1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከስፖርቱ ዓለም

ሰኞ፣ የካቲት 12 2004

በአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ሻምፒዮና ውድድር ያለፈው ሰንብት በየቦታው ማራኪ የሆኑ ግጥሚያዎችና በርካታ ጎሎች የታዩበት ነበር።

https://p.dw.com/p/1469x
ምስል Reuters

በአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ሻምፒዮና ውድድር ያለፈው ሰንብት በየቦታው ማራኪ የሆኑ ግጥሚያዎችና በርካታ ጎሎች የታዩበት ነበር። በስፓን ፕሪሜራ ዲቪዚዮን እንኳ ሬያልና ባርሣ ብቻ ዘጠኝ ጎሎች ለማስቆጠር ችለዋል። ሣምንቱ ከዚሁ ሌላ በዓለምአቀፍ ደረጃ የአትሌቲክስ፣ የቴኒስና የቡጢ ውድድርም ጭምር የተካሄዱበት ነበር።

በእግር ኳስ እንጀምርና በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ውድድር ሬያል ማድሪድ ዘንድሮ በማንም የሚገታ ሆኖ አልተገኘም። ንጉሣዊው ክለብ በሣምንቱ ግጥሚያውም  ሬሢንግ ሣንታንዴርን 4-0 በመርታት ሊጋውን በአሥር ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ለሬያል ጎሎቹን ያስቆጠሩት ካሪም ቤንዜማ ሁለቱን እንዲሁም የተቀሩትን ክሪስቲያኖ ሮናልዶና አንሄል-ዲ-ማሪያ ናቸው።                             

ሬያል ማድሪድ አሁን ከ 23 ግጥሚያዎች በኋላ 61 ነጥቦች አሉት። ሁለተኛው ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ባርሤሎናም ዘንድሮ ከአመራሩ ራቅ ቢልም በኖው-ካምፕ ስታዲዮሙ ባካሄደው በበኩሉ ግጥሚያ ቫሌንሢያን 5-1 አሸንፏል። ለቀደምቱ ክለብ አራቱን ጎሎች ያስገባው ደግሞ የዓለም ድንቅ ተጫዋች አርጄንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ነበር።                                                                              

ሶሥተኛው ቫሌንሢያ በዚህ ሽንፍቱ ከባርሤሎና 11 ነጥቦች ሊርቅ በቅቷል። በሬያልና በባርሣ ከፍተኛ ድሎች የሁለቱ ክለቦች የጎል አግቢነት ፉክክርም እየጠነከረ ሲሄድ 28 ያስቆጠረው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሜሢን በአንዲት ጎል ብልጫ አስከትሎ ይመራል። ሁለቱ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች እስካሁን በድምሩ 55 ጎሎችን ማስቆጠራቸው ሲሆን ይህም አጥቂዎች እንኳ ያልተሳካላቸው እጅግ አስደናቂ ነገር ነው።

በፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ውድድር ከጌታፌ 1-1 የተለያየው ኤስፓኞል አራተኛ ሲሆን ቢልባዎም በተመሳሳይ 33 ነጥቦች አምሥተኛ ነው። አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ በስድሥተኝነት ይከተላል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሣምንቱ የፌደሬሺኑ ዋንጫ አምሥተኛ ዙር ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። ባለፈው ዙር ማንቼስተር ዩናይትድን ከውድድሩ ያስወጣው ሊቨርፑል ትናንት ብራይተንን 6-1 ረትቶ ወደ ሩብ ፍጻሜው ሲያልፍ ሰንደርላንድ ባልተጠበቀ ሁኔታ አርሰናልን 2-0፤ ላይሴስተር ሲቲያ ኖርቪች ሲቲን 2-1፤ ኤቨርተን ብላክፑልን 2-0፤ እንዲሁም ቦልተን ወንደረርስ ሚልዎልን 2-1፤ ስቶክ ሲቲይ  ክሮውሊይ ታውንን 2-0 አሸንፈዋል።

የተቀሩት ግጥሚያዎች፤ ቼልሲያ ከበርሚንግሃም፤ እንዲሁም ስቴቨኔጅ ከቶተናሃም ሆትስፐር ደግሞ የተፈጸሙት በእኩል ለእኩል ውጤት ነበር።  ትናንት በወጣው ዕጣ መሠረት በሩብ ፍጻሜው እርስበርስ የሚገናኙት ሊቨርፑል ክስቶክ ሲቲያ፤ የቼልሲይና የበርሚንግሃም አሸናፊ ከላይሴስተር ሲቲያ፤ ስቴቨኔጅ ወይም ቶተንሃም ሆትስፐር ከቦልተን ወንደረርስ፤ እንዲሁም ኤቨርተን ከሰንደርላንድ ይሆናሉ። በተረፈ በፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ሁለቱ የማንቼስተር ተፎካካሪ ክለቦች ማንቹስተር ሲቲያና ማንቼስተር ዩናይትድ ቀደምቱ ሆነው እንደቀጠሉ ነው።

1. Bundesliga, Saison 2011/2012, 22. Spieltag, Hertha BSC - Borussia Dortmund
ምስል dapd

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ሄርታ በርሊንን 1-0 በመርታት አመራሩን ውድ ሶሥት ነጥቦች ማስፋቱ ሰምሮለታል። ዶርትሙንድ እስካሁን በ 16 ግጥሚያዎች ያልተሸነፈ  ሲሆን በጠቅላላው 49 ነጥቦች አሉት። በአንጻሩ ሣምንቱ ያልቀናው ታላቁ ክለብ ባየርን ሙንሺን ነበር። ባየርን ከመጨረሻው ክፍራይቡርግ ጋር ባደረገው ግጥሚያ በ 0-0 ውጤት ሲወሰን ይህም ወደ ሶሥተኛው ቦታ እንዲያቆለቁልና ሁለተኝነቱን ለግላድባህ እንዲያስረክብ ነው ያደረገው።

ግላድባህ ካይዘርስላውተርንን 2-1 ሲያሸንፍ ሻልከም ቮልፍስቡርግን 4-0 ረትቶ አራተኛ በመሆን ከቀደምቱ ክለቦች አንዱ መሆኑን እንደጠበቀ ቀጥሏል። ሻልከን ካነሣን የክለቡ ታዋቂ አጥቂ የስፓኑ ራውል በዚያው ግጥሚያ 400ኛ ጎሉን ለማስቆጠር በቅቷል።  ከዚሁ ሌላ ብሬመን ከተከታታይ  እኩል ለእኩል ውጤቶች በኋላ ሃምቡርግን 3-1 በማሸነፍ አምሥተኝነቱን ሲያስከብር ሌቨርኩዝን ደግሞ ስድሥተኛ ነው። በጎል አግቢንት የባየርኑ ማሪዮ ጎሜስና የሻልከው ክላስ-ያን-ሁንቴላር እያንዳንዳቸው 18 አስቆጥረው ይመራሉ።

በኢጣሊያ ሴሪያ-አ የኢንተር ሚላን የሽንፈት ጉዞ መቀጠል በሣምንቱ የሻምፒዮናውን ያህል ማነጋገር የያዘ ጉዳይ ሆኗል። ኢንተር በቦሎኛ 3-0 ሲረታ ይህም በተከታታይ ሶሥተኛ ሽንፈቱ መሆኑ ነበር። ባለፉት ግጥሚያዎቹ ከ 15 ነጥቦች አንዲት ብቻ ሊወስድ የቻለው ኢንተር ሚላን በዚሁ ወደ ስባተኛው ቦታ ሲያቆለቁል የክለቡ ደጋፊዎች የቀድሞው አሰልጣን ሆሴ ሞሪኞ እንዲመለስ እስከመጠየቅ ደርሰዋል። በነገራችን ላይ ፖርቱጋላዊው ዕውቅ አሠልጣኝ ሞሪኞ በወቅቱ ከሬያል ማድሪድ ጋር በስኬት ጉዞ ላይ ነው የሚገኘው።

ለማንኛውም በኢጣሊያው ሻምፒዮና ሌላው የሚላን ክለብ ኤሲ ሚላን ቼሴናን 3-1 በማሸነፍ በ 50 ነጥቦች በአመራሩ ቀጥሏል።  ጁቬንቱስም ካታኛን በተመሳሳይ ውጤት ሲያሸንፍ አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ ሁለተኛ ነው። እርግጥ ጁቬንቱስ ገና አንድ ጨዋታ ይጎለዋል። ኡዲኔዘና ላሢዮ ደግሞ በእኩል 42 ነጥብ ሶሥተኛና አራተኛ ሆነው ይከተላሉ።

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ሰንበቱ ሁለቱ ቀደምት ክለቦች ፓሪስ-ሣንት-ዠርማንና ሞንትፔሊየር እርስበርስ የተገናኙበት ነበር። ሁለቱ ክለቦች በዚሁ ግጥሚያ 2-2 ሲለያዩ የፓሪሱ ክለብ በ 51 ነጥቦች መምራቱን ቀጥሏል፤ ሞንትፔሊየር በ 50 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን በገዛ ሜዳው ከሽንፈት ለጥቂት ነው ያመለጠው። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ሊል በ 42 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን ኦላምፒክ ማርሴይ፣ ኦላምፒክ ሊዮን፣ ሣንት-ኤቲየንና ሬንስ በእኩል 39 ነጥብ ይከተላሉ።

በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶ የመጨረሻውን ሴቱባልን 3-1 በመርታት ቀደምቱን ክለብ ቤንፊካ ሊዝበንን ለጊዜውም ቢሆን እስከ አንዲት ነጥብ ተቃርቧል። ቤንፊካ የበኩሉን ግጥሚያ ከጊማሬሽ የሚያካሂደው ገና በዛሬው ምሽት ነው። እናም አመራሩን ወደ አራት ሊያስፋ ይችላል። በተቀረ ብራጋ ሶሥተኛ ሲሆን ስፖርቲንግና ማሪቲሞ አራተኛና አምሥተኛ ናቸው። በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ደግሞ በሰንበቱ ግጥሚያዎች መሪዎቹ ሁለት ክለቦች መሸነፋቸው ሻምፒዮናውን እያጠበበው ሄዷል።                                                                                                        

አንደኛው አይንድሆፈን በግሮኒንገን 3-0 ሲረታ የቅርብ ተፎካካሪው አልክማርም በተመሳሳይ ውጤት በኡትሬህት መሸነፉ ግድ ነው የሆነበት። ሁለቱ ክለቦች እኩል 45 ነጥቦች ሲኖሯቸው ሄረንፌንና ኤንሼዴ በሁለትና ሶሥት ነጥቦች ልዩነት በጣሙን ነው የቀረቧቸው። አንደኛውን ከስድሥተኛው ከአያክስ አምስተርዳም የሚለዩት አምሥት ነጥቦች ብቻ ሲሆኑ በዚሁ ክልል ውስጥ ያሉት ክለቦች በሙሉ ሻምፒዮን የመሆን ትልቅ ዕድል አላቸው።

በተረፈ የያዝነው ሣምንት የአውሮፓ ሻምፒየና ሊጋ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች የሚካሄዱበት ነው። በነገው ምሽት የስፓኙ ሬያል ማድሪድ የሲኤስኬኤ ሞስኮ እንግዳ ሲሆን የእንግሊዙ ቼልሢያ ደግሞ ኢጣሊያ ውስጥ ከናፖሊ ጋር ይገናኛል።  በብሄራዊ ደረጃ ችግር ቢገጥመውም በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግን ጥሩ ዕርምጃ ያደረገው ኢንተር ሚላንም በማግሥቱ ረቡዕ የኦላምፒክ ማርሤይ ተጋጣሚ ነው።                                    

 ሁለቱ የኢጣሊያ ክለቦች የአገሪቱ ሊጋ ተዳክሟል የሚለውን ትችት ለማስተባበል ቀላል ትግል አይጠብቃቸውም።  ለማንኛውም ሳይጠበቅ እስክዚህ የደረስው የስዊዝ ሻምፒዮን ባዝልም በዚያው ምሽት የጀርመኑን ቀደምት ክለብ ባየርን ሙንሺንን ያስተናግዳል። 

Sport Leichtathletik WM Berlin Deutschland 5000m Flash-Galerie
ምስል AP

አትሌቲክስ

የቀድሞው የቻይና የመሰናክል ሩጫ ሻምፒዮን ሊዩ-ሢያንግ በእንግሊዝ-በርሚንግሃም የአዳራሽ ውስጥ ውድድር የቤይጂንጉን የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚ የኩባ አትሌት ዳይሮን ሮብልስን በማሸነፍ የዓመቱን ጥሩ ጅማሮ ለማድርግ በቅቷል።  በ 60 ሜትር አጭር ሩጫ በወንዶች ጃማያካውያኑ ሌሮን ክላርክ፣ ኔስታ ካርተርና አሳፋ ፓውል ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል ሲያሸንፉ በሴቶች ደግሞ አሜሪካዊቱ ቲያና ማዲሰን ቀድምቷ ሆናለች።               

በ 800 ሜትር የኢትዮጵያው መሐመድ አማን ሲያሸንፍ በ 1500 ሜትርም ገ/መድህን መኮንን ሶሥተኛ ወጥቷል። በሁለት ማይል  ኬንያዊው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ የእንግሊዙን ሞ ፋራህን አስከትሎ ሲያሸንፍ ሩጫውን በአረተኛነት የፈጸመው ደግሞ ታሪኩ በቀለ ነበር። በሴቶች 1500 ሜትር ገንዘቤ ዲባባ ስታሸንፍ በ 3 ሺህ ሜትርም መሠረት ደፋር ቀዳሚ ሆናለች። ገለቴ ቡርካና መሰለች መልካሙም በ 3 ሺህ ሜትሩ ሩጫ ሶሥተኛና አራተኛ በመውጣት ግሩም ውጤት አስመዝግበዋል።

Flash-Galerie Victoria Azarenka
ምስል picture alliance/ZUMA Press

ቴኒስ

በካሊፎርኒያ የሣን-ሆሴ ኤቲፒ የቴኒስ ውድድር ትናንት በተካሄደ ፍጻሜ ግጥሚያ የካናዳው ሚሎሽ ራኦኒች ኡዝቤክ ተጋጣሚውን ዴኒስ ኢስቶሚንን በማሸነፍ ለድል በቅቷል። ካናዳዊው ወጣት ያለፈው ዓመት አሸናፊ እንደነበርም አይዘነጋም። በዶሃ የካታር ኦፕን የሴቶች ፍጻሜ ውድድር ደግሞ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነችው የቤላሩሷ ኮከብ ቪክቶሪያ አዛሬንካ የአውስትራሊያ ተጋጣሚዋን ሣማንታ ስቶሱርን በፍጹም ልዕልና 6-1,6-2 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።                                                

ድሉ ለአዛሬንካ በተከታታይ 17ኛው መሆኑ ነው። ከዚሁ ሌላ ሰንበቱን የስዊዙ ሮጀር ፌደረር አርጄንቲናዊውን ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖትሮን በማሸነፍ የሮተርዳም ባለ ድል ሲሆን ቦጎታ ላይ በተካሄደ የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያም የስፓኟ ላራ-ቬቺኖ ሩሢያዊቱን  አሌክሳንድራ ፓኖቫን ለመርታት በቅታለች።

Flash-Galerie Muhammad Ali
ምስል picture-alliance/dpa

በቡጢ ለማጠቃልለል ዝነኛው ካሲየስ ክሌያ፤ ሞሐመድ አሊ ባለፈው ሰንበት ላስ ቬጋስ ውስጥ ታዋቂ የፊልም፣ የስፖርትና የሙዚቃ ከዋክብትን ጨምሮ ሁለት ሺህ ያህል እንግዶች በተገኙበት ግብዣ ስባኛ ዓመት የልደት በዓሉን አክብሯል። ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ለታዋቂው የስፖርት ሰው በላኩት የቪዲዮ መልዕክት «መልካም ልደት ሻምፒዮን» ሲሉ ነበር የአሊን ትልቅነት በአድናቆት መለስ ብለውያስታወሱት

የአሜሪካ ፉት ቦል ሊግ ታላቅ ጂም ብራውን ደግሞ «አሜሪካ በባርነት ጀምራ በጥቁር ፕሬዚደንት አበቃች። ሞሐመድ አሊ ደግሞ የዚህ ታሪክ አንድ ትልቅ አካል ነው» ሲል ነው ጊዜ የማይሽረውን ድንቅ ስፖርተኛ ያወደሰው። የልደቱ  በዓል የተከበረው የፓርኪንሰን ሕመምተኛ የሆነውን የአሊን ሕይወት ለማወደስ በቻ ሣይሆን ለአንጎል ምርምር በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብም ለመሰብሰብ ጭምር ነበር።                                                      

ባለቤቱ ሎኒ የአሊ ትልቅ ፍላጎት ሌሎችን መርዳት መሆኑን ነው በዚሁ አጋጣሚ የተናገረችው። ሞሐመድ አሊ በዕውነትም ውትሮ ለሚያስፈራው ቡጢ እንኳ ሰብዓዊና ውብ ገጽታ ለማጎናጸፍ የበቃ ታላቅ ስፖርተኛ ነው። እኛም በጎውን ሁሉ እንመኝለታለን። ቡጢን ካነሣን  የኡክራኒያው ቪታሊ ክሊችኮ ባለፈው ቅዳሜ በዚህ በጀርመን ሚዩኒክ ውስጥ በተካሄደ ግጥሚያ የዓለም ቡጡ ካውንስል የከባድ ሚዛን ማዕረጉን በቀላሉ ለማስከበር በቅቷል።

ክሊችኮ ለድል የበቃው የብሪታኒያ ተጋጣሚውን ዴሬክ ቺሶራን በአንድ ወጥ የዳኞች ውሣኔ ነው።  ቺሶራ በበኩሉ ግን ክጨዋታው በፊት ክሊችኮን በመተኮስ፤ ከዚያም ከግጥሚያው በኋላ በተካሄደ ጋዜጣዊ ጉባዔ አኳያ በከፈተው ግብግብ ስርዓተ-ዓልባ መሆኑን አስመስክሯል። አድራጎቱ ሁሉ ለዚያውም በዙዎች በዓይን-ቁራና የሚከታተሉትን የቡጢ ስፖርት ዝና ይብስ የሚያደፈርስ ነው። ግለሰቡ በሚዩኒክ ፖሊስ ለተወሰነ ጊዜ ተይዞም ነበር።    

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

           

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ