እንግጫ ፣ የአዲስ አመት ማብሰሪያ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:50
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:50 ደቂቃ
14.09.2017

«እንግጫ»የአዲስ አመት ማብሰሪያ

በኢትዮጵያ አዲስ አመት ሲመጣ በርካታ ባህላዊ ክዋኔወች ይካሄዳሉ። ከነዚህ መካከል በአዲስ አመት ዋዜማ በልጃገረዶች የሚከናወነው የእንግጫ ነቀላ አንዱ ነዉ።ይህ በዓል ባለፈዉ ጳጉሜ 4 ቀን በደብረ ማርቆስ ከተማ በአደባባይ ተከብሯል።

የሰዉ ልጅ ሰዓታትን ቀናትንና አመታትን ከፋፍሎ እንደ የእምነቱ፣ባህሉና የስልጣኔ ደረጃዉ የየራሱን የቀን መቁጠሪያ  አዘጋጅቶ ይጠቀማል። ከነዚህም ዉስጥ የአይሁድ፣የክርስትና፣የሂጅራ፣የቻይና፣የፋርስና ሌሎችም የዘመን መቁጠሪያወች ይጠቀሳሉ። ሀገራችን  ኢትዮጵያም የራሳቸዉ የዘመን መቁጠሪያ ካላቸዉ ሀገሮች አንዷ ናት። የዘመን መቁጠሪያ  ብቻም ሳይሆን የዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ የሚካሄዱ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔወች ባለቤትም ነች። ክረምት አልፎ አዲስ ዘመንና አመት በተለወጠ ቁጥር የአዲሱን አመት መዳረሻና መባቻ  የሚያመላክቱ የተለያዩ ባህላዊ አካባበሮች በተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ይካሄዳሉ።ከአሮጌዉ አመት የመጨረሻ ወር ከነሐሴ ጀምሮ፤ የአዲሱ አመት መጀመሪያ  እስከ ከሆነዉ እስከ ወርሃ መስከረም ድረስ  በወጣት ልጃገረዶች እና ወንዶች የሚዘወተሩት በአደይ አበባና በለምለም ሳር የሚታጀቡት  የቡሄ፣የሆያሆዬ፣የአበባአየሽ ወይ፣የአሸንዳ፣የሶለል፣ የሻደይና የእንግጫ  በዓላት ከባህላዊ ስርዓቶቹ ዉስጥ ይጠቀሳሉ። የፍቼ ጨምበላላና የኤሬቻም  አዲስ  አመት መምጣቱን የሚያበስሩ በዓላት  ናቸዉ።
     
እንግጫ የሳር አይነት ነዉ። የእንግጫ ነቀላ በዓል ደግሞ ዘመን ሲለወጥ  የሚከወን ባህላዊ ስራት ነዉ።በአዲስ አመት ዋዜማ ልጃገረዶች  ወንዝ ወርደዉ እንግጫ ይቆርጣሉ። በዚያዉ ቀን ማምሻ  የቆረጡትን እንግጫ ይጎነጉኑታል።ሲነጋ ሊጃገረዶቹ ከያሉበት ተጠራርተዉ በመሰባሰብ  በየሰዉ ቤት እየዞሩ የተጎነጎነዉን እንግጫ የቤቱ ምሰሶ ላይ በማሰር አዲሱን አመት ያበስራሉ። ይህ ባህላዊ ክዋኔ በዜማና በጭፈራ የታጀበ ነዉ።ይህ የልጃገረዶች በዓል በሰሜን ሸዋ፣ በምስራቅ ና ምራብ ጎጃም እንዲሁም በሌሎች ቦታወች  ይከወን የነበረ ቢሆንም እየደበዘዘና በከተሞች አከባቢም እየጠፋ በመሄድ ላይ እንዳለ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የማይዳሰሱ ቅርሶችን በተመለከተ ባሳተመዉ መድብል ላይ ተገልጿል።

Young Flower Adey Abeba Blumen Äthiopienከማይዳሰሱ ቅርሶች ዉስጥ የሚመደበዉ ይህ የልጃገረዶች ጨዋታ እየደበዘዘ  የመጣ ቢሆንም  አሁን አሁን እንደ  አሸንዳና ኢሬቻን  የመሳሰሉ በዓላት ፈረንጆቹ የጎዳና ላይ ፌሽታ በሚሉት መልኩ በአደባባይ መከበር መጀመራቸዉ ባህሉን ጠብቆ ለትዉልድ ለማስተላለፍ መነቃቃትን የፈጠረ ይመስላል።
በመሆኑም ይህ በዓል በምስራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም አዘጋጅነት የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ  በሚል በደብረማርቆስ ከተማ በንጉስ ተክለሀይማኖት አደባባይ  በያዝነዉ አዲስ አመት ዋዜማ  ከጳጉሜ 3 እስከ 4 ለመጀመሪያ ጊዜ ተከብሯል። ከምስራቅ ጎጃም ዞን ባህልና  ቱርዝም  መምሪያ ባገኘነዉ መረጃ መሰረት የበአሉ ድባብ ነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ነዉ።በሀገሬዉ አጠራር «ደቦት» ወይም ችቦ ለማዘጋጀት የሚያገለግል ኮሸሽላ የተባለ እንጨት በመሰበሰብ ይጀምራል ።ጠመናይና ቀበርቾ የተባሉ ቤት ዉስጥ ቤት ውስጥ የሚጨሱ ስራስሮችን ጨምሮ ነሀሴ 16 ቀን የሚጎዘጎዝ  «ከሴ»የተባለ ጥሩ መዓዛ ያለዉ ተክል ከአደይ አበባ ጋር ተደባልቆ ይታጨዳል።ይህም አዲሱን ዘመን በጥሩ ስሜት ለመቀበል የሚከወን ነዉ።በአሉ በዚህ ሁኔታ ይቀጥልና የአዲስ አመት ዋዜማ ላይ የእንግጫ ነቀላ በዓል ይከናወናል።የበዓሉ መከበር ትዉፊቱን ወደ ትዉልድ ለማስተላልፍ ይረዳል ይላሉ የምስራቅ ጎጃም ዞን ባህልና  ቱርዝም መምሪያ  ወ/ሮ ዉዳለም አልማዉ።

Young Flower Adey Abeba Blumen Äthiopien


የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪ የሆነዉ ወጣት አቤል ብርሃኑ እንዳጫወተን ይህ የዘመን መለዋጫ በዓል በአደባባይ ከመከበሩ በፊት ባህሉን ከኪነጥበብ ጋር በማስተሳሰር  በትያትር መልክ አዘጋጅቶ በትንሹም ቢሆን በደብረ ማርቆስ ከተማ ለታዳሚዎች አቅርቦት ነበር።የበአሉን አከባበር ከነዜማዉ ልቅም አድርጎ አጥንቶታል።  በእለቱ ከሚዜሙት መካከልም ጥቂቶቹን ስንኞች ነግሮናል።

የቅዱስ ዮሀንስ ያልዘፈነች ቆንጆ

ቆማ ትቀራለች እንደ ሰፈር ጎጆ

እቴ አደይ አበባ ነሽ

ዉብ ነሽ ዉብ ነሽ

ይህንን ዜማ ልጃገረዶች እንግጫዉን እየነቀሉ ያዜማሉ።ይህንን ዜማ ሲሰሙ የአካባቢዉ ጎረምሶች ወደ ልጃገረዶቹ ይመጣሉ።ይህኔ ታዲያ ዜማዉ ይቀየራል።

እንግጫችን ደነፋ

ጋሻዉን ደፋ

እንግጫዬ ነሽ ወይ

Young Flower Adey Abeba Blumen Äthiopien

እሰይ እሰይ

የቅዱስ ዮሀንስ የመስቀል የመስቀል

የላክልኝ ድሪ ሰላላ መላላ

መልሰህ ዉሰደዉ ጉዳይም አይሞላ

ይህንን ዜማ ሲሰማ ለወደዳት ልጃገረድ ማተብ ያስርላታል።

የከሴ አጨዳና የእንግጫ ነቀላ በዓል በዋናነት የልጃገረዶች በዓል ቢሆንም አመሻሽ ላይ በልጆችና በልጃገረዶች የተነቀለዉ እንግጫ እየተጎነጎነ ጣራ ላይ ያድርና ጠዋት ላይ በዘመን መለወጫ እለት ለበረከትና ለረድዔት በሚል ራስ ላይ  ፣የሊጥ እቃ ላይና ሌማት ላይ ይታሰራል።የተጎነጎነዉ እንግጫም እስከ መስቀል በዓል ድረስ ይቆይና ከደመራ ጋር ይቃጠላል።አመዱንም ከህፃን እስከ አዋቂ ይቀባዋል።ይህ ለጤንነት ሲባል በማህበረሰቡ የሚከወን ነዉ።ወጣት አቤል ብርሃኑ ባደገበት በምስራቅ ጎጃም  አካባቢ የእንግጫ ነቀላ  የመተጫጫና የፍቅር ተጓዳኝ የመፈለጊያ በዓል ጭምር  ነዉ። የፍቅር መግለጫ ስንኞችም አሉ።

አበባዉ ያብባል በየሁሉ ደጅ

ምነዉ እኔ የለኝ የከንፈር ወዳጅ

አንት የከንፈር ወዳጅ በጊዜ ሳመኝ

ጤፍ አበጥራለሁ የሰዉ ግዙ ነኝ

የሰዉ ግዙ ሆኖ የሰዉ ግዙ መዉደድ

እሳት በገለባ እፍ ብሎ ማንደድ ።  

በኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛጘኝ አበራ እንደገለፁት በማህበረሰቡ ዘንድ ተረስተዉ የነበሩ ባህላዊ  እሴቶቻችን እየወጡ በአደባባይ መከበር መጀመራቸዉ ከትዉልድ ወደ ትዉልድ ከማሸጋገር ባለፈ ለቱሪስት መስህብነትም የላቀ  ጠቀሜታ አለቸዉ።

ፀሐይ ጫኔ 

ሂሩት መለሰ

ተዛማጅ ዘገባዎች