1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦባማ የሰላም ኖቤል ተሸለሙ

ዓርብ፣ መስከረም 29 2002

ፅናት፥ ሥልት፥ ትዕግስት፥ አንደበተ ትሩትዕነታቸዉ ቀለም፥እምነት፥ የፖለቲካ መርሕ፥ ሐገር- የሚጋራቸዉን አይደለም የአለም ሕዝብ በተለይ የወጣቱን ቀለብ የማይስቡበት ምክንያት በርግጥ አልነበረም።ባራክ ኦባማ ይቻላል።

https://p.dw.com/p/K38V
ምስል AP

09 10 09

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የዘንድሮዉን የአለም ታላቅ የሠላም ሽልማትን ኖቤል ተሸለሙ።የኖርዌዉ ሸላሚ ኮሚቴ ዛሬ ማርፈጃ ላይ እንዳስታወቀዉ ኦባማ ለታላቁ ሽልማት የበቁት አለም አቀፍ ዲፕሎማሲን ለማጠናከርና በሕዝቦች መካካል ትብብርን ለማስረፅ ልዩ ጥረት በማደርጋቸዉ ነዉ።ኦባማ የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን ከያዙ ገና ስምንተኛ ወራቸዉ ነዉ።የሸላሚዉ ኮሚቴ እንደሚለዉ ግን የኦባማን ያክል ያአለምን ትኩረት የሳበ፥ ለሕዝቡ መልካም ተስፋ የሰጠ ግለሰብ ብዙም የለም።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝሩን አጠናቅሮታል።

«አባቴ የዉጪ ተማሪ ነበር።ኬንያ ዉስጥ አንዲት ትንሽ መንደር ተወልዶ-ያደገ ነበር።ፍየል እየጠበቀ ነዉ-ያደገዉ።ከደሳሳ የቆርቆሮ ቤት ነዉ የተማረዉ።አባቱ፥ የኔ አያት ወጥ ቤት ነበር።የብሪታንያዎች አገልጋይ።»

ከአያት፥ አባታቸዉ የወረሱት ዘር-ቀለም፥እምነት-እስከ ሐቻምና ያለሙትን-እዉንነት፥ ሐቻምና ያሉትን ገቢራዊነት ያነቅፈዋል-ነበር-የእስከአምናዉ-የብዙዎች እምነት።አላማ-ቃላቸዉ ግን በጠንካራይቱ ሐገር ጠንካራ መሠረት ነበረዉ።አለዉም።

«ለዘብተኛ አሜሪካ የለም።ወግ አጥባቂ አሜሪካ የለም።የተባበሩት የአሜሪካ መንግሥታት ነዉ

ያለዉ።ጥቁር አሜሪካ የለም።ነጭ አሜሪካ የለም።የላቲኖ-አሜሪካ የለም።የእስያ አሜሪካ የለም።ያለዉ የተባባበሩት አሜሪካ ነዉ።»

ከሚሹት ለመድረስ ገና ከጅምሩ የማንዴላን ሥልት፥ፅናት- ምርኩዝ-አብነታቸዉ አድርገዉ ፥ ፖለቲካዉን እንደ ኬኔዲ፥ የዘር-ቀለም እኩልነት ትግሉን እንደ ኪንግ ይዘዉሩት ገቡ።አበክረዉ የሚታገሉለትን፥ እምነት አላማ ከሕዝብ ለማስረፅ-የአንጣዎቻቸዉን ሴራ፥ ስድብ፥ ዛቻ ዘለፋ-ትችትን በጣጥሰዉ ለማለፍ ብዙዎች የማይችሉትን መቻል-መታገስ ነበረባቸዉ።

ፅናት፥ ሥልት፥ ትዕግስት፥ አንደበተ ትሩትዕነታቸዉ ቀለም፥እምነት፥ የፖለቲካ መርሕ፥ ሐገር- የሚጋራቸዉን አይደለም የአለም ሕዝብ በተለይ የወጣቱን ቀለብ የማይስቡበት ምክንያት በርግጥ አልነበረም።ባራክ ኦባማ ይቻላል።

«ዝግጁ እንዳልነበረን ይነገረን ነበር።ወይም መሞከር እንደማይገባን፥ ወይም እንደማንችል ሲነገረን ለዘመናት የነበሩት የአሜሪካ ትዉልዶች ምላሻቸዉ የሕዝቡን መንፈስ ባንድ የሚጠቀልል-ነበር።አዎ እንችላለን።አዎ እንችላለን።---»

ጥቁር-ነጭ፥ ቢጫ-ክልስ፥ ለዘብተኛ ወግ አጥባቂ ወንጀለኛ ሕግ አስከባሪ፥ አጭበርባሪ ፍትሐዊ ሁሉን አሰባጥራ የያዘችዉ-ግን ለዘመናት ያንድ ዘር-የበላይነት የነገሰባት-ሐገር ፕሬዝዳት ሆኑ።ቻሉበት።እንደ ታላቂቱ ሐገር ታላቅ መሪ ለአለም ያስተላለፉት የመጀመሪያ ጥሪ-መልዕክታቸዉ ደግሞ የአለም ሰላም ነበር።

«ዛሬ ይሕንን የምትመለከቱ፥ ከትላልቆቹ ርዕሠ-ከተሞች አባቴ እስከተወለደባት ትንሽ መንደር ያላችሁ የሌሎች ሐገራት ሕዝብና መንግሥታት በሙሉ፥-አሜሪካ የያንዳዱ የሰላም ወዳድ ሐገር፥ የሰላም ወዳድ ወንድ፥ ሴት፥ ሕፃናት በሙሉ፥ ወዳጅ መሆንዋን እወቁ።አሁንም ለመምራት ዝግጁ መሆናችንን ተረዱ።»

ኢራቅ የሰፈረዉ ጦር ቀስ በቀስ ለማስወጣት መወሰናቸዉ። የኹዋንታናሞ ማጎሪያ ጣቢያን መዝጋታቸዉ።እስራኤልና ፍልስጤምን ለማደራደር መቁረጣቸዉ።ምሥራቅ አዉሮጳ ሊተከል የታቀደዉን የሚሳዬል ጣቢያ መሠረዛቸዉ፥ ሌላም ታክሎበት ለሰላም የመቆማቸዉን ጅምር መሠከረ።

ከኢራን ጋር በቀጥታ ለመደራደር-መስማማታቸዉ፥ የአለም የኑክሌር ጦር መሳሪያን ለመቀነስ ከሩሲያ ጋር መስማማታቸዉ፥የተፈጥሮ ሐብትን ለማስጠበቅ፥ የገንዘብ ኪሳራን ለማስወገድ ከሌሎች ጋር የጋራ አቋም መያዛቸዉ፥ ዉዝግብ ልዩነትን በዲፕሎማሲ ለማስወገድ መቁረጣቸዉን ለኖርዌዉ ሸላሚ ኮሚቴ አረጋገጠ።

Nobelpreis Alfred Nobel
አልፍሬድ ኖቤልምስል AP

«የኖርዌ የኖቤል ኮሚቴ፥-ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ አለም አቀፍ ዲፕሎማሲያን እና የሕዝቦችን ትብብር ለማጠናከር ላበረከቱት አቻ የማይገኝለት ጥረት የ2009ኙን ኖቤል ሽልሟቸዋል።ኦባማ አለም ከኑክሌር ጦር መሳሪያ እንድትፀዳ ለያዙት አለማ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።»

ኖቤልንም ቻሉበት።-ዛሬ።

ነጋሽ መሐመድ፣

ተክሌ የኋላ፣