1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሜድትራኒያን ሞት ፊት የቆሙት ስደተኞች

ማክሰኞ፣ የካቲት 17 2007

ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ አመት የሜድትራኒያን ባህርን በጀልባ ለማቋረጥ ከሞከሩ 218,000 ሰዎች መካከል 3,500 መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን አስታውቋል። በዚህ በተመሳሳይ መንገድ ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ በመጨመር ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/1EghI
Italien Flüchtlingsdrama Lampedusa Flüchtlingsboot
ምስል picture-alliance/ROPI

ሰለሞን መንግስቴ በሊቢያዋ የቤንጋዚ ከተማ ባለቤቶቹ ጥለውት የሄዱትን ቤት ይንከባከባል።አትክልት ይኮተኩታል። ግቢውን ያጸዳል። ሰለሞን በቤንጋዚ ብቻውን አይደለም። ባለቤቱ የዝና እዘዘው ቀን ቀን ከሰው ቤት ትሰራለች። ሰለሞን ስለ ወርሃዊ ደሞዙ ሲጠየቅ ፈገግ እያለ «በእውነት መቼ እንደሚከፍሉኝም አላወኩም።» ሲል ይመልሳል።

ሰለሞን ተወልዶ ካደገበት የጎንደር አካባቢ ወደ ሱዳን ገዳሪፍ የተጓዘው ለደላሎች አምስት ሺ የኢትዮጵያ ብር ከፍሎ በአስቸጋሪ የሌሊት ጉዞ ነበር። ጉዞውን ያመቻቹለት የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህገ-ወጥ ደላሎች ነበሩ። «ጉዞው የሚጀመረው ለሊት ሰው በሌለበት ሰዓት በእግር ነው። የሚለው ሰለሞን መንገዱ ከሶስት እስከ ሰባት ቀናት ሊወስድ እንደሚችል ይናገራል። ከገዳሪፍ በኋላ በመኪና የሚደረገው ጉዞ «ሰው በሰው ላይ ጭነው ስለተጓዝን በእግር ከተደረገው የበለጠ ያስከፋል።»ሲል ያስታውሳል።

በተመሳሳይ መንገድ ከኢትዮጵያ ከወጣችው ከባለቤቱ የዝና እዘዘው ጋር የተዋወቁት በሱዳን በቤተ-ክርስቲያን ነበር። ሁለቱ ስደተኛ ወጣቶች መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ሶስት ጉልቻ መሰረቱ። ከ2003-2006 ዓ.ም. የዝና በሰው ቤት ሰለሞን ተመላላሽ ስራ እየሰሩ ቢቆዩም ሃገሩ አልተመቻቸውም። እንደገና ሌላ መንገድ-ሌላ ጉዞ አሁንም በህገ-ወጥ መንገድ

ከሱዳን ወደ ሊቢያ ለመጓዝ ለህገ-ወጥ ደላሎች በነፍስ ወከፍ ስድስት ሺ በአጠቃላይ አስራ ሁለት ሺ የሱዳን ፓውንድ ከፍለዋል። ሰለሞን ከባለቤቱ ጋር ከሱዳን ተነስተው የሰሐራ በርሃን ሲቋርጡ ጉዞውን ያመቻቹትን ሰዎች «አይን ያወጡ ደላሎች » ሲል ይገልጻቸዋል። 9.4 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሰፋውን የሐራ በርሃ ማቋረጥ ለጥንዶቹ መራር ነበር። «አንዲት ዛፍ ለውርርድ የማታይበት» ይለዋል ሰለሞን የሰሐራ በርሃን። የዝና እዘዘው ከሱዳን ወደ ሊቢያ ላደረጉት ጉዞ ዋንኛ ምክንያታቸው «ዞሬ ወደ አገሬ ብመለስ ምን ይዤ ልመለስ? » የሚለው ጥያቄ ትልቅ ቦታ እንደነበረው ታስታውሳለች። ስምንት ቀናት የፈጀውን ጉዞ ስታስታውስ ሲቃ ይተናነቃታል። ከበርሐው ንዳድ እና ውሃ ጥም ባሻገር ከውስጧ ሃዘን የቀበረ ትዝታ አላት። « ስንት እህቶቻችንን በበርሐ ጥለናቸው መጥተናል። እህቴ ወንድሜ አትልም። እህቴ ተኝታ ብትቀር አትቀሰቅስም።» ስትል ስለተሻገረችው የበርሐ ሞት ትናገራለች። ከሱዳን ወደ ሊቢያ በነበረው ጉዞ ስደተኞችን ከጫኑ ሶስት መኪኖች መካከል አንዱ ተገልብጦ ብዙዎች ማለቃቸውን ሰለሞን ያስታውሳል።

Elendsflüchtlinge aus Afrika
ምስል picture-alliance/dpa/dpaweb

ሰለሞን እና እዝና የሰሐራ በርሃን አቋርጠው ሊቢያ ሲገቡ ከለበሱት ልብስ በቀር በእጃቸው አንዳች ነገር አልነበረም። ውስን ምግብ፤አልባሳት እና የግል ንበረቶች የያዙባቸው ሻንጣዎች መንገድ መቅረታቸውን እዝና ተናግራለች። እናም ሁለቱ ወጣት ጥንዶች ሊቢያ ሲደርሱ ፓስፖርትም ይሁን የጉዞ ሰነድ በእጃቸው አልነበረም።

የሊቢያ ሁለተኛ ከተማ የሆነችው ቤንጋዚ እንደ ቀድሞ ሰላም እና መረጋጋት ርቋታል። ነዋሪዎቿ የመኖሪያ ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል።ሰለሞን እና የዝና በቤንጋዚ የበረከተው የጥይት ተኩስ እና ሞት ስጋት ፈጥሮባቸዋል። እናም ሜድትራኒያን ባህርን ተሻግረው አውሮጳ ሊገቡ ቆርጠዋል።ሰለሞን «አሁን ካለንበት ቢንጋዚ የእቃ መርከብ ይመጣል ይባላል። ግን አይገኝም። እሱ 1,500 ዶላር ነው። ከደላላው ጋር ተነጋግረናል። በመጣ ጊዜ እነግራችኋለሁ ብሎናል።» ሲል የመጀመሪያ አማራጫቸውን ያስረዳል። ሁለተኛ አማራጫቸው አሁን ካሉበት ቤንጋዚ ከሊቢያዋ ዋና ከተማ 50 ኪ.ሜ. ወደ ምትርቀው ጋሪቡሊ መጓዝ ይኖርባቸዋል።«ከጋሪቡሊ ትልቅ የሚባለው እስከ 1,500 ዶላር የሚከፈልበት ነው። መካከለኛ የሚባለው ከ900-1100 ዶላር የሚከፈልበት ሲሆን አነስተኛ የሚባለው እና ብዙ ጊዜ አደጋ ደረሰባት የሚባለው ጀልባ ጉዞ ሰባት መቶ እና ስምንት መቶ ዶላር ያስከፍላሉ።» የሚለው ሰለሞን ጉዞው አስራ ስምንት ሰዓታት እንደሚወስድም መረዳታቸውን ተናግሯል።

Jemen Sanaa Flüchtinge Mai 2014
ምስል picture-alliance/dpa

ሰለሞንም ሆነ እዝና በጉዞው ስለሚገጥማቸው መከራ ጠንቅቀው ያውቃሉ። እዝና ከለቅሶዋ ጋር እየታገለች ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌላቸው ታስረዳለች። «ምን ይዤ?» ከሚለው የኢኮኖሚ ጥያቄ ባሻገር በእጃቸው የጉዞ ሰነድ ባለመኖሩ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ቢያስቡ እንኳ ያለፉበትን መራራ ጉዞ መድገም ይኖርባቸዋል።ሰለሞን «አቅጣጫ የመሳት፤የመናወጥ፤ብርድ፤የመገልበጥ እና የመዋጥ ችግር እንዳለ እንሰማለን። እንዲህ አይነት እጣም የሚደርሳቸው ሰዎች እንዳሉ እንያወቅን ነው። ከሞት ጋር እየተነጋገርን ነው ማለት ትችላለህ።» ሲል ተናግሯል።

በዚህ ወር ብቻ ከሊቢያ ወደብ ተነስተው የሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ ጣሊያን ለመሻገር የሞከሩ 300 ስደተኞች ለሞት ሳይደረጉ እንዳልቀረ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን አስታውቋል። ባለፈው አመት ብቻ 218,000 ሰዎች የሜድትራኒያን ባህርን በጀልባ አቋርጠዋል። 3,500 ያህሉ ግን ከጉዞው መጨረሻ መድረስ ሳይችሉ በባህሩ ላይ ህይወታቸውን አጥተዋል። ሰለሞን እና የዝና በጉዞው ሊገጥማቸው የሚችለውን ሁሉ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ቢሆንም ፓስፖርትም ይሁን ህጋዊ የጉዞ ሰነድ በእጃቸው ባይኖርም ጉዞ ለመጀመር ዝግጅት ላይ ናቸው።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ