1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እነ አቶ በረከት ጉዳያቸው አዲስ አበባ እንዲታይ ጠየቁ

ዓርብ፣ ጥር 17 2011

አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ከእስር እንዲለቀቁ እና ጉዳያቸውም በአዲስ አበባ እንዲታይ ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄያቸውን አቃቤ-ሕግ ተቃውሟል። ሁለቱ የቀድሞ ጉምቱ ሹማምንት በእስር ቤት መሰደባቸውን፤ ምግብ እንዳልቀረበላቸው እና ቤተሰቦቻቸው ጉዳያቸውን ከመከታተል መከልከላቸውን ጠቅሰው አቤቱታ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/3C9pF
Äthiopien Regierungsvertreter
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በባሕር ዳር ከተማ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት ቀረቡ።

 

 

ተጠርጣሪዎቹ "ከእስር ተለቅቀን ክርክራችንን በውጭ እናድርግ" ሲሉ ቢጠይቁም አቃቤ ሕግ "ሰነድ ሊያጠፉብኝ ስለሚችሉ ጥያቂያቸውን እቃወማለሁ" ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች ለየካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም.  አንዲቀርቡና ወደ ማረሚያ ቤት አንዲወርዱ አዝዟል፡፡

ጉዳዩን የሚመለከው የባህር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ዛሬ ከጠዋቱ 3፡47 ተሰየሙ፣ 3፡50 ላይ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ተከታትለው ወደ አዳራሹ ገቡ፡፡

አቶ በረከት ስምዖን ከስር ነጭ ሸሚዝና ጠቆር ያለ ሱሪና ኮት ለብሰዋል ነጠላ ጫማ አድርገዋል፡፡

አቶ ታደሰ ካሳ ነጣ ያለ ኮት ከነጭ ሸሚዛቸው ላይ ደርበዋል። ቡኒ ሱሪ ለብሰዋል እሳቸውም እንደ አቶ በረከት ሁሉ ነጠላ ጫማ ነው ያደረጉት፡፡ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች ስለራሳቸው እንዲያብራሩ ጠየቀ፡፡ አቶ በረከት እድሚያቸው 62፣ ባለትዳር፣ የ3 ልጆች አባትና አሁን ስራ እንደሌላቸው አብራሩ፡፡

አቶ ታደሰ ካሳም እድሜያቸው 53፣ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት እንደሆኑ ተናገሩ፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የተከሰሱበትን የክስ ማመልከቻ ለእያንዳንዳቸው እንዲደርስ ካደረገ በኋላ ምላሽ እንዲሰጡ ጠየቀ፡፡ ድርጊቱን እንዳልፈፀሙ ግለሰቦቹ መልስ ከሰጡ በኋላ በፖሊስ ጣቢያ የደረሰባቸውን ጫና አብራርተዋል፡፡

አቶ በረከት ሲያብራሩም ከዚህ በፊት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በደቦ ፍርድ እየተሰጠኝ ነው የደበረ ማርቆሱን ድርጊት ለአብነት በማንሳት፡፡ ትናንትና በቁጥጥር ስር ባለሁበት ፖሊስ ጣቢያ ሌባ፣ ዘራፊ፣ ነፍሰ ገዳይ እየተባልሁ ተሰድቤያለሁ፣ ስለሆነም የክልሉ መንግስት ክብራችን ሊያስጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡ ቤተሰቦቼ የፍርድ ሂደቱን እንዳያዩ ተከልክለዋል፣ ምግብ አልተሰጠንም የሚሉ ቅሬታዎችን አቅርበዋል፡፡

አቶ ታደሰ ካሳ በበኩላቸው ተመሳሳይ ስድብ እንደደረሰባቸውና የህግ የበላይነት እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡

አቶ በረከት መንግስት የሚያውቀው የደም መርጋትና የልብ ህመም እንዳለባቸው፣ አቶ ታደሰም አንደዚሁ የአስም በሽተኛና የልብ ህመም እንዳለባቸው ለፍርድ ቤቱ አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም በርካታ መድሀኒቶች አንደሚወስዱ ቤተሰቦቻቸው እያዘጋጁ የሚያቀርቡላቸውን ሀኪም ያዘዘው ምግብ በተወሰነ ሰዓት እንደሚመገቡ ጠቁመው ስለሆነም ጉዳያችን ቤተሰቦቻችን ባሉበት በአዲስ አበባ ይታይልን የሚል ጥያቄ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡

እንደዚሁም የተጠረጠሩበት ወንጀል በእስር ቤት ሆኖ ለመከራከር የሚያስችል መሰረት ስለሌለው በውጭ ሆነን እንከራከር ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አቶ በረከት በተለይ ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከታገዱ በኋላ ወደ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ አንዲሁም በአገር ውስጥ በስም መጥቀስ ባይፈልጉም እርሳቸው “የሽፍቶች መደበቂያ” ተብሎ ይጠራል ወዳሉት አካባቢ ድረስ መሄዳቸውንና ጉዳያቸውን በራስ መተማመን ከእስር ውጭ ሆነው መከራከር እንደሚችሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

አቃቢ ህግ በሰጠው ምላሽ ተጠርጣሪዎች ይመሩት የነበረው ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ለአንድ የውጭ ኩባንያ በ90 ሚሊዮን ዶላር መሸጡን ጠቁሞ ነገር ግን ፋብሪካው የተሸጠበት ገንዘብ በጥረት ውስጥም ሆነ በዳሽን ቢራ ካምፓኒ ውስጥ አይገኝም ብሏል፡፡

 ሌሎች አስፈላጊ ሰነዶችም ያልተሰበሰቡ በመሆኑ ግለሰቦቸን ከእስር መልቀቅ ከነበራቸው ስልጣን አንፃር መረጃ ያጠፋሉ የሚል ስጋት ስላለ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት አንዲከታተሉ ጠይቋል፡፡

ጉዳያቸውም በባሕር ዳር የሚታየው የተጠረጠሩበት ወንጀል የተፈፀመው በአማራ ክልል በመሆኑ እንደሆነና ወደ አዲስ አበባ ይዛወርልኝ የሚለው ጥያቄ ተቀባይነት የለውም ብሏል አቃቤ ህግ፡፡ አመጋገባቸውን በተመለከተ አስካሁን የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አቅም በፈቀደ መጠን ሲያቀርብላቸው መቆየቱን ጠቅሶ ካሁን በኋላ ግን ቤተሰቦቻቸው እንዲያቅርቡ አመልክቷል፡፡ እንደዚሁም ለተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የ14 ቀናት አንዲፈቀድለት አቃቤ ህግ ጠይቋል፡፡

የግራ ቀኙን አስተያየት ካዳመጠ በኋላ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በዚሁም መሰረት ግለሰቦቹ ከነበራቸው ከፍተኛ ስልጣን አንፃር መረጃ ሊያጠፉ ይችላሉ ከሚል እሳቤ ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ፣ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት የተፈፀመው በአማራ ክልል በመሆኑ ጉዳያቸው በዚሀ በባህር ዳር እንዲታይ ወሰኗል፡፡

ቤተሰቦቻቸውም በማንኛውም የፍርድ ሂደት ወቅት እየቀረቡ እንደማንኛውም ሰው ሂደቱን እንዲከታተሉ፣ አቃቤ ህግ የጠየቀው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተግባራዊ እንዲሆንና የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ፣ ፖሊስም አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግላቸው በማለት ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ወስኗል።

የእለቱን የፍርድ ሂደትም ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ55 ደቂቃ ላይ ተጠናቅቋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

እሸቴ በቀለ