1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ኤኮኖሚ በ3.8% እንደሚያድግ አይኤምኤፍ ተነበየ

ረቡዕ፣ ጥር 24 2015

ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት ኤኮኖሚ በተያዘው ዓመት በ3.8% ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ይፋ አድርጓል። "ያለፈው ዓመት ለክፍለ አኅጉሩ ፈታኝ ነበር" ያሉት የድርጅቱ ዋና ኤኮኖሚስት ፒየር ኦሊቪየ የሩሲያ ጦርነት በዩክሬን፣ የኢነርጂ ቀውስ፣ የዋጋ ንረትን ለመዋጋት የሚደረገው ጥረት ጫና ማሳደራቸውን ተናግረዋል

https://p.dw.com/p/4Mz5k
Pierre-Olivier Gourinchas
ምስል Patrick Semansky/AP/picture alliance

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ኤኮኖሚያዊ ትንበያ

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በጎርጎሮሳዊው 2023 ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ምጣኔ ሐብት በ3.8 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይፋ አድርጓል። በዓመት ሁለት ጊዜ የዓለምን የኤኮኖሚ ሁኔታ የሚያሳይ ትንበያ ይፋ የሚደርገው ድርጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት ምጣኔ ሐብት ዕድገት "መጠነኛ" እንደሚሆን ገልጿል። በጎርጎሮሳዊው 2024 የክፍለ አኅጉሩ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት ወደ 4.1 በመቶ ከፍ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ አይኤምኤፍ ጥር 23 ቀን 2015 ይፋ ያደረገው ሰነድ ያሳያል።

በትንበያው መሠረት ከሰሐራ በርሐ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት የትልቁ ኤኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ናይጄሪያ በ3.8 በመቶ፤ በተከታይ ደረጃ የምትገኘው ደቡብ አፍሪካ በአንጻሩ 3.2 በመቶ ያድጋሉ። "ያለፈው ዓመት ለክፍለ አኅጉሩ ፈታኝ ነበር" ያሉት  የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ኤኮኖሚስት ፒየር ኦሊቪየ "የሩሲያ ጦርነት በዩክሬን፣ የኢነርጂ እጥረት ቀውስ፣ የዋጋ ንረትን ለመዋጋት የሚደረገው ጥረት እና ይኸን የተከተለው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ እጥረትን በመሳሰሉ ውጪያዊ ምክንያቶች" ጫና ማሳደራቸውን ተናግረዋል።

የክፍለ አኅጉሩ 3.8 በመቶ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት በቀጠናው ከነበረው የተለመደ የዕድገት መጠን ዝቅ ያለ ነው" ያሉት ኦሊቪየ "በቀጠናው የምግብ ዋጋ የሩሲያ ጦርነት በዩክሬን ከመጀመሩ በፊት ወደ ነበረበት መመለስ ቢጀምርም ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አሁንም ከፍ ያለ ነው። ከሕዝባቸው መካከል አብዛኛው የምግብ ዋስትና እጦት የሚገጥማቸው አገራት አሉ" ብለዋል።

ናይጄሪያ ወደብ
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያው መሠረት ከሰሐራ በርሐ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት የትልቁ ኤኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ናይጄሪያ በ3.8 በመቶ፤ በተከታይ ደረጃ የምትገኘው ደቡብ አፍሪካ በአንጻሩ 3.2 በመቶ ያድጋሉ።ምስል Pius Utomi Ekpei/AFP/Getty Images

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በ5.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለፈው ጥቅምት ተንብዮ ነበር። ትንበያው በዓመቱ የኢትዮጵያ አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን ወደ 126 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ያሳያል። የኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያ በአንጻሩ ኤኮኖሚዋ በ5.1 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ሲተነበይ፤ አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠኗ 100 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሆኖ ይቆያል። የድርጅቱ ትንበያ ከሰራ ኢትዮጵያ ኬንያን ተክታ በክፍለ አኅጉሩ የአራተኛው ግዙፍ ኤኮኖሚ ባለቤት ትሆናለች።

የቀደመው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ይፋ የሆነው የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት የገታው ግጭት የማቆም ሥምምነት ከመፈረሙ በፊት ነው። በሥምምነቱ ጋብ ያለው ጦርነት እና ተያያዥ ጉዳዮች አይኤምኤፍ በመጪው ሚያዝያ ይፋ በሚያደርገው የዓመቱ ሁለተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ይጠብቃሉ።

በጦርነቱ ሳቢያ የተስተጓጎሉ ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ማንሰራራት እና ለመልሶ ግንባታ ከአገሪቱ አጋሮች የሚጠበቀው ዳጎስ ያለ ድጋፍ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ለምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት መነቃቃት አስተዋጽዖ ሊያደርጉ ይችላሉ ከሚሏቸው መካከል ናቸው። ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓ ኅብረት ካሉ ዓለም አቀፍ አጋሮቿ በጦርነቱ ምክንያት የተከለከለችውን እርዳታ መልሳ ማግኘት ከቻለች እና ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ ንዋይ መሻሻል ካሳየ የተሻለ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል።

Äthiopien, Tigray Konflikt, Getachew Reda von TPLF und Feldmarschal Berhanu Jula
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በ5.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለፈው ጥቅምት ተንብዮ ነበር። ትንበያው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሥምምነት ጋብ ከማለቱ በፊት የተሰጠ ነው። ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP

የዓለም ኤኮኖሚስ እንዴት ይሆን?

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጥር ወር ትንበያ የዓለም ኤኮኖሚ መጻኢ ጊዜ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ጥቆማ ሰጥቷል። በሰነዱ መሠረት የዓለም ኤኮኖሚ ባለፈው ዓመት ከተተነበየው 3.4 በመቶ ዝቅ ያለ 2.9 በመቶ ዕድገት ይኖረዋል። ይኸ ዕድገት በሚቀጥለው ዓመት ወደ 3.1 በመቶ ከፍ ሊል ይችላል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ኤኮኖሚስትፒየር ኦሊቪየ “የዓለም ኤኮኖሚ በሚቀጥለው ዓመት ከማገገሙ በፊት በዚህ ዓመት ይቀዛቀዛል ተብሎ ይጠበቃል። ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ከቀደሙት ዓመታት አኳያ ደካማ ነው። እነዚህ ፈተናዎች ቢኖሩም የአሁኑ ተንበያ በጥቅምት ወር ይፋ እንዳደረግንው ያን ያክል ጨለምተኛ አይደለም። ይኸ ትንበያ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ተነቃቅቶ የዋጋ ንረት የሚቀንስበትን ወቅት ሊወክል ይችላል" ሲሉ  ተናግረዋል።

የበለጸጉት አገሮች በተለይ ከፍ ያለ የኤኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ የሚገጥማቸው ናቸው። የበለጸጉ ከሚባሉት አስር አገሮች ዘጠኙ ዛሬ ሁለተኛ ወሩን ባስቆጠረው የጎርጎሮሳዊው 2023 ኤኮሚያዊ ዕድገታቸው እንደሚቀዛቀዝ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ኤኮኖሚስት ፒየር ኦሊቪየ ተናግረዋል።

ቻይና ግዙፍ ዕቃ ጫኝ መርከብ ከወደብ ቆሞ
በጎርጎሮሳዊው 2023 በዓለም የሁለተኛው ግዙፍ ኤኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ቻይና 5.2 በመቶ ዕድገት እንደሚኖራት ትንበያው ያሳያል።ምስል STR/AFP/Getty Images

አሜሪካ በ1.4 በመቶ፤ ብርቱ የኢነርጂ ቀውስ የገጠመው የአውሮፓ ኅብረት በአንጻሩ 0.7 በመቶ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። የሩሲያ ኤኮኖሚ በአንጻሩ በዩክሬን ጦርነት እና ጦርነቱን ተከትሎ በተጣሉበት በርከት ያሉ ማዕቀቦች የገጠመውን ፈተና ተቋቁሞ መዝለቁን የዓለም አአፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ አሳይቷል። ድርጅቱ በጥቅምት ወር በጎርጎሮሳዊው 2023 የሩሲያ ኤኮኖሚ በ2.2 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል የሰጠውን ትንበያ ከልሶ እንዲያውም በ0.3 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ይፋ አድርጓል።

በጎርጎሮሳዊው 2023 በዓለም የሁለተኛው ግዙፍ ኤኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ቻይና 5.2 በመቶ ዕድገት እንደሚኖራት ትንበያው ያሳያል። በተለይ ባለፉት ዓመታት በኮቪድ ሳቢያ ቅርቃር ውስጥ ገብቶ የቆየው የቻይና ኤኮኖሚ ማንሰራራት ለተቀረው ዓለም ተስፋ የሰጠ ጉዳይ ነው። "የቻይና ኤኮኖሚ ዳግም መከፈት በዓለም የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ አለው። ምክንያቱም ኤኮኖሚው አንዴ ሙሉ በሙሉ ከተከፈተ ባለፈው ዓመት እንደተመለከትንው ያለ በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚፈጠር መስተጓጎል ይቀንሳል ብለን እንጠብቃለን" ሲሉ ፒየር ኦሊቪየ ተናግረዋል።  

የዋጋ ንረት ዓለም አቀፋዊው ፈተና

የዋጋ ንረት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ፖሊሲአ ውጪዎች ሁሉ ፈተና ሆኖ እንደዘለቀ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ኤኮኖሚስት በትላንትናው መግለጫቸው ተናግረዋል። በድርጅታቸው መረጃ መሠረት በሸማቾች ዋጋ መረጃ ጠቋሚ ያለፈው ዓመት የዋጋ ንረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ነበር። ይሁንና ከዓለም አገሮች 84 በመቶው ካለፈው ዓመት አኳያ በጎርጎሮሳዊው 2023 ዝቅ ያለ የዋጋ ንረት ሊኖራቸው እንደሚችል የዓለም የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ያሳያል።

የምግብ ግብዓቶች በገበያ
በሸቀጦች እና አገልግሎቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት በ2022 አራተኛ መንፈቅ ወደ 6.9 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን በዚህ ዓመት መጨረሻ ወደ 4.4 በመቶ ዝቅ ይላል ተብሎ ይጠበቃል። ምስል Wolfgang Maria Weber/imago images

"በአብዛኛዎቹ ቦታዎች በሁሉም መለኪያዎች የዋጋ ንረት የመሻሻል አዝማሚያ አሳይቷል። በምግብ እና በኢነርጂ ላይ የሚታየውን ተለዋዋጭ የዋጋ ጭማሪ ባያካትትም በሸቀጦች እና አገልግሎቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት በብዙ አገሮች ከፍተኛው ደረጃ ላይ አልደረሰም" ሲሉ ፒየር ኦሊቪየ ተናግረዋል።  

"የቻይና በድንገት መከፈት እንቅስቃሴዎች መልሰው እንዲነቃቁ አስተዋጽዖ አበርክቷል። የዋጋ ንረት ጫናዎች መርገብ ሲጀምሩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሁኔታዎች መሻሻል ጀምረዋል" ያሉት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ኤኮኖሚስት  "ይኸ ዶላር በሕዳር ከነበረው ጥንካሬ አኳያ ያሳየው መዳከም በማደግ ላይ ለሚገኙ ኤኮኖሚዎች እፎይታ የፈጠረ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል። ኤኮኖሚስቱ "ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት በዚህ ዓመት ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል" ይበሉ እንጂ  ከ80 በመቶ በላይ በሚሆኑ አገሮች በ2024 ከኮቪድ ወረርሽኝ በፊት ከነበረበት በላይ ሆኖ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

በሸቀጦች እና አገልግሎቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት በ2022 አራተኛ መንፈቅ ወደ 6.9 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን በዚህ ዓመት መጨረሻ ወደ 4.4 በመቶ ዝቅ ይላል ተብሎ ይጠበቃል። የቻይና ምጣኔ ሐብት በኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ ወይም ሌላ ኤኮኖሚያዊ ምክንያቶች ሊገጥመው የሚችል መገተር፤ የዋጋ ንረት እንዲሁም የሩሲያ ጦርነት በዩክሬን አሁንም ለዓለም ኤኮኖሚ ዋንኛ ፈተናዎች ሆነው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ፒየር ኦሊቪየ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ