርምራውን ሲያካሂድ የቆየው የአማራ ክልል ስነ ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ከነበረው የችሎት ውሎ አስቀድሞ የምርመራ ውጤቱን የሚያሳይ ሰነድ ለተጠርጣሪዎቹ ሰጥቶ ነበር። ተጠርጣሪዎቹ 1,009 ገጾች ያሉትን ሰነድ ችሎት ከመቅረባቸው አንድ ቀን በፊት እንደተቀበሉ ገልጸው ሰነዱን አንብቦ ለመረዳት ጊዜ ያንሰናል በማለታቸው ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል። 
በዛሬው ችሎት ተከሳሾች የቀረበባቸውን አራት የሙስና ወንጀሎች በዝርዝር አዳምጠዋል። የመጀመሪያው ክስ ከዳሽን ቢራ ፋብሪካ የአክስዮን ድርሻ ሽያጭ ጋር የተያያዘ ነው። ዳሽን ቢራ ፋብሪካ የማምረትም ሆነ የገበያ አቅም እያለው እና ተገቢው ጥናት ሳይካሄድ ተጠርጣሪዎቹ 50 ነጥብ 14 በመቶ ድርሻውን ለእንግሊዙ ዱየት ቢቬሬጅ ፋብሪካ በመሸጥ ጉዳት ማድረሳቸው በክሱ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም “ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ሲባል በፋብሪካው ላይ ከ1.9 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ሊደርስ ችሏል” በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ሁለተኛው ክስ የአዋጭነት ጥናት ሳይካሄድ “ዱቬንቱስ ዊንድ” ከተባለ የግል ኩባንያ ጋር የመብራት እና የውሃ ቆጣሪ እንዲያመርት ተከሳሾቹ ከህግ አግባብ ውጭ በመዋዋል ጉዳት ማድረሳቸውን ያትታል። በዚህም ለባንክ ዋስትና በመስጠት፣ ለፋብሪካ ግንባታ ኪራይ፣ ለህንፃ ጥገና በሚል ምንም አይነት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሳይኖር ከ210 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲባክን አድርገዋል በሚል ተከስሰዋል፡፡

በሶስተኛ እና በአራተኛ ክስ ደግሞ ከ“ዱቬንቱስ ዊንድ” ኩባንያ ጋር በትያያዘ የኩባንያውን ጥቅም ማስጠበቅ ሲገባቸው የባንክ እዳ ጭምር በመክፈል ከ149 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል በሚል በዋና ወንጀል አድራጊነት ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ በሁለተኛ እና ሶስተኛ ክሶች የዱቬንቱስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ስራ አስኪያጅ እና ባለቤት አቶ ዳንኤል ይግዛው ተካተውበታል፡፡

ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እና የክስ መቃወሚያቸውን ለፍርድ ቤቱ በፅሁፍ የሰጡ ሲሆን ይዘቱን ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ፍርድ ቤቱ መቃወሚያቸውን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ በመስጠት የዛሬ ውሎውን አጠናቅቋል።

ጠበቆቻቸው ማስፈራሪያ ስለደረሰባቸው የህግ አማካሪ ለማግኘት መቸገራቸውን ገልጸው የነበሩት አቶ በረከት እና አቶ ታደሰ ዛሬም ችሎት የቀረቡት ያለ ጠበቆቻቸው ነው። አብረዋቸው የተከሰሱት የአቶ ዳንኤል ጠበቃ ግን በችሎቱ ተገኝተዋል። 

ዓለምነው መኮንን

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ