1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ተፈናቃዮች ልብሳቸውን እንደ ሽንት ጨርቅ እየተጠቀሙ ነው»

ዓርብ፣ ጥቅምት 12 2014

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሊዮን  የሚቆጠሩ ሰዎች ጦርነት ሸሽተው ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። እነሱም ፈጣን ርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ይህንንም የተገነዘቡ እና በውጪው ዓለም የሚገኙ ግለሰቦች በተለያየ መንገድ በአሁኑ ሰዓት ርዳታ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ አንዱ በጀርመን ሀገር ነዋሪ የሆነው ተስፋዬ አበበ ነው።

https://p.dw.com/p/420vM
Äthiopien I Kriegsvertriebene in Dessie
ምስል T. Abebe

የወጣቶች ዓለም

ተስፋዬ አበበ ካለፈው ወር አንስቶ በፌስቡክ ገፁ አማካኝነት የርዳታ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀምሯል።ገንዘቡ የሚውለው በጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ እና ደሴ ከተማ ለተጠለሉ ሰዎች ሲሆን የመጀመሪያውም ዙር ርዳታ ሰሞኑን ለተረጂዎች ደርሷል ይላል። በጀርመን በተለይ ኮሎኝ ከተማ ብዙ ኢትዮጵያውያንን የሚያውቀው ተስፋዬ ከዚህ ቀደም የኢትዮ-ኮሎኝ ስፖርትና ባሕል ማኅበር ሊቀመንበር ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የዚሁ ማህበር ምክትል ሊቀመንበር እና በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባህል ፌደሬሽን ፀሀፊ ነው። ለዚህ የወጣቶች ዓለም ዝግጅትም አዲስ አይደለም። « በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ጦርነት ምክንያት በጣም ብዙ ስደተኞች ወደ ደሴ ከተማ መምጣታቸውን እዛ ካሉ ቤተሰቦቼ ስሰማ እና እኔም እዛ ስላደኩኝ ብዙ መረጃ ደረሰኝ» የሚለው ተስፋዬ ጓደኞቹ የርዳታ ማሰባሰቡን እንዲጀምር እንዳበረታቱት ይናገራል። እሱም በአካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ርዳታ ማሰባሰብ ጀመረ።» የማላውቃቸው ሰዎች ሁሉ ስልክ ደውለው ገንዘብ የሰጡኝ ሰዎች አሉ» ይላል ተስፋዬ። ወደፊት ደግሞ ከቤተክርስትያን እና ምግብ ቤቶች ገንዘብ የማሰባሰብ እቅድ አለው።

አሉላ አሰጋኸኝ እና ኑሩ መሀመድ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። ተስፋዬ ከጀርመን የሚያስተባብረውን ገንዘብ እንዴት በስራ ላይ እንደሚውል እያማከሩት አብረውት ይሰራሉ። ነጋዴው ኑሩ ከተስፋዬ ጋር መስራት ከመጀመሩ በፊትም የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመርዳት ተሳትፎ ስለሚያውቅ ሰዎቹ በፍጥነት የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ለመለየት ጊዜ አልፈጀበትም። « ከሰሜን ወሎ የተፈናቀሉ ሰዎችን በግሌ ሄጄ አይቼ የነበረ ጊዜ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ በጣም ከፍተኛ የሆነ ችግር ነበረባቸው።»  ይህንንም ችግር ለአሉላ እና ተስፋዬ አጋርቶ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተጠለሉ ስደተኞችን ጎብኝተው ርዳታውን አድርሰዋል። ኑሩ ወደፊትም ህፃናት ላይ እና ሴቶች ላይ ተተኩሮ መሠራት እንዳለበት ያሳስባል።

አሉላ ሁለት ኃላፊነት አለው። በአንድ በኩል ከጀርመን ተሰባስቦ የሚደርሰውን ገንዘብ ተጠቅሞ ቁሳቁስ መግዛት እና ለተፈናቃዮቹ መስጠት ሲሆን ሌላው ደግሞ ይህንን ርዳታ ላበረከቱ ሰዎች በተጨባጭ የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ ነው። ኃላፊነቱን እንዴት እየተወጣው ይሆን? « በመጀመሪያው ዙር ርዳታ የተወሰኑ ፎቶዎች ልከናል። በሁለተኛው ዙር ደግሞ ይበልጥ ተዓማኒ እንዲሆን በቪዲዮ ቀረፃ እና ቃለ መጠይቅ ለማድረግ» አስቤያለሁ ይላል። መርዳት የሚፈልጉ አካላት ደግሞ ርዳታ የማይደርሳቸው አካባቢዎች ስላሉ ሁሉንም ቦታዎች እንጎበኙ ይመክራል።
ወደ ደሴ ከተማ ተፈናቅለው የሄዱ ሰዎችን ቀጥሎ ለመርዳት ግን ራሳቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ደህንነት ወሳኝ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን አሉላ እንደሚለው ከፍተኛ አለመረጋጋት ከተማዋ ላይ ይስተዋላል። « ደሴ ከተማ የሚኖሩ ነጋዴዎች እና ነዋሪዎች ርግጠኛ ባልሆነ ወሬ እየተደናገጡ የንግድ ቦታቸውን እየዘጉ እቃጨውንም እየጫኑ እየሄዱ ነው።» አሉላ በርግጠኝነት መናገር የሚችለው ግን የከባድ መሳሪያ ድምፅ በከተማዋ ይሰማ እንደነበር ነው።  ጀርመን የሚኖረው ተስፋዬ በመጀመሪያው ዙር ርዳታ ጥሩ ተሞክሮ ስለነበረው በዚሁ መንገድ ሊገፋበት ይፈልጋል። « አምስት ሳንቲም ሳይጎል እቃው እዛው ሊደርስ ችሏል። አሁን ያገኘናቸው ደሴ ከተማ የሚገኙ ወጣቶችም ለመርዳት ይፈልጋሉ።  » ይህም ተስፋዬን ቀጥሎ ርዳታ ለማስተባበር አበረታታች ሆኖ አግኝቶታል።

Äthiopien I Kriegsvertriebene in Dessie
ምስል T. Abebe

ሙሉውን ዘገባ በድምፅ ያገኙታል።


ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ