1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኧልሸባብ የምሥራቅ አፍሪቃ ስጋት

ረቡዕ፣ መስከረም 15 2006

ኧልሸባብ የተሰኘው የሶማሊያ ፅንፈኛ ቡድን ቅዳሜ፣ መስከረም 11 ቀን 2006 ዓም ኬንያ መዲና ናይሮቢ በሚገኝ አንድ ሰፊ የገበያ አዳራሽ ውስጥ በከፈተው ድንገተኛ ጥቃት ቢያንስ 72 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። በገበያ አዳራሹ የነበረው የእገታ ርምጃ ከአራት ቀናት ቆይታ በኋላ መጠናቀን ታውቋል። ለመሆኑየኧልሸባብ ማንነት እና አነሳስ ምን ይመስላል?

https://p.dw.com/p/19oYJ
የኬንያ የፀጥታ ኃይላት
የኬንያ የፀጥታ ኃይላትምስል CARL DE SOUZA/AFP/Getty Images
ኧልሸባብ የእገታ ተግባር የፈፀመበት ሕንፃ
ኧልሸባብ የእገታ ተግባር የፈፀመበት ሕንፃምስል picture-alliance/AP

ፅንፈኛ እንደሆነ እና ከኧል ቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይነገርለታል፤ የሶማሊያው ታጣቂ ቡድን ኧልሸባብ። ይህ ፅንፈኛ ቡድን በተለይ ባሳለፍነው ቅዳሜ ኬንያ መዲና ናይሮቢ ውስጥ ያደረሰው አሰቃቂ የሽብር ጥቃት የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። ጥብቅ የሸሪዓ ሕግ በመላ ሶማሊያ ለመዘርጋት ከሚታገለው የኧልሸባብ አንዱ ክፍል አንስቶ ቡድኑ የተለያዩ ገጽታዎች እና የትግል ስልቶች አሉት። ዶ/ር መሀሪ ተድላ የፀጥታ ጥበቃ ጥናት ተቋም ባልደረባ ናቸው። የኧል ሸባብ ሌላኛው ገጽታ ምን እንደሚመስል እንዲህ ይገልፃሉ።

« ሕግና ስርዓት እንዲከበር፣ ሠላምና ፀጥታ እንዲሰፍን በማድረጉ ረገድ በወቅቱ የነበረው ብቸኛው ኃይል ኧልሸባብ በመሆኑ ቡድኑን የተቀላቀሉት ፅንፈኛ ያልሆኑት ሌሎች የኧልሸባብ ክፍሎች ወይንም ተከታዮች ጥለው ወጥተዋል። ስለእዚህ የተቀረው ክፍል በከፍተኛ ሁናቴ ዓለማቀፋዊ ከመሆኑም ባሻገር የመንግሥት አስተዳደርን በተመለከተ የሚከተለው ርዕዮተ-ዓለም የተቃኘውም ሆነ መመሪያ የሚቀበለው ከኧልቃይዳ ነው። »

የኧልሸባብ አነሳስ በሶማሊያ። ከሁለት ዓስርት ዓመት አንስቶ የእርስ በእርስ ጦርነት ባልተለያት ሶማሊያ እጎ አ በ2006 «በሶማሊያ የሸሪአ ፍርድ ቤቶች ህብረት» የተሰኘው ቡድን የሀገሪቱ ዋና ከተማ ሞቃዲሾን ይቆጣጠራል። መዲናዋን ብቻም አይደለም የመንግሥት አስተዳደሩንም በመያዝ ይህ አክራሪ ቡድን በመላ ሶማሊያ የሸሪዓ ሕግ መዘርጋቱን ያውጃል። ከሶማሊያ የሸሪአ ፍርድ ቤቶች ህብረት ውስጥ አንድ ጽንፈኛ ቡድንም የኢትዮጵያ አካል የሆነውን የኦጋዴን ክፍል እንደሚወር ይዝታል። ብዙም ሳይቆይ የኢትዮጵያ ጦር በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ እየተደረገለት ወደ ሶማሊያ ድንበር ይዘልቃል።

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከ18 ዓመታት ቀደም ብሎ በተመድ ጥላ ስር በመሆን ሶማሊያ መግባቱን እንደጣልቃ ገብነት ይመለከቱ የነበሩ ሶማሊያውያን የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ መዝለቅን ሁለተኛ ወረራ ሲሉ እንዲመለከቱት አድርጓል። በእዚህ መሀከል ነበር ኧል ሸባብ የተሰኘው አክራሪ ቡድን ተጠናክሮ ሊወጣ የቻለው። በጀርመኑ ማክስ ፕላንክ ተቋም ውስጥ ስለ ሶማሊያ ለ12 ዓመታት ያጠኑት ማርኩስ ሆህነ።


«በሶማሊያ ሽብርን የመዋጋቱ ተግባር በመሠረቱ ሽብርን አስፋፍቷል። በእርግጥ ስር የሰደደው ቀደም ብሎ ነው። በአሜሪካኖች አለያም በኢትዮጵያኖች የተተከለ አይደለም። ሆኖም እነዚህ አነስተኛ፣ ፅንፈኛ ቡድኖች ማቆጥቆጥ የመጀመራቸው ነገር በሶማሊያ አቅጣጫውን ከሳተው ሽብርን የመዋጋት ተግባር ጋር ይያያዛል። »

ኧልሸባብ በሶማሊያ የነበረውን ጠንካራ ይዞታ ያጣው እጎአ በ2011 ነው። በወቅቱ በሶማሊያ የአፍሪቃ ኅብረት ሠላም አስከባሪ ጓድን በመቀላቀል ኬንያ ጦሯን ሶማሊያ አዝምታ ነበር። እናም ያን ተከትሎ ኧል ሸባብ በኬንያ ምድር የበቀል ርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ዝቶ እንደነበር ይታወሳል።

ኧል ሸባብ ከሶሥት ዓመታት በፊት ኡጋንዳ ውስጥ የሽብር ጥቃት ፈፅሞ ቢያንስ 76 ሰዎችን መግደሉ ይታወሳል። ልክ እንደኬንያ ሁሉ ዩጋንዳም ጦሯን ወደ ሶማሊያ መላኳ ይታወቃል። ኧልሸባብ ቀደም ሲል የሰነዘረውን ዛቻ በኬንያ ምድር ተግባራዊ አድርጎ በርካታ ሠላማዊ ሰዎችን ገድሏል። የተለያዩ የዜና ምንጮች የሟቾቹ ቁጥር ቢያንስ 72 ነው ሲሉ እየዘገቡ ነው።

ኧልሸባብ የተሰኘው የሶማሊያ ፅንፈኛ ቡድን አሁንም ድረስ በተለይ በደቡባዊ ሶማሊያ አንዳንድ ክፍሎች በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

የኧልሸባብ ጥቃት በኬንያ መዲና ናይሮቢ
የኧልሸባብ ጥቃት በኬንያ መዲና ናይሮቢምስል TONY KARUMBA/AFP/Getty Images


ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ