1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አከራካሪዎቹ የወ/ሮ መዓዛ እና የፕሮፌሰር ህዝቄል ንግግሮች

ዓርብ፣ ነሐሴ 3 2011

በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሳምንቱ ውስጥ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ ሁለቱ ከግለሰቦች ንግግሮች ጋር የተያያዙ ናቸው። ንግግሮቹ የተደመጡት ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ እና ከታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ህዝቄል ጋቢሳ አንደበት ነው። በቪዲዮ የተደገፉት እነዚህ ንግግሮች በማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ ትችቶች ቀስቅሰዋል።

https://p.dw.com/p/3Neet
Meaza Ashenafi
ምስል picture-alliance/Geisler-Fotopress/C. Niehaus

አከራካሪዎቹ የወ/ሮ መዓዛ እና የፕሮፌሰር ህዝቄል ንግግሮች

በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሳምንቱ ውስጥ መነጋገሪያ ከነበሩ አበይት ጉዳዮች ውስጥ ሁለቱ ከግለሰቦች ንግግሮች ጋር የተያያዙ ናቸው። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በአንድ የውይይት መድረክ ላይ የተናገሩት ነው። ሁለተኛው ደግሞ አዲስ አበባ በሚገኘው የሚሊኒየም አዳራሽ ለወሎ ተፈናቃዮች የሚሆን ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ፕሮፌሰር ህዝቄል ጋቢሳ ያሰሙት ንግግር ነው። በቪዲዮ ጭምር የተደገፉት የሁለቱም ግለሰቦች ንግግሮች በማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ ትችቶች ቀስቅሰዋል። 

አከራካሪው የወ/ሮ መዓዛ ንግግር የተደመጠው “የፍትህ አካላት ጥምረት” የተሰኘ ኮሚቴ የዛሬ ሳምንት አርብ ሐምሌ 26 ባዘጋጀው ውይይት ላይ ነበር። ውይይቱ “የሕግ ተገዥ ነኝ” በሚል መሪ ቃል ኮሚቴው የጀመረው እንቅስቃሴ አንድ አካል እንደሆነ ተነግሯል። የኮሚቴው ሰብሳቢ በሆኑት ወ/ሮ መዓዛ የተመራው ውይይት በፍትህ አካላት እየተደረጉ ስላሉ ለውጦች እና ስላጋጠሙ ችግሮች ሀሳቦች የተነሱበት ነበር። በፌደራል በተያዙ የሕግ ጉዳዮች ላይ ዳኝነት ለመስጠት በክልሎች ሲንቀሳቀሱ ችግር እንደሚያጋጥማቸው በውይይቱ ወቅት ያነሱት ተሳታፊዎች የፌደራል ፍርድ ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ መፍትሔ ይኖረው እንደው ጠይቀዋል።

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ በፌደራል እና በክልሎች መካከል ህግን በማስከበር ላይ ያለመደማመጥ እና የቅንጅት ችግሮች መከሰታቸውን አምነዋል። የፌደራል እና የክልል መንግስታትን ግንኙነት በተመለከተ እንደትምህርት ሊወስድ ይችላል በማለት በአሜሪካን ሀገር የተከሰተን አንድ ሁነትም በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

Meaza Ashenafi
ምስል Federal Government Communication Affairs Office of Ethiopia

የወ/ሮ መዓዛ ንግግር “አንድ ክልል ላይ ያነጣጠረ ነው” ብለው ያመኑ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ ላይ ከፍተኛ ትችት እና ውግዘት አዝንበውባቸዋል። የተወሰኑቱ እንደውም ፕሬዝዳንቷ ከስልጣናቸው ይወርዱ ዘንድ የሚቀሰቅስ ግልጽ ዘመቻ ከፍተውባቸዋል። ወ/ሮ መዓዛ የትኛውንም ክልል በንግግራቸው ባያነሱም በርካቶች ግን መልዕክቱ “ለትግራይ ክልል የተነገረ ነው” በሚል መራር ትችቶችን ጽፈዋል። 

እንዲህ አይነት እምነታቸውን ካንጸባረቁት ውስጥ ይትባረክ ገብረመድህን የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ይገኙበታል። ይትባረክ “ዳኛ ወይስ ደመኛ?” በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቁት ጽሁፍ የፕሬዝዳንቷን አስተያየት “በጣም ያሳፍራል፤ ያሳዝናልም” ሲሉ ገልጸውታል። “የፍትህ ተቋም ከፖለቲካ ነጻ እና ገለልተኛ መሆን አለበት ተብሎ በሚጠየቅበት ማግስት በተቃራኒው እየተጓዘ ያለው ተቋም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ‘ትግራይ የወሰን እና የማንነት ኮሚሽን እንዲመሰረት በፊርማቸው ይሁንታ አልሰጡምና የኃይል እርምጃ ይወሰድባቸው’ የሚል የደመኛ ማስጠንቀቂያ መልዕክት አስተላልፈዋል። ይህ ከአንድ የፍትህ የበላይ ጠባቂ ባለስልጣን የማይጠበቅ ቢሆንም ቅሉ የእርሳቸው ማንነት እንዲገለጥልኝ ረድቶኛል” ብለዋል ጸሐፊው።  

ስምዖን ብርሃኔ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ በበኩላቸው “መዓዛ አሸናፊ እንዲህ ማለቷ ጥሩ ነው። ጥንቃቄ እናደርጋለን። ከወዛደር እስከ ወታደር ያለው ትግራዋይ የወረራውን አካሄድ በመረዳት ማክሸፍ አለበት” ሲሉ “በትግራይ ላይ የተቃጣ ነው” ላሉት ምሳሌ ምላሽ ሰጥተዋል። ተስፋ የተባሉ ጸሀፊ በዚያው በትዊተር “በወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ አቋም እጅጉን አዝኛለሁ፤ አፍሬያለሁም” ሲሉ ስሜታቸውን አጋርተዋል።  

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷን ምሳሌ “ትልቅ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ንግግር” ሲሉ የጠሩት አንተነህ ረዳኢ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ “የማከብራት መዓዛ አሸናፊ በአጠቃላይ ትልቅ ስህተት ነው የሰራችው” ብለዋል። በግላቸው ፕሬዝዳንቷ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡበት እንደሚሹ የጠቀሱት አቶ አንተነህ “ጦርነትን እንደ አማራጭ ማቅረብ ምን የሚሉት ህግ ማስከበር እንደሆነ ግልፅ ልታደርግ ይገባታል” ሲሉ በአጽንኦት ጠይቀዋል።

ወ/ሮ መዓዛ “የአሜሪካንን ታሪክ ለኢትዮጵያ ሕግ ማጣቀሻ ማድረጋቸውን” ያነሱት ካሳ ሃይለማርያም በአሜሪካ ህገመንግስት ስለ ሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተደነገገውን በማንጸሪያነት ጠቅሰው በኢትዮጵያም የዳኝነት አካሉ ከፖለቲካ ነጻ መሆን ይገባው እንደነበር ይሞግታሉ። ካሳ በፌስ ቡክ ገጻቸው “ከመነሻው የአሜሪካ ሕገመንግሥት፤ ‘ፍርድ ቤት ከፍርድ ቤት ጉዳዮች እና ክርክሮች ጋር ብቻ እንዲገናኝ’ በማለት የዳኝነትን ስልጣን ይገድባል። በማከልም የአሜሪካ ፍርድ ቤት ለአስፈፃሚው አካል የምክር አስተያየቶችን አይሰጥም። ይልቁንም ተግባሩ የተወሰኑ የፍርድ ቤት ጉዳዮችን እና ክርክሮችን በመወሰን ላይ ብቻ የተገደበ ነው ይላል። ወ/ሮ መዓዛ ግን ክብር ያለው ከፍተኛው የፍትሕ እርከን ላይ ተቀምጠው፤ ሕገመንግስትና ሕግን ረግጠው፣ አፈንግጠው፤ ከምክርም አልፈው የትግራይን ህዝብ በጦር ሃይል ስለመውረር ግፊት በማድረግዎ፤ ከዳኝነት ወርደው ወታደራዊ በሚመስል ስብእና ለመኮፈስ በመከጀልዎ፤ አዝናለሁ፤ በእርሶ እንዳፍር አስገድደውኛል” ብለዋል።  

የህግ ባለሙያው እሸቱ ሁማ ቀኖ ወ/ሮ መዓዛ የአሜሪካ የህግ ጉዳይን በምሳሌነት መጥቀሳቸውም ሆነ “በአገሪቱ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ውሳኔዎችን አስፈፃሚው [አካል] ተፈፃሚ ማድረግ አለበት ወይም ይችላል በሚል የሰጡት አስተያየት ብዙ ችግር ያለው አይደለም” ባይ ናቸው። ”ችግሩ ያለው እርሳቸው የሚመሩት የፍርድ ቤት ስርአት ምን ያህል ፍትሃዊ ነው? ምን ያህልስ ከአስፈፃሚው የመንግሥት አካል ተፅዕኖ ውጪ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ተገቢ መልስ መስጠቱ ላይ ነው” ሲሉ በፌስ ቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ ላይ ትችት ያስከተለባቸውን ንግግር በተመለከተ የመስሪያ ቤታቸው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ዳይሬክቶሬት ሰኞ ዕለት በፌስ ቡክ ገጹ ማብራሪያ አቅርቧል። “ወ/ሮ መዓዛ ይሄንን ምሳሌ ያቀረቡት የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ለማስከበር ያደጉት አገራት እስከምን ድረስ እንደሚሄዱ ታሪክን የማወቅ ግንዛቤአችንን የሚያሰፋ በመሆኑ ነው” ያለው ዳይሬክቶሬቱ “በአገራችን ዳኞቻችን በየክልሉ በመዘዋወር የፌዴራል ጉዳዮችን ለማየት እና ለመወሰን የፍርድ ቤት ትዕዛዞች እና ውሳኔዎችን መተግበር ካልቻሉ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሕዝቡ የሚያደርገው ጥሪ ባዶ መፈክር ነው” ሲል አስገንዝቧል።

ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳይ ተሸጋግረናል። ለኦሮሞ ህዝብ የመብት ጥያቄዎች በመሟገት የሚታወቁት የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ህዝቄል ገቢሳ ለብዙሃን መገናኛዎች በሚሰጧቸው ቃለምልልሶቻችም ሆነ በተለያዩ መድረኮች በሚያደርጓቸው ንግግሮች ውዝግብ አያጣቸውም። ባለፈው እሁድ ሐምሌ 28 በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደ ዝግጅት ላይ ያሰሙት ንግግርም ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሞታል። ዝግጅቱ በወሎ ከቀያቸው ተፈናቅለው ለተጠለሉ ዜጎች የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ የተሰናዳ ነበር። በዚህ መሰናዶ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሮፌሰር ህዝቄል በኦሮምኛ እና አማርኛ ቋንቋዎች ንግግር አድርገዋል።

Asemahegn Aseres
ምስል DW/A. Mekonnen

የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች በስፋት ለተቀባበሉት ለፕሮፌሰሩ ህዝቄል ንግግር ምላሽ ከሰጡ ግለሰቦች መካከል የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ ይገኙበታል። ዋና ዳይሬክተሩ በግል የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፕሮፌሰር ህዝቄል በንግግራቸው “አማራን ለማዳከም” በማሰብ ሁለት ጉዳዮችን መጥቀሳቸውን አንስተዋል። “አንደኛው በኩሽ እንቅስቃሴ ሰበብ በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦችን ከአማራው መነጠል፤ ሁለተኛው ተጨማሪ የማንነት ጥያቄዎች በክልሉ ውስጥ እንዲነሱ መደገፍ” እንደሆነ የጻፉት አቶ አሰማኸኝ  ይህ የፕሮፌሰር ህዝቄል ፍላጎት “ቀቢጸ ተስፋ ነው” ሲሉ አጣጥለዋል። 

መንግስቱ ዘገየ የተባሉ ግለሰብ በፌስ ቡክ ገጻቸው “ወሎ ወሎ ነው” ሲሉ የታሪክ ምሁሩን ገለጻ ተቃውመዋል። “የወሎ ኦሮሞ ከወሎየነት የተለየ ማንነት የለውም። የወሎ ኦሮሞ በመልክ፣ በስነ ልቡና፣ በባህል፣ በሁለንተናዊ ማንነቱ ቅርበቱ ለቃሉ እና ለአጣየ አማራ ለቃሉ፣ አርጎባ፣ ለራያ ራዩማ እንጅ ለወለጋ ኦሮሞ አይደለም። የወሎ አማራ፣ የወሎ ኦሮሞ፣ የወሎ አርጎባ፣ የወሎ አገው፣ የወሎ ራያ ግዙፍ መገለጫው ወሎየነት እንጅ የጎሳው ስንጥቅ መልክ አይደለም” ሲሉ ሞግተዋል።  

ከድር እንድሪስ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው “ አሁን ባለው ህግ መንግስት እና ስርዓት፤ በታሪክም ይሁን በነባራዊ ሁናቴ ወሎ ውስጥ የወሎ ህዝብ በአንድነት ዘር ቀለም ሀይማኖት ሳይለያይ እሴቱን ጠብቆ ይኖራል። ይህ አንድነት የህዝቡ ህልውና ነው። ልዩነቶች ከተፈጠሩ ሌሎች ከርቀት እያዩ፣ እየነገዱ፣ ከእሳቱ እየሞቁ፣ የወሎ ህዝብ ግን ከባድ ችግር ውስጥ ይገባል፤ በእሳት ይነዳል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። 

ሀሰን ሂዲያ በዚያው በፌስ ቡክ “ ‘ወሎን የመሰረተዉ ኦሮሞ ነዉ’፣ ‘ወሎን የመሰረተዉ አማራ ነዉ’ ብሎ በታሪክ መከራከር ይቻላል። በአሁኑ [ወቅት] ግን ወሎ የኦሮሞ ናት፣ ወሎ የአማራ ናት እያሉ ለአንድ ብሄር ለመስጠት መሞከር ስህተት ነዉ። ወሎ አሁን የኦሮሞዉም፣ የአማራዉም፣ የአፋሩም፣ የአርጎባዉም ናት። ማንም የግሉ ሊያደርጋት አይችልም፤ የጋራችን ናት። በአፋችሁ ‘ወሎ የወሎዬዎች ናት’ እያላችሁ በተግባር የአንድ ብሄር ለማድረግ የምትታገሉ ሰዎች ለኔ አትስማሙኝም” ሲሉ ሀሳባቸውን አካፍለዋል። ቢሊሊ ኦሮሞ የተሰኙ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ለተከራካሪዎች ጥያቄ ማቅረብን መርጠዋል። “ፕሮፌሰር ህዝቄል ወሎ ኦሮሚያ ነዉ ቢል ችግሩ ምንድነዉ? እናንተም እኮ አፋርን [ደፍጥጣችሁ] ግዛታችን እስከ አሰብ ነዉ ብላችሁ እየተመኛችሁ አይደል?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ሙሉ ጥንቅሩን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ