1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንወያይ፦ ጦርነቱና በጦርነቱ ማግስት

እሑድ፣ ኅዳር 20 2013

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የመቀሌ ከተማን ቅዳሜ፣ ኅዳር 19 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩ ተገልጧል። ትግራይ ውስጥ የሚደረገውን ውጊያ ተከትሎ በኢትዮጵያ ውስጣዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊ ሒደቶች ምን መልክ ሊይዙ ይችላሉ? ዋነኛ ተግዳሮቶቹስ ምንድን ናቸው? የእንወያይ መሰናዶ።

https://p.dw.com/p/3lyD0
Tigray-Konflikt | Militär Äthiopien
ምስል Ethiopian News Agency/AP/picture alliance

«ወሳኙ ጦርነት አልቋል።»

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የመቀሌ ከተማን ቅዳሜ፣ ኅዳር 19 ቀን፣ 2013 ዓ.ም እንደተቆጣጠረ ተገልጧል። «ሕግ የማስከበር ዘመቻ የመጨረሻው ምዕራፍ» በተባለው የቅዳሜ ዕለቱ ውጊያ ንጹሐን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞች እና ቅርሶች ሳይጎዱ መቀሌ መግባት እንደተቻለ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታራቸው ይፋ አድርገዋል። የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላም የመከላከያ ሠራዊት መቐለን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን በትናንቱ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ዐስታውቀዋል። ቀሪው ሒደት «ጦርነቱ ከአሁን በኋላ የሚሆነው በፖሊስ እና የተበታተነ፣ በየጎሬው የተደበቀ ኃይል የመለቃቀም እና ወደ ሕግ የማቅረብ ነገር ነው የሚሆነው። በወሳኝ መልኩ ጦርነቱ ቆሟል። የወያኔ አመራር በመደምሰሱ ምክንያት፣ የመጨረሻ ምሽጉ በመደርመሱ ምክንያት፤ የመከላከያ ሠራዊታችን እጅ በመግባቱ ምክንያት ወሳኙ ጦርነት አልቋል» ሲሉም ገልጠዋል። 

የእለተ እሁድ ሳምንታዊ  የእንወያይ መሰናዶ በውጊያው ወቅት ስለተከሰቱ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች፤ ስለ ጦርነቱ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እይታ እና ከጦርነቱ በኋላ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ያወሳል። 

Äthiopien Tigray | Hauptstadt Mekele
ምስል imago images/GFC Collection

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኃይላት ባደረጓቸው ውጊያዎች እስካሁን በውል ባይታወቅም በርካታ ሰዎች መገደላቸው እና በሺህዎች የሚቆጠሩት መፈናቀላቸው ተዘግቧል። ከዐርባ ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ሱዳን መሰደዳቸውንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ዐስታውቋል።

ማይ ካድራ በተባለው ከተማ እና አካባቢ ከስድስት መቶ በላይ በአብዛኛው የአማራ ተወላጅ የኾኑ ሰላማዊ ሰዎች «ሳምሪን» በሚል ስም በተደራጁ የትግራይ ወጣቶች በግፍ ሲጨፈጭፉ በአካባቢዉ የሠፈረዉ የትግራይ የሚሊሺያና የፖሊስ ኃይል ከጨፍጫፊዎቹ ጋር ተባባሪ እንደነበር የኢዮጵያ የሠብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሠመኮ) በመግለጫው ዐሳውቋል።

ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች የምርመራ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ማካኼዱንም ገልጧል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በማይካድራው የተፈጸመውን አሰቃቂ እልቂት አውግዟል። ሌሎች ሰብአዊ መብት ጥሰቶችም በገለልተኛ ወገን እንዲጣሩ ጥሪ አድርጓል።

Tigray-Konflikt | Militär Äthiopien
ምስል Ethiopian News Agency/AP/picture alliance

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግጭቱ እንዲረግብ እና ውይይት እንዲካኼድ ጠይቋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ  ባለሥልጣናት፦ «ሕግን ማስከበር» ስላሉት የትግራይ «ዘመቻ» ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብን ለማስረዳት በውጭ ሃገራት ጉዞ አድርገዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በትግራይ ስላለው ኹኔታ በዝግ ስብሰባ ተወያይቶ ያለ ስምምነት መበተኑ ተዘግቧል።

የትግራይ ዘመቻን ተከትሎ በኢትዮጵያ ውስጣዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊ ሒደቶች ምን መልክ ሊይዙ ይችላሉ? ዋነኛ ተግዳሮቶቹስ ምንድን ናቸው? የዛሬው እንወያይ መሰናዶ ዋነኛ ማጠንጠኛ ነው።  በውይይቱ እንዲሳተፉ ሦስት እንግዶችን ጋብዘናል። 

ማስታወሻ፦ ውይይቱ የተደረገው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የመቀሌ ከተማን ቅዳሜ፣ ኅዳር 19 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን ከመግለጹ አንድ ቀን ቀደም ብሎ፤ ዐርብ እለት ነው። 

ሙሉ ውይይቱን የድምፅ ማገናኛውን በመጫን ማድመጥ ይቻላል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ