1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሰሜን ወደ ደቡብ የተመለሱት ሱዳናውያንና ህዝበ ውሳኔው

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 29 2003

የፊታችን እሁድ ፣ የደቡብ ሱዳን ህዝብ ፤ የአገሪቱ አንድነት እንደተጠበቀ በካርቱም አገዛዝ ሥር ለመቆየት ወይም ተገንጥሎ የራሱን መንግሥት ለማቋቋም ፤--ከሁለት አንዱን ለመወሰን አደባባይ ወጥቶ ድምፅ ይሰጣል። አሁን ጁባ ውስጥ የምትገኘው የዶቸ ቨለ ባልደረባ ዚሞነ ሽሊንድቫይን ፣ ብዙኀኑ ነጻነትን እንደሚመርጡ ጥርጥር የለም ባይ ናት።

https://p.dw.com/p/Qoli
ምስል AP

ከሰሜን ወደ ደቡብ በጀልባም ሆነ መርከብ፤ ጁባ ለመግባት፣ 3 ሳምንት ያስጉዛል።

ከካርቱም ተነስተው ጁባ ከገቡት መካከል አንጀሎ ሎኪ የተባሉት የደቡብ ሱዳን ተወላጅ ይገኙበታል። ሎኪ በዐረብኛ እንዲህ አሉ።

«ሰሜን ሱዳናውያን ፣ ደቡቡ እኮ በቅርቡ ከሰሜኑ መገንጠሉ ነው ይሉን ነበር። ይህም ሲሆን፤ በሰሜን ሱዳን ለሚኖሩ ደቡብ ሱዳናውያን ኑሮ ይበልጥ ከባድ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አልሆነም። በሌላም በኩል ፣ የደቡብ ሱዳን መስተዳድር፣ ወደ ትውልድ ቦታችን መመለስ እንደምንችል ይነግረን ስለነበረ፣ ወደትውልድ ቦታዬ ለመመለስ ወስኜ ነው ተጉዤ እዚህ የገባሁት።»

ለ 55 ዓመቱ ጎልማሣ አንጀሎ ሎኪ ፣ ይህ ቀላል ውሳኔ አልነበረም። በልጅነት ያደጉትና የተማሩት ሰሜን ሱዳን ውስጥ ነው ። ያገቧት ሚስታቸውም ሰሜን ሱዳናዊት ናቸው ። 5 ወንዶች ልጆች ተወልደውላቸዋል። ሜካኒኩ አንጀሎ ሎኪ፤ ጥሩ ደመወዝም ይከፈላቸው ነበር። አሁን ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ትተው ነው ጁባ የገቡት ። የጉዞው ወጪ ከባድ ነው ። ጥሪታቸውን አራግፈዋል። ለዚህም ነው ቤተሰብ መጨመር ያልቻሉት። ወደፊት ልጆቻቸው በደቡብ ሱዳን ዕድላቸውን እንዲሞክሩ በማሰብም ፣ በራሳቸው ፓስፖርት ላይ የልጆቻቸውን ፎቶግራፍ ጭምር ለጥፈዋል።

«ደቡብ ሱዳን ነጻ እንዲሆን ነው የምፈልገው። የጦርነቱን ዘመን አስታውሰዋለሁ። ዐረቦች ፣ በእኛ ደቡብ ሱዳናውያን ላይ መጥፎ ድርጊቶችን ፈጽመውብናል። ሰብአዊ መብታችን ገፈዋል። ክብራችንን አዋርደዋል። ከህዝበ-ውሳኔው በኋላ፣ ባለቤቴና ልጆቼ ወደ ደቡብ እንደሚመጡ ተስፋ አለኝ።»

አነጀሎ ሎኪ እንደብዙዎቹ ደቡብ ሱዳናውያን ፣ ለመመዝገብና የምርጫ ካርድ ለመውሰድ ዘግይተው ነው ወደ ጁባ የመጡት። 20 ዓመታት በወሰደው የእርስ በርስ ጦርነት 4 ሚሊዮን ያህል ደቡብ ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት ሀገራትና ወደ ውጭ ለስደት ተዳርገው ነበር ፣ አሁንም 1,5 ሚሊዮን ያህል የደቡብ ሱዳን ተወላጆች በሰሜን ሱዳን እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ይገምታል። እስካሁን ደቡብ ሱዳን የገቡት 50ሺ ገደማ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከደቡብ ሱዳን መስተዳድር ጋር በመተባበር ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም በመርዳት ላይ ይገኛል። የድርጅቱ ተጠሪ፣ ሊሰ ግራንድ እንዲህ ብለዋል።

«የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ ተመላሾቹ እዚህ እንደደረሱ እርዳታ እንዲቀርብላቸው ያደርጋሉ። ምግብ ፣ ድንኳን እንዲሁም የህክምና አገልግሎትና የመሳሰለው እንዲሰጣቸው እናደርጋለን። ይሁንና ፤ ተመላሾቹ፤ ለዘለቄታው ከሞላ ጎደል ኑሮአቸው እንዲስተካከል የማድረጉ ኀላፊነት የደቡብ ሱዳን መስተዳድር ነው። እዚህም ላይ እኛ እርዳታ ማቅረባችን አይቀሬ ነው። ባስቸኳይ 30 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገን በኒው ዮርክ ለሚገኘው የ ተ መ ድ ጽህፈት ቤት አመልክተናል። አንዳንድ ልጆች ኩፍኝ ይዟቸዋል። የክትባት መድኀኒት ያስፈልገናል። ከዚህም ሌላ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ አንፈልግምና፤ እርዳታው በየመንደሩ እንዲታደል ነው የምናደርገው። ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያ ማቋቋም አያስፈልግም»

መሳይ መኮንንn

አርያም ተክሌ