1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሰሞኑ፦ የሶማሌ ክልል ኹከት፤ የካርታ ውዝግብ

ዓርብ፣ ነሐሴ 4 2010

በሶማሌ ክልል መቀመጫ ጅግጅጋ ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሰው እና ወደ ሌሎች የክልሎቹ ከተሞች የተዛመተው ግጭት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች የሳምንቱ ትልቁ መነጋገሪያ ነበር። የክልል እና የአካባቢ ካርታዎች ጉዳይም ሲያወዛግብ ቆይቷል።

https://p.dw.com/p/32ytO
Äthiopien Soldaten
ምስል Getty Images/AFP/J. Vaughan

የሶማሌ ክልል ግጭት፤ የካርታ ውዝግብ

ሳምንቱን የበርካታ ኢትዮጵያውያን ትኩረት ሶማሌ ክልል ላይ አርፎ ነበር። በክልሉ መንግስት መቀመጫ ጅግጅጋ ባለፈው ቅዳሜ ድንገት የፈነዳው ብጥብጥ ድንጋጤ ፈጥሯል። ብጥብጡ ሌሎች የክልሉ ከተሞችን በፍጥነት ከማዳረስ አልፎ ዳፋው ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመዛመት ጊዜም አልፈጀበትም። ችግሩ እንደተከሰተ ወዲያውኑ ይፋ የሆነው ፌስ ቡክን በመሳሰሉ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲሆን ለቀናትም ብዙዎች ስለ ጉዳዩ መረጃዎች ሲቃርሙ የነበረው ከእነዚህ የመገናኛ አውታሮች ነበር። 

በጅግጅጋ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በብዛት ገብተዋል በሚል ተቀሰቀሰ የተባለው ተቃውሞ ወደ ለየለት ሁከት መሸጋገሩም የታየው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ነው። ከከተማይቱ ይወጡ የነበሩ በምስል እና ቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎች ሁኔታው አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን አመላክተዋል። ምስሎቹ በተለያዩ ተቋማት ላይ የተደረጉ ዝርፊያዎችን፣ እዚህም እዚያም በረዥሙ ሲትጎለጎል የሚታይ ጭስ፣ የአብያተ ክርስቲያናትን ቃጠሎ እንዲሁም አደባባይ የወጡ በርካታ ሰዎች የሚያሳዩ ነበሩ። 

በሶማሌ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲተላለፉ ከነበሩ መልዕክቶች፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ቅዳሜ ማምሻውን ከሰጠው መግለጫ እና የኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በፌስ ቡክ ገጻቸው አስነበቡት ከተባለ አወዛጋቢ ጽሁፍ ውጭ ከባለስልጣናት በኩል የተባለ ነገር አለመኖሩ የመረጃ ውዥንብሩን አባብሶታል። በርከት ያሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች በሶማሌ ክልል ካሉ ዘመዶቻቸው በስልክ አገኘነው ያሉትን መረጃ በየሰዓቱ ማውጣታቸው የችግሩ ከባድነት ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል። በዚህ ሁሉ ውስጥ መንግስታዊው የቴሌቪዥን ጣቢያም ሆነ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ሰዎች የሞቱበትን ብጥብጥ ከመዘገብ በመታቀባቸው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከፍተኛ ትችት ደርሶባቸዋል። በመንግስት የሚተዳደሩት መገናኛ ብዙሃን የተሸበበ ልሳናቸው መከፈት የጀመረው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ጅግጅጋ በይፋ መግባታቸውን እና ክልሉን ለረጅም ዓመታት ሲያስተዳድሩ የነበሩት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ከስልጣናቸው መልቀቃቸውን ካወጁ በኋላ ነበር። ሳምንቱን ሙሉ መነጋገሪያ የነበረው የቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት የአቶ አብዲ ሁኔታ እና እጣ ፈንታ እስካሁንም እንቆቅልሽ እንደሆነ አለ።  

Äthiopien Stadt Jijiga
ምስል DW/T. Waldyes

ወሰን አየሁ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ በሶማሌ ክልል የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ጠቅለል አድርገው ተመልክተውታል። “ከአንድ ያረጀ እና የተበላሸ ሥርዓት ወደተሻለ ሁኔታ ስትጓዝ መንገዱ ፍፁም ቀና ሊሆን አይችልም፡፡ ወይም ቀና አይሆንም፡፡ በሌላ አነጋገር ከአሮጌው መንገድ ወደ አዲሱ መንገድ ጉዞ ስትጀምር ‘መታጠፊያ’ ሊገጥመህ ይችላል፡፡ እዚያ መታጠፊያ ላይ ስትደርስ ልትደናበር፣ ልትደናገር ትችላለህ፡፡ አብረህ ከምትጓዘው ሰው ጋር ተስማምተህ የአዲሱን መንገድ ትክክለኛ አቅጣጫ እስክትይዝ ‘መንገራገጭም፤ መነጫነጭም’ ሊከተል ይችላል፡፡ አሁን እንደዚያ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለን ይመስለኛል፡፡ ካረጀ እና ካፈጀው አግላይ ሥርዓት ወጥተን፣ ወደ አሳታፊ ሥርዓት የምናደርገው ጉዞ ታሪካዊ መታጠፊያ ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡

የሱማሌ ክልል ሁከት ለዚህ ሁነት ዓይነተኛ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ አሁን ወሳኙ ጥያቄ ከዚህ፣ ‘የታሪክ መታጠፊያ’ በአስቸኳይ ወጥተን ወደምንፈልገው አቅጣጫ የምንምዘገዘገው እንዴት ነው? የሚል ነው፡፡ መልሱ ቀላል ነው፡፡ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ወደቀደመውና ወደተጠየፍነው አግላይ ሥርዓት እንመለስ፣ ወይስ ወደ አሳታፊ ሥርዓት እንገስግስ?”

ጋዜጠኛ ፍስሀ ተገኝ በትዊተር ገጹ “የፍቅር ከተሞች የሆኑት ድሬደዋ፣ ሀረር እና ጅጅጋ እንዲህ የማንም የፖለቲካ ነጋዴ መቀለጃ ሆነው ማየት በእውነት ያሳምማል” ሲል ጽፏል። “ባለፉት 27 አመታት ውስጥ በእነዚህ ግዙፍ የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞችና ህዝብ ላይ ግፍ ተሰርቷል፤ ተንኮልም ተሸርቧል” ብሎ የሚያምነው ፍስሀ ስሜቱን በሀዘን ምልክት አጅቦ አጋርቷል። መቅደስ የተባለች ተጠቃሚ በዚያው በትዊተር “የብሄር ጦርነት ሲከሽፍባቸው ወደ ሀይማኖት-ነክ ተሸጋግረዋል። ያልገባቸው ነገር ህዝቡ እንደነሱ ቀሽም አይደለም። ቤተ-እምነትን ማቃጠል እና አማኙን ማሳደድ፣ መግደል ከቅሽምናም በላይ ራስን መግደልና እና ማዋረድ ነው” ስትል ተችታለች።

አብይ ሰለሞን በበኩሉ “ጅጅጋ የሆነውን ሁሉ ስንሰማ፣ ደቡብ አፍሪካ ላይ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመው ግፍ፣ ሊብያ ላይ በISIS የተገደሉ  ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ምኑ ይገርምና! እና ሀገር የቷ ትሆን? ቤትስ የት ነው? እኔ እና ልጆቼስ ከየትኛው ወገን ነን?” ሲል በፌስ ቡክ ገጹ ጠይቋል። የሶማሌ ክልሉ ግጭት ያሳዛነው ነቢል ሰይድ ሀሳቡን በፌስቡክ እንደሚከተለው አካፍሏል። 

“ለሚያልፍ ፖለቲካ የንፁሃን ወገኖቻችን ህይወት ሲቀጠፍ በጣም እናዝናለን። ለሚያልፍ የፖለቲካ ቁማር ጭፍኖች ተነድተው ወገናቸውን በዘር፣ በጎሳ ለይተው ሲጎዱ ይበልጥ እናዝናለን። ከዚህም ከፍቶ ለጥቂቶች ሥልጣን ጥም፣ የፖለቲካ ቁማር፣ ክቡር የሆነውን የእምነት ተቋም ቤተክርስቲያን ሲቃጠልና የሃይማኖት አባቶች ሲገደሉ በጣሙን እናዝናለን። የእዚህ ዘግናኝ ድርጊት ጠንሳሾችን፣ ተባባሪዎችን እና ተነጂዎችን ሰውነት እንጠራጠራለን። የፌደራል መንግስት እዚህ ጭንቅ ላይ ሆነው የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት ሁኔታ ድረሱልን እያሉ ያሉትን ወገኖች ሊደርስላቸው ግድ ይላል። እንደ ዜጋ አፋጣኝ መፍትሄ እፈልጋለሁ” ብሏል ነቢል። 

Äthiopien Abiy Ahmed OPDO
ምስል Abdulbasit Abdulsemed

የእሙ ልጅ በተሰኘ ስም ፌስ ቡክ የሚጠቀሙ ግለሰብ በሶማሌ ክልል የታየውን ችግር ለመፍታት መንግስት መውሰድ ይገባዋል ያሉትን እርምጃ ጠቁመዋል።  “የዶ/ር አብይ መንግስት የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማስጠበቅ የወሰዳቸው እርምጃዎች ፖለቲካዊ ብስለትና ብልህነት የተላበሱ ነበሩ፡፡ በተለይም በሀገሪቱ ተቋማት ውስጥ ረጃጅም እጅ ያላቸው አካላትን (Deep state) ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥፋት ለመቀነስ ወይም ለማስወገድ የመረጠው ጎዳና የሚወደስ ነው፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ብስለትና ብልህነት በሶማሌና አፋር ክልልም ሊደገም ይገባል፡፡ በተለይም የሶማሌ ክልል እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው፡፡ ሰሞኑን እየተሰማ ያለው ሁከት ወደለየለት ቀውስ እንዳያድግ እና ሀገሪቷን ብሎም የምስራቅ አፍሪቃን ቀጠና ሰላምና መረጋጋት እንዳያናጋ ብስለት የተሞላባቸው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መፍትሄዎች ከየትኛውም ወታደራዊ መፍትሄ በፊት መቅደም አለባቸው፡፡

መንግስት በቀዳሚነት በክልሉ የሚኖሩ ዜጎችን ሰላምና ደህነትን ለማስጠበቅ የፖለቲካ ስራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ከጎረቤት ሀገሮችም በዋናነት ከሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሌላንድና ፑንትላንድ ጋር በቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋት ዙሪያ በአስቸኳይ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ከመንግስት እስከዛሬ ያሳየንን የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ብልህነትና ብስለት ዛሬም፣ ነገም እንጠብቃለን፡፡ የመጨረሻ አማራጮች የመጀመሪያ ሲሆኑ መጨረሻው የከፋ ይሆናል፡፡”

አሊ ሳሚር ሲጋድ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ በሶማሌ ክልል የታየውን ችግር ለመፍታት ባቀረቡት የመፍትሄ ሀሳብ ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳይ እንሻገራለን። “ኦህዴድ እንደ ቀደሞው የህወሃት ቡድን ባለሥልጣናት ሶማሌ ክልልን በሞግዚት ለመስተደደር ባይሞክር ጥሩ ነው። የሶማሌ ህዝብ ፍላጎት ይጠባቅ። ሁሉም የህብረተሰብ አካላት ተወካዮች በተገኙበት ቦታ የሁለት አመት የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት” ብለዋል አቶ አሊ። 

ከሰሞኑ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲያወዛግብ የሰነበተው የካርታ ጉዳይ ነው። ለውዝግቡ መነሻ የሆኑት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃዋር መሐመድ ናቸው። በጊንጪ ከተማ በኦሮሚያ ክልል ህይወታቸውን ላጡ ወጣቶች ሊገነባ ለታቀደው መታሰቢያ አቶ ጃዋር የመሰረት ድንጋይ እንዲያስቀምጡ ይደረጋል። በመሰረት ድንጋዩ ላይ የተሳለው የኦሮሚያ ካርታ “የአማራ ክልል አካባቢዎችን አጠቃልሏል” በሚል በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተቀሰቀሰው ንትርክ የተለያየ መልክ እየያዘ ለቀናት ቀጥሏል። ብዙዎች የራሴ የሚሉትን ካርታ እየሳሉ በቁም ነገርም፣ ቀልድ በቀላቀለ መልክም ነገሩን ተችተዋል። ይህን የታዘቡት ኤፍሬም ኤፍሬም የተባሉ የፌስ ቡክ ጸሀፊ “የራስ ከራስ ጋር ጨዋታና ቁዘማ” በሚል ርዕስ ተከታዩን አስነብበዋል። “ብዙዎቻችን ላለፉት 27 ዓመታት ከአገራችን ፖለቲካ ተገልለንና ራሳችንን አግልለን ኖርንና ዐቢይ ሲመጣ ነቃን። ከዚያማ መተኛት አቃተን። ሁሉም ለውጥ ዛሬውኑ ካልሆነ ሞተን እንገኛለን አልን። የተኛንበትን ዘመን ለማካካስ የምንሞክር ይመስላል። የምንጠብቀውና የምንፈልገው ነገር እውነታ ላይ የተመረኮዘ ነገር አይደለም። የመረጃ ምንጫችንን እንኳን ጠንቅቀን አናውቅም፤ በቅጡም አልለየንም። የፖለቲካ ጉርምስና ልበለው?

Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

የምንደግፈውን አካል የሚጎዳ ነገር ስንሠራ አይታወቀንም። ከኦሮሞው መካከል የተገኙትን መሪዎች ሊያስበላቸው የሚታትረው እዛው ያለው ለኦሮሞ እታገላለሁ የሚለው ነው። እነቲም ለማ ይህንን ድል ያገኙት ከተሸናፊው የኦነግ አይዲዮሎጂ በማምለጣቸው እንደሆነ አልገባውም። እንደለመደው ተቀብሮ ሊቀብራቸው ይጥራል። ወያኔ ዳር ተቀምጦ ይስቃል። ራሱ ለራሱ ያጸደቀውን ካርታ እየተመለከተ ሲደሰት ይውላል። ካርታው በካርታ እንደሚሻር አይገምትም። ወረቀት ላይ ማስመርና መሬት ላይ ማስመር ያላቸውን ልዩነት ከኢትዮ-ኤርትራ ገና አልተማረም” ብለዋል። 

ሰሚር አሊ በፌስ ቡክ ይህንኑ የካርታ ጉዳይ አንስቷል። “የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የተስፋፊነት ፋክክራቸው ከመስፋቱ የተነሳ የምድር ካርታ አልቆ በእነ ማርስ እና ጁፒተር ይገባኛል እንዲሁም ‘ጨረቃ የኔ ነች፤ ጸሀይ የኛ ነች’ ክርክር ውስጥ በቅርቡ ሳይገቡ አይቀሩም” ሲል ተሳልቋል። ሊበን ጸጋዬ“ሀገር ማለት ካርታ ነው ሆነ ነገሩ” ሲሉ ትዝብታቸውን በትዊተር አስፍረዋል።  

ብሩክ ሚካኤል “የኦሮሚያን ካርታ መያዝ ሀጥያት አይደለም” ሲሉ በፌስ ቡክ ተከራክረዋል። “የኦሮሚያን ካርታ በመሰረት ድንጋዩ ላይ መለጠፍ በኦሮምያ የሞቱ ወጣቶችን ጠቅልሎ ማሳያ ነው። ኢትዮጵያ እንደ አሜሪካ ሁሉ በፌደሬሽን አስተዳደር የምትመራ ነች ። በፌደሬሽን አስተዳደር ደሞ ክልሎች የራሳቸው ካርታ ፣ባንዲራና የመተዳደርያ ህጎች አሏቸው ። ካሊፎርንያ የራሷ ካርታ አላት። የካልፎርንያ ነዋሪዎች ልክ እንደ ኦሮምያ ነዋሪዎች በካልፎርንያ ካርታ ቅርፃቅርፅ ይሰራሉ ፣ የቁልፍ መያዣ አድርገው ይጠቀሙበታል ፣ ቲሸርትና ኬፕ ላይ አሳትመው በተለያየ ዝግጅቶችና በተራው ቀንም ጭምር ያጌጡበታል ። የኦሮምያ ነዋሪዎች ወይም ጀዋር በኦሮምያ ካርታ ከካልፎርነያ ነዋሪዎች የተለየ ምንም የሰራው ነገር የለም።  

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

ካርታው ወደ አማራ ክልል ዘልቆ ገባ ? እውነት ገብቶ ከሆነ በዚህ እኔም ከናንተ ጋር እስማማለው ። ለስራ ፣ለፍቅርና ለመተባበር ካልሆነ በቀር ማንም ወደ ማንም ክልልን ዘው ብሎ ገብቶ የኔ ነው እንዲል አልፈቅድም። ከዚህ አይነት ሰዎች ጋርም አልሰለፍም። በዚህ ወደ አማራ ክልል ዘልቆ ገባ የሚባለው ካርታ በስህተት ተሰርቶ ከሆነ ካርታን በወረቀት፣ በእንጨትና በተለያዩ ቅርፃቅርፅ የሚሰሩ ሰዎች ለወደፊት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክራለው ። በትክክል የአማራን መሬት ነጥቆ የኦሮምያ ለማድረግ የታሰበ ከሆነ ህገወጥ ነው፣ የማይገባውን ያውም የሰው መሬት ለመውረር ከጀዋር ጋር የሚሰለፍ ኦሮሞም የለም እሱም ይህን አያስብም ስለዚ ይህን ‘ሊወረን ነው’ የሚል ውሃ የማያነሳ ክስ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።  

ዋሲሁን ተስፋዬ የብሩክን ሀሳብ የሚቃረን አስተያየት በፌስ ቡክ ሰጥተዋል። “ጨፍኑ ላሞኛችሁ የሚባል ነገር አይሰራም” ሲሉ የተንደረደሩት ዋሲሁን “ኦነግ የራሱን ካርታ ሲከልል አይቶ እንዳላየ የሚሆን አመራር ስለሰላም ለመስበክ ሲሞክር ይደብራል” ብለዋል። “ ‘ኦነግ መሬታችሁን የመውረር እቅድ እንዳለው በካርታው ቢነግራችሁም ግድ የላችሁም፤ ከሰላም ስለማይበልጥ ቻሉት’ አይነት ጨዋታ ሩቅ አያስኬድም። እርግጥ ነው ከሰላም የሚበልጥ ምንም ነገር የለም፣  ሆኖም ግን ሰላሙን ዘላቂ የማያደርግ ውጥን ሲዘጋጅ አይንን ጨፍኖ ዘላቂ ሰላምን ለማግኘት ማሰብ አይታሰብም” ሲሉ ተቃውመዋል። 

እስክንድር መስፍን በትዊተር “በኢትዮጵያ ታሪክ ወደ ኋላ ተመልሰን የሕዝቦች አኗኗር እና አሰፋፈር ሁኔታ እናጥና ብንል አሁን በሕሊናችን ካለው ወይም ክልል ተብሎ ከተሰመረልን ጋር በፍጹም አይገናኝም” ብለዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን የምናጠቃልለው ፍቃዱ ጃለታ በትዊተር ባሰፈሩት የግል ምልከታ ይሆናል። “የሚያግባባን ካርታ የለንም፤ የሚያግባባን ባንዲራ የለንም፤ የሚያግባባን ጀግና የለንም፤ የሚያግባባን ቋንቋ የለንም ። የዶ/ር አቢይ  ልፋት” ሲሉ አቶ ፍቃዱ አጭር መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።  

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ