1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሰላጣ ያጣላ ተህዋሲ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 23 2003

ጀርመን ዉስጥ ሰላጣ መመገብ የጤና ችግር ያስከትላል ከሚባልበት ደረጃ ባይደርስም፤ እሳት ያልነካዉን ምግብ ለመመገብ ስጋቱ ከፍ ብሏል።

https://p.dw.com/p/RR3f
EHECምስል picture-alliance/dpa

ሰሞኑን የጀርመን የጤና ባለሙያዎችን ያሳሰበዉ ኤሄክ የተሰኘዉ ባክቴሪያ ከአስር በላይ የተቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ማሳጣቱ ነዉ። ባክቴሪያዉ በተለይ ከስፓኝ በሚገባ በጥሬዉ ከሚበላ አትክልት ላይ ተገኝቷል ነዉ የሚባለዉ።

ዛሬ ባክቴሪያ ስለተገኘ ለጤና ትኩረት በመስጠት ስለጤናማ አመጋገብ የሚነገረዉ አትክልት መመገብ ጤና ነዉ የሚለዉ አባባል ይቀየራል ማለት አይሆንም በጀርመን። አትክልትን በአግባቡ አጥቦ፤ መመገብ በዋነኛነት የተመከረ ሲሆን ቢቻል እሳት ያልነካዉን አትብሉ ነዉ የሰሞኑ የጀርመን መገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቡት ዘገባ ፍሬ ነገር። ከየምግቡ በተጓዳኝ ሰላጣና ሌሎች አትክልቶችን መመገብ በጀርመኖች አኗኗር ስልት መደበኛ ነዉ። ከፍራፍሬዉ በተጨማሪ ነዉ ታዲያ። በርግጥ በአገር ዉስጥ በገበሬዎች የሚመረት አትክልት ለገበያ መቅረቡ ባይቀርም በየምግብ ሸቀጣሸቀጥ መደብሮች የተለያዩ ሀገራት ምርቶች ይሸጣሉ። ሰሞኑን ትኩረት የሳበዉ ችግር አለበት የተባለዉ ከስፓኝ የገባዉ አትክልት ነዉ።

Salatgurke EHEC Spanische Gurken als Ehec-Quelle identifiziert
ተህዋሲዉ የተገኘበት አትክልት ኸያርምስል AP

ይህን አትክልት በሰላጣነት የተመገቡ ቢያንስ 12 ሰዎች እስካሁን ኤሄክ በተባለ ጀርም ወይም አደገኛ ተህዋሲ ህይወታቸዉን ተነጥቀዋል። በብዙ መቶዎች የተገመቱ ወገኖች ደግሞ በዚሁ ህመም ተይዘዉ ህክምና በመከታተል ላይ ናቸዉ። የሚገርመዉ በዚህ ተህዋሲ ምክንያት ህይወታቸዉን ካጡት ከ12ቱ አስራ አንዱ ሴቶች ናቸዉ። በምህፃሩ ኡሄክ የተሰኘዉ ህመም የደም ተቅማጥ አስከትሎ ጉብትን የሚጎዳ ሲሆን ከከፋ ዉጤቱ ሞት እንደሆነ ባለሙያዎች አሳዉቀዋል። የጤና እክሉ ጠንከር ብሎ የታየዉ ደግሞ በሰሜን ጀርመን ሃምቡርግ እንደሆነ ነዉ ዘገባዎች ያመለከቱት። የጀርመን የጤና ጉዳይ ባለሙያዎች በአገሪቱ የተከሰተዉን የጤና እክል አስመልክተዉ አስቸኳይ ዉይይት እንዲጀመር ትናንት ጠይቀዋል። ዘገባዎች እንደሚሉት እስካሁን ይህን የጤና እክል በሚመለከት ወደሃኪም ቤት የሄዱ ሰዎች ቁጥር አንድ ሺ ሁለት መቶ ደርሷል። እስካሁን ቁጥሩ ስንት እንደደረሰ አዲስ የተሰማ ነገር ባይኖርም መቀመጫዉ ስቶክሆልም ስዊድን የሆነዉ የአዉሮጳ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል እንደሚለዉ በዓለም በስፋት ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች አንዱ ነዉ። ጀርመን ዉስጥ እንዲህ ያለ የበሽታ ምልክት የሚታይባቸዉ ህመምተኞች ቁጥር ግፋ ቢል በዓመት አንድ ሺ ቢደርስ እንደሆነ ያመከቱት ሃኪሞች፤ ባለፉት 10ቀናት ብቻ የታማሚዎች ቁጥር 1,200 መድረሱ የችግሩን አሳሳቢነት እንደሚያሳይ ጠቁመዋል። ከዚህም ሌላ አሁን በሰዎቹ ላይ የሚታየዉ ህመም ጠንከር ያለና ህይወትን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ እንደሆነም ተመልክቷል። ሮበርት ኮህ የተሰኘዉ የጀርመን ብሄራዊ የበሽታዎች ተቋም፤ ሰዎች ጥሬ ኸያር ማለት ኪኩምበር፤ ቲማቲምና የሰላጣ ቅጠል ከመመገብ እንዲቆጠቡ አሳስቧል። የተቋሙ ኃላፊ ፕሮፌሰር ራይንሃርድ ቡርገር በሰሜን ጀርመን የህመምተኞች ቁጥር መብዛቱን ያመለክታሉ፤

EHEC Keime
ምስል dapd

«በሰሜን ጀርመን የበሽታዉ ሁኔታ በመጠንከሩ፤ ኩላሊታቸዉ የሚታጠብ፤ አንዳንዶችም ደም የመቀየር ደረጃ እስኪደርሱ ጎድቷቸዋል። ሃኪም ቤቶች እዚህ ማስተናገድ ከሚችሉት በላይ ታማሚን ይዘዋል፤ የግድ ወደአጎራባች አካባቢዎች ህመምተኞችም ማሸጋገር ይኖርባቸዋል። ከፍተኛ የህክምና ርዳታ መስጠት የሚችሉት ክፍሎች ከመጠን በላይ ተጨናንቀዋል።»

በተለይ በሽታዉ መጀመሪያ በተከሰተበትና በተስፋፋበት ሰሜን ጀርመን አካባቢ ኗሪዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም መክሯል። ምንም እንኳን እስካሁን ለበሽታዉ ምክንያት የሆነዉ አትክልት ከየት እንደገባ በጥናት አልተረጋገጠም የሚሉ ቢኖሩም አሁን በመታከም ላይ የሚገኙት ታማሚዎቹም ሆኑ ህይወታቸዉን ያጡት ወገኖች ጥሬ ቲማቲም፤ የሰላጣ ቅጠልና ኸያርን አብዝተዉ መመገባቸዉን ተናግረዋል። ብዙዎችም የስፓኝ የሚገባ ነዉ ያሉትን ኪኩምበር ማለት ኻያር ለምንጭነቱ ከሰዋል። አትክልት ማለት ሰላጣ አትብሉ ከበላችሁም ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጉ የሚለዉ ማስጠንቀቂያ ከተሰማ ወዲህ በርካቶች ምንም እንኳን ከምግባቸዉ ሰላጣን ማከል ቢወዱም መቆጠባቸዉን ይናገራሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ