1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሰዎች፤ለሰዎች-የኖሩት ሰዉ ስንብት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 26 2006

ግርማ-ሞገሳሙ ሽማግሌ ከልብ የመነጨ ፈገግታ ለገሰኝ።ክንዱን እያያሻሸሁ ሳዋራዉ--- አንዳድ ባልደረቦቹን ጠየቀኝ።ከሚጠይቀኝ ሰዎች አንዳዶቹን ከጥቂት ጊዜ በፊት አግኝቷቸዉ ነበር--» እና አከሉ ፀሐፊዋ---«ካርል የማስታወስ ችሎታዉ እየከዳዉ መሆኑን የተገነዘበ መሰለኝ።»

https://p.dw.com/p/1CAlW
ምስል picture-alliance/dpa

እንደ ፊልም ተዋኝ ጀርመኛ በሚናገረዉ አዉሮጳዊ ዘንድ አድናቆት ሥም፤ ዝናቸዉ የናኘዉ በ1955 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎረሳዊያኑ አቆጣጠር ነዉ) በተጫወትቱት ታሪካዊ የፍቅር ፊልም ነዉ።ዚሲይ፤የፊልሙ ርዕሥ የዋናዋ ገፀ ባሕሪ መጠሪያም ነዉ።ዚሲን ሆና የተጫወትችዉ ሮሚ ሽናይደር ግንቦት ሃያ ዘጠኝ 1982 አረፍች።ሰላሳ-ሁለት ዓመት ቆይተዉ የፊልም ላይ ፍቅረኛቸዉ በሞተችበት ዕለት ሞቱ።አስደነቁ።«አባቴን» አሉ ትልቁ ልጃቸዉ በቀደም «ኢትዮጵያዉያንም «አባባ» ይሉታል፤ እና አሁን« ባባቶች ቀን ሞተ።እንደ ልጅ ለወላጆቻቸዉ፤ እንደወንድ ለሴቶች፤ እንደ አባት ለልጆች፤ እንደ በጎ አድራጊ ለግፉዓን የነበራቸዉ ፍቅርም አስደናቂ ነበር።እንዳስነቁ ኖረዉ-እንደኖሩት ሞቱ።ካርልሐይንስ በም።ላፍታ እንዘክራቸዉ።

በ2003 -ሰባ አምስትኛ የልደት በዓላቸዉን ሲያከብሩ-የዕድሜያቸዉን መግፋት፤ የሥራቸዉን ባሕሪ፤ዉጥረት ጠቃቅሶ ጋዜጠኛዉ ጠየቃቸዉ «እስከ መቼ ይቀጥላሉ፤ ኢትዮጵያስ ይኖራሉ» ዓይነት ብሎ።ዕቅድ፤አላማ-ፍላጎታቸዉን ለመግለፅ አብነት ያደረጉት አባታቸዉን ነበር።አባታቸዉ የሙዚቃ መሳሪያ መሪ-(ኮንዳክተር) ነበሩ።«ልክ እንደ አባቴ እሰከጨረሻዉ እሰራለሁ። የሙዚቃ መሳሪያ መሪ (ኮንዳክተር) የነበረዉ አባቴ ሕይወቱ ልታልፍ ሁለት ወር እስኪቀረዉ ድረስ ሲሰራ ነበር።እኔም ጤናዬና አካሌ እስከፈቀዱልኝ ድረስ ጠንክሬ መስራቴን አቀጥላለሁ።ኢትዮጵያ ዉስጥ ለረጅም ጊዜ መኖር እችላለሁ ብዬ በርግጠኝነት እስባለሁ።የፊልም ኮከብ እባል በነበረበት ዘመን እንኳ የተንደላቀቀ ኑሮ ኖሬ አላዉቅም።ቅንጦት ለኔ ብዙም ትርጉም የለዉም።ሕይወት የሚመቸች ቀለል ሲል ነዉ።አራት ነጥብ።»

Karlheinz Böhm Romy Schneider Sissi
ምስል imago/teutopress

አቶ ቆጠራ-ዮሐነስ በኢትዮጵያ የሰዎች ለሰዎች ምክትል ሐላፊ ናቸዉ።ጤናቸዉ እንደማይፈቅድ ሲገነዘቡ በ1981 የመሠረቱትንና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለሰላሳ ዓመት የመሩትን ድርጅት የመሪነት ሥልጣን ለባለቤታቸዉ ለወይዘሮ አልማዝ በም እስረከቡ።2011።ያቺን ሐገር መለየት ግን አልቻሉም ወይም አልፈለጉም።ኢትዮጵያን።በ2012 ባለቤታቸዉን እና ሁለት ልጆቻቸዉን እስከትለዉ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ሔዱ።«ካርልና ቤተሰቦቹ በተለያዩ አካባቢዎች ያደረጉት ጉብኝት አስደስቷቸዋል።» ፃፉ የካርል ሐይንስ በም የሕይወት ታሪክ ፀሐፊ ቢአት ቬንደኪንድ-ባለፈዉ ቅዳሜ በታተመዉ ቢልድ በተሰኘዉ የጀርመን ጋዜጣ።

«ጉዞዉ እንደተገባደ ግን-ካርል ታመመና ሆስፒታል ገባ።ትንሽ ማገገም ነበረበት።ቀጠሉ ፀሐፊዋ።«ነሐሴ ነዉ-ሁለት ሺ አሥራ-ሁለት።ከትንሺቱ ሆስፒታል፤ ጠባብ ክፍል ስገባ፤ ያ ደጉ፤ ግርማ-ሞገሳሙ ሽማግሌ ከልብ የመነጨ ፈገግታ ለገሰኝ።ክንዱን እያያሻሸሁ ሳዋራዉ--- አንዳድ ባልደረቦቹን ጠየቀኝ።ከሚጠይቀኝ ሰዎች አንዳዶቹን ከጥቂት ጊዜ በፊት አግኝቷቸዉ ነበር--» እና አከሉ ፀሐፊዋ---«ካርል የማስታወስ ችሎታዉ እየከዳዉ መሆኑን የተገነዘበ መሰለኝ።»

የመጨረሻዉ መጀመሪያ መሆኑ ነበር።ቆጠራ ዮሐንስ ግን የሆነዉ-በዚሕ ጊዜ ይሆንል ብለዉ አልገመቱም ነበር።

ካርል ሐይንስ በም።የተራቡ ኢትዮጵያዉያንን ከማየታቸዉ በፊት ድሐነትን ማወቃቸዉ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ። አባታቸዉ ኦስትሪያ ዉስጥ ስም-ዝናቸዉ የገነነ የሙዚቃ መሳሪያ መሪ (ኮንዳክተር)ነበሩ።ፕሮፌሰር ካርል በም።እናታቸዉ ታዋቂ ድምፃዊት።ለሁለቱ ታዋቂዎች ብቸኛዉ ልጅ 1928 ተወለደ።በ1955 ዚሲ በተባለዉ ታሪካዊ የፍቅር ፊልም የኦስትሪዊዉን ወጣት ንጉሰ-ነገስት የፍራንስ ዮሴፍን ባሕሪ ተላብሶ ሲጫወት-የፊልም አፍቃሪዎችን ቀልብ ስርቆታል።

ወጣቱ ካርል የኦስትሮ-ሐንጋሪዋን ንግስተ-ነገሥታት ኤሊዛቤት አማሊ ኦዦኒን ወይም የዚሲን ባሕሪ ተላብሳ ከተጫወተችዉ ሮሚ ሽናይደር ጋር ሆነዉ የሠሩት ፊልም-ዚሲ ለዚያ ዘመኑ ወጣት የፍቅር አብነት ነበር።

ምናልባት ሞትንም-ድሕነትንም በቅርብ ያወቃቸዉ በተመሳሳይ ጊዜ ሳይሆን አልቀረም።1981።«የ87 ዓመት አባቱ ከሞት ጋር ሲፋለሙ አጠገባቸዉ ነበር» ይላሉ የሕወት ታሪካቸዉ ፀሐፊ ቬንደኪንድ።ካርል የባቱን እጅ እንደጨበጠ-አባትዮዉ እስከ መጨረሻ አሸለቡ።«አንድ ቀን የተፈጥሮ ጥሪን መቀበል ግዴ ነዉ» ብሎ ነበር» አከሉ የሕይወት ታሪካቸዉ ፀሐፊ።

Schauspieler Karl-Heinz Böhm mit Frau in Äthiopien
ምስል picture-alliance/dpa

አባታቸዉን እንደቀበሩ ጊዜ አላጠፉም ረሐብ-ከሞት ወደ ሞት የሚያጉዛቸዉን ኢትዮጵያዉያንን ከሞት ለማዳን (ለመርዳት) ይጣደፉ ገቡ። በዚያዉ ዓመት የመሠረቱት ሰዎች ለሰዎች-ሜንሽን ፉር ሜንሽን የተባለዉ ግብረ ሰናይ ድርጅት-ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰወስት ሆስፒታሎችን ጨምሮ ከመቶ የሚበልጡ የጤና ጣቢያዎችን አስገንብቷል።365 ትምሕርት ቤቶችን አሰርቷል።በርካታ የንፁሕ የመጠጥ ዉሐ ጉርጓዶችን አስቆፍራል።ምርጥ ዘሮች አከፋፍሏል።የሴቶች ግርዘት እንዲቆም ታግላል።ሌላም ብዙ።

ሰዎቹን ለመርዳት የዕዉቀታቸዉ ምንጭ-ተርጂዎቹ ራሳቸዉ ናቸዉ።አንዴ ጋዜጠኛዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተተከታታይ ድርቅና ረሐብ ሥለ መከሰቱ ሰብብ-ምክንያትን የእርሻ ባለሙያዎች ምን ይላሉ ብሎ ጠየቃቸዉ ።መለሱ-እንዲሕ እያሉ።

«በተደጋጋሚ በድርቅና ረሐብ በሚጠቃዉ በሐገሪቱ ምሥራቃዊ ግዛት የሚኖሩ ገበሬዎችን ጠይቄ ነበር።ገበሬዎቹ የነገሩኝ እኔን በጣም ነዉ ያስገረመኝ።ዓለም አልገባንም ነዉ-ያሉኝ።እያት አባቶቻችን በቂ ምርት ያመርቱ ነበር።እንዲሕ አይነት ችግር ይመጣል የሚል ጥርጣሬ አልነበራቸዉም።እኛ ግን ይኸዉ እየተቸገርን ነዉ።የሚጥለዉ የዝናብ መጠን በየአመቱ እየቀነስ ምርታችንም እያነሰ ነዉ-ነዉ፤ አልገባንም ነዉ የሚሉኝ።»

ጠይቀዉ፤ አዳምጠዉ፤አዉቀዉ መፍትሔ ፈለጉ።መፍትሔዉ ሰዎቹ ራሳቸዉ መፍትሔ እንዲፈልጉ መርዳት። ትምሕርትንና ጤናን ማስፋፋት፤ የተሻለ ወይም ምርጥ ዘር ማሰራጨት።ብዙ ጣሩ።ያም ሆኖ፤ከሠሩት ብዙ ይልቅ ያልሰሩት እጅግ ብዙ እንደሚበልጥ-አላጡትም።ከረዱት ብዙ ያልረዱት ወይም ርዳታ የሚሻዉ እጅግ በጣም ብዙ እንደሚበልጥ ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።ሙከራ-ምግባራቸዉ ግን ባንድ ወቅት እንዳሉት አብነት ለመሆን ነዉ።

«ሁሉንም ሰዎች መርዳት እንደማንችል ግልፅ ነዉ።እኔ ለምሳሌ እዚሕ መቱ ከተማ የተገነባዉን ዓይነት ሆስፒታል ሁሉም ጋ መሥራት አልችልም።የትምሕርቱንና የጤናዉን ሥርዓት፤ የማሐበረሰቡን ማሕበራዊ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ መለወጥና ማሟላት አልችልም።ይሁንና ለሌላዉ ምሳሌ የሚሆን ነገር ለመሥራት እንሞክራለን።የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ አብነት አድርጎ የወሰደና የሚወስዳቸዉን ነገሮች ለመስራት ነዉ የምጥረዉ።አሁንም የኢትዮጵያ ባለሙያዎች የኛን ሥራዎች እንደ ምሳሌ አድረገዉ እንደሚወስዷቸዉ እየነገሩን ነዉ።

Karlheinz Böhm Menschen für Menschen Äthiopienhilfe
ምስል picture-alliance/dpa

እንዳባታቸዉ ሊሞቱ ሁለት ቀን እስኪቀራቸዉ በርግጥ አልሰሩም። ግን አንድ ሰዉ ሊሠራዉ ከሚችለዉ በላይ አድርገዋል።እንደ ፊልም ተዋኝ ጀርመንኛ በሚናገረዉ ዓለም ዘንድ ሥም-ዝናቸዉ ናኝቷል።እንደ በጎ አድራጊ ከሐረር-እስከ መቱ፤ ከመንዝ እስከ ትግራይ ለፍተዋል።ሥራ-አስተሳሰብ፤ አላማ እቅዳቸዉ ከአዲስ አበባ እስከ በርሊን፤ ከቪየና እስከ ቤርን፤ ከብራስል እስከ ኒዉዩርክ እንደ አብነት ተጠቅሷል።ቆጠራ የሚያክሉት አለ።

ላካርል ሐይንስ በም ከየርዕሠ-ከተሞቹ የጎረፈዉ ሽልማት፤ ማሕበራቱ የተንቆረቆረላቸዉ ምሥጋና ከየዩኒቭርሲቲዎቹ የተበረከተላቸዉ የክብር ማዕረግ-ለምግባራቸዉ ታላቅነት-ታላቅ አብነት ነዉ።እንደ-በጎ አድራጊ ብቻ ሳሆን እንደፊልም ተዋኝ ማፍቀርን ጥሩ አድርገዉ ከዉነዉታል።እንደ ወንድ ኖረዉታል።አራቴ ተሞሽረዋል።የመጨረሻዋ -ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ በም ናቸዉ።ብዙ ልጆች አፍርተዋል።ከወይዘሮ አልማዝ የሚወለዱት ኒኮላስ እና አይዳ ይባላሉ።

የሕይወት ታሪካቸዉ ፀሐፊ ለመጨረሻ ጊዜ ያየቻዉ አዲስ አበባ ሆስፒታል ተኝተዉ ነበር።ነሐሴ 2012።«አዋርቼዉ ልሰናበተዉ ሥል «ሥንብት እንደማልወድ ታዉቂያለሽ አለኝ» አሉ ፀሐፊዋ።ግን እንደ ፊልም ተዋኝ ሮሚ ሽናይደር በሞተችበት-እንደ ሚሊዮን ኢትዮጵያዉን «አባት»- የአባቶች ቀን በሚከበርበት ዕለት-ተሰናበቱ።ሐሙስ ግንቦት-29 2014።86 ዓመታቸዉ ነበር።ካርል ሐይንስ በም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ።ለባለቤታቸዉ፤ ለልጆች፤ ለልጅ ልጆቻቸዉ፤ ለዉላጅ-ዘመድ ወዳጆቾቻዉ ፅናቱን እንመኝ።

25 Jahre Menschen für Menschen
ምስል picture-alliance / dpa/dpaweb

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ