1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንስት የፖለቲካ እስረኞች የታሰቡበት ዘመቻ

ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 3 2007

ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም ዙርያ ያሉ እንስት የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ ዘመቻ እያካሄደች ነው። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሳማንታ ፓዎር ይፋ በተደረገዉ በዚህ ዘመቻ ከተካተቱ 20 እንስቶች መካከል ሶስት ኢትዮጵያውያንና አንዲት ኤርትራዊት ይገኙበታል።

https://p.dw.com/p/1GTC4
Demonstration der Semayawi-Partei in Addis Ababa Äthiopien 22.09.2013
ምስል DW

[No title]

ነሐሴ 29፤ 30 እና ጳጉሜ አንድ 2007 ዓ.ም. ብሌን መስፍን፤ሜሮን አለማየሁና ንግስት ወንዲፍራው የታሰቡበት ቀን ነበር። ሶስቱን እንስቶች የዘከረው 20ዎቹን ፍቱ (#FreeThe20) የተሰኘው የአሜሪካን መንግስት አዲስ ዘመቻ ነው።

20ዎቹን ፍቱ (#FreeThe20) የተሰኘው ይህ ዘመቻ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሳማንታ ፓዎር ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ይፋ የተደረገ ነው። በዘመቻው የተካተቱት ብሌን መስፍን፤ሜሮን አለማየሁና ንግስት ወንዲፍራው የኢትዮጵያ መንግስት ሊቢያ ዉስጥ በግፍ የተገደሉ ኢትዮጵያዉያንን ለመዘከር የጠራዉን የአደባባይ ሠልፍ በማወክ ተከሰው በእስር ላይ ናቸው። «ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፤የመሰብሰብና የመደራጀት የሚባሉትን መሰረታዊ መብቶች ተግባራዊ በማድረጋቸው» መታሰራቸውን የሚናገሩት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ኢንጂኔር ይልቃል ጌትነት የፖለቲካ እስረኛ ናቸው ብለው ያምናሉ።

Demonstration in Addis Abeba 02.06.2013 Protest Slogan
ምስል DW/Y. G.Egziabher

ከ20 ዓመታት በፊት በቤጂንግ በተደረገ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ 189 የዓለም አገሮችና ከ30,000 በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የፆታ እኩልነትና የሴቶች መብትን ለማሳደግ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር። በጉባዔው የሴቶችን አቅም ለማሳደግና ሰብዓዊ መብታቸውን ለማስጠበቅ «የቤጂንግ አዋጅ» የተሰኘ የተግባር መመሪያ ይፋ አድርገዋል። መመሪያው ግን የፈየደው ነገር ያለ አይመስልም። የአሁኑ ዘመቻ የመጣው የዓለም አገራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጽ/ቤት መስከረም 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሊመክሩ በተዘጋጁበት ወቅት ነው።

20ዎቹን ፍቱ የተሰኘው ዘመቻ ከሶስቱ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ኤርትራዊቷን አስቴር ዮሐንስና ግብፃዊቷን ሳና ሳዒፍ ከአፍሪቃ ጨምሯል። በየቀኑ አንድ የፖለቲካ እስረኛን የሚዘክረው ዘመቻ የመስከረም ወርን በሙሉ የሚካሄድ ይሆናል።

ሃሳብን በነፃነት ለመግለፅ ባሳየችው ልዩ ቁርጠኝነት ትግልና ፅናት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት ሽልማትን ያገኘችው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ በሽብርተኝነት ክስ ለአምስት ዓመታት በእስር ቤት ቆይታለች። ለርዕዮት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለእንስቶች ፈታኝ ነው።

«በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ በአባልነትም ይሁን በመሪነት ለመሳተፍ የሚሞክሩ ሴቶች ከብርቱካን ሚደቅሳ ጀምሮ እየደረሰባቸውን ነገር እያየን ነው።» የምትለው ርዕዮት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምህዳር «በፍጹም የሚያበረታታ አይነት ሁኔታ የለም።» ስትል ትናገራለች። ደፍረው በፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍም ይሁን በጋዜጠኝነት መንግስትን የተቹ እንስቶች ለእስር መዳረጋቸው ሙከራውን ከባድ አድርጎታል ትላለች።

Demonstration der Semayawi-Partei in Addis Ababa Äthiopien 22.09.2013
ምስል DW

በአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚተዳደር የዘመቻው ድረ-ገጽ ብሌን፤ ሜሮንና ንግስት «ለዴሞክራሲ መርሆዎች በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የሰማያዊ ፓርቲ ቀዳሚ አባላት ነበሩ።» ሲል ገልጿቸዋል። ሶስቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ለእስር ሲዳረጉ የመጀመሪያቸው አይደለም ያሉት ኢንጂኔር ይልቃል ጌትነት የእስር ውሳኔውን አጥብቀው ያጠይቃሉ። «ሴቶችን በማንቃታቸው፤ወጣት በመሆናቸው፤በህገ-መንግስቱ መሰረታዊ መብቶች እንዲከበሩ በጥብቅ የሚከራከሩና የሚሟገቱ» ያሏቿውን ሶስቱን እንስቶች እውነተኛ የኢትዮጵያ ሴት ልጆች ሲሉ ይገልጿቸዋል።

በዘመቻው የተመረጡት 20 እንስቶች በመላው ዓለም ከታሰሩት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው ያሉት አምባሳደር ሳማንታ «የሴቶችን አቅም ማጎልበት ከፈለጋችሁ በአመለካከታቸውና በሚታገሉላቸው መብቶች አትሰሯቸው። ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የአምስት ዓመታት የእስር ጊዜዋን ጨርሳ የተፈታችው ርዕዮት ዓለሙ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች ተሳትፎ መገደብ አሉታዊ ጫና እንዳለው ትናገራለች።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ