1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከስፖርቱ ዓለም

ሰኞ፣ መስከረም 21 2005

የትናንቱ የበርሊን ማራቶን አሸናፊዎች በወንዶች ኬንያዊው ጆፍሪይ ሙታይና በሴቶች ደግሞ ኢትዮጳያዊቱ አበሩ ከበደ ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/16ICF
ምስል Reuters

የትናንቱ የበርሊን ማራቶን አሸናፊዎች በወንዶች ኬንያዊው ጆፍሪይ ሙታይና በሴቶች ደግሞ ኢትዮጳያዊቱ አበሩ ከበደ ሆነዋል። የበርሊን ወኪላችን ይልማ ሃ/ሚካኤል በተከታተለው ውድድር ላይ አርባ ሺህ ሯጮች ተሳትፈው ነበር።

በእግር ኳስ እንጀምርና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቼልሢይ እስካሁን አንዴም ሳይሸነፍ በድል ጉዞው እንደቀጠለ ነው። ክለቡ ባለፈው ሰንበት የለንደን ከተማ ተፎካካሪውን አርሰናልን 2-1 ሲያሸንፍ አመራሩን ወደ ሶሥት ነጥቦች ከፍ ማድረጉ ተሳክቶለታል። ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ በኦልድ ትሬፎርድ ስታዲዮሙ በቶተንሃም ሆትስፐር 3-2 ሲረታ ከሁለተኛ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ወርዷል። በቦታው የተተካው ሣውዝሃምፕተንን 3-1 ያሸነፈው ኤቨርተን ነው። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ማንቼስተር ሢቲይም ፉልሃምን 2-1 በመርታት በአራተኝነቱ ቀጥሏል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና በስድሥተኛ ግጥሚያውም ሲያሸንፍ ወደፊታችን ሰንበት «ኤል ክላሢኮ» ማለት ከሬያል ማድሪድ ጋር የሚደረግ የሊጉ ታላቅ ግጥሚያ የሚሻገረው ሙሉ 18 ነጥቦቹን ይዞ ነው። ባርሣ ሤቪያን 3-2 ሲያሸንፍ ኤስፓኞልን 1-0 የረታው አትሌቲኮ ማድሪድ ሁለት ነጥቦች ወረድ ብሎ በ 16 ሁለተኛ ነው። ማላጋ ደግሞ በ 14 ነጥቦች ሶሥተኛ ሆኖ ይከተላል።                                                                                        

በሌላ በኩል ጅማሮው ብዙም ያልሰመረለት ሬያል ማድሪድ ትናንት ዴፖርቲቮ ኮሩኛን 5-1 በመቅጣት እንደገና የተለመደ ጥንካሬውን ለማሳየት ችሏል። ከአምሥት ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው ድንቅ ጨዋታ ያሳየው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነበር። ሬያል በዚሁ ወደ ስድሥተኛው ቦታ ከፍ ሲል እርግጥ ከባርሤሎና ገና በስምንት ነጥቦች ዝቅ ያለ ነው። ስለዚህም መጪው የሁለቱ ቀደምት ክለቦች ግጥሚያ በተለይም ለሬያል ወሣኝ ባህርይ ይኖረዋል።

Bundesliga Eintracht Frankfurt SC Freiburg
ምስል dapd

በጀርመን ቡንደስሊጋም ሁኔታው በጣሙን ተመሳሳይ ነው። ባየርን ሙንሺን ብሬመንን 2-0 ሲያሸንፍ የእስካሁን ስድሥት ግጥሚያዎቹን በሙሉ በድል በመወጣት ግንባር ቀደም እንደሆነ ነው። ማን አሰበው፤ ከሁለተኛው ዲቪዚዮን የወጣው አይንትራኽት ፍራንክፉርትም ከአንዲት እኩል ለእኩል ውጤት በስተቀር አንዴም ሳይሸነፍ የባየርን የቅርብ ተፎካካሪ እንደሆነ ቀጥሏል። በሣምንቱ ከሁሉም በላይ ትልቁን ዕርምጃ ያደረገው ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ዶርትሙንድ ነበር። ዶርትሙንድ እጅግ ጠንካራ ጨዋታ በማሳየት ግላድባህን 5-0 ሲቀጣ አሁን ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ብሏል። አራተኛው ከዶርትሙንድ ጋር እኩል 11 ነጥቦች ያሉት ሆኖም በጎል ዝቅ ያለው ሻልከ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ ቱሪን ሮማን 4-1 በመሸኘት በአመራሩ ሲቀጥል ሣምፕዶሪያን 1-0 ያሸነፈው ናፖሊም በተመሳሳይ 16 ነጥብ ሁለተኛ ነው። ኢንተርና ላሢዮ አራት ነጥቦች ወረድ ብለው ይከተላሉ። በፈረንሣይ ሻምፒዮና ኦላምፒክ ማርሤይ በሰባተኛ ግጥሚያው ለመጀመሪያ ጊዜ ሽንፈት ቢደርስበትም ሊጋውን አሁንም በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ይመራል። ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን በ 15 ነጥቦች ሁለተኛ ሲሆን አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ ሶሥተኛው ሊዮን ነው። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ቤንፊካና ፖርቶ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።

በተቀረ ነገና ከነገ በስቲያ ረቡዕ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር የምድብ ዙር ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ጠንካሮች ከሚባሉት መካከልም ቤንፊካ ሊዝበን ከባርሤሎና፤ ፖርቶ ከፓሪስ-ሣንት-ዠርማን፤ አርሰናል ከኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ፤ ማንቼስተር ሢቲይ ከዶርትሙንድና አያክስ አምስተርዳም ከሬያል ማድሪድ ይገኙበታል።            

Berlin Marathon Gewinner Geoffrey Mutai
ምስል picture-alliance/dpa

አትሌቲክስ

39ኛው የበርሊን ማራቶን ትናንት በኬንያና በኢትዮጵያ አትሌቶች ድል ተፈጽሟል። የበርሊኑ ማራቶን በጀርመን ታላቁ ሲሆን አርባ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተሳትፈውበት ነበር። ቀደም ሲል በፕሬግራማችን መግቢያ ላይ እንደጠቀስነው የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ሃይለ ሚካኤል በስፍራው ተገኝቶ ውድድሩን ተከታትሏል።

WTA-Turnier Berlin (Feature Regenwetter)
ምስል picture-alliance/dpa

ቴኒስ

በቴኒስ የማሌዚያ-ኦፕን ትናንት በተካሄደው የወንዶች ፍጻሜ ግጥሚያ አርጄንቲናዊው ሁዋን ሞናኮ ሶሥት ሰዓት በፈጀ ጨዋታ የፈረንሣይ ተጋጣሚውን ዡሊየን ቤኔቱን በ 2-1 ውጤት ለማሸነፍ በቅቷል። የትናንቱ ድል ሞናኮን በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ ወደ አሥረኛው ቦታ ከፍ የሚያደርግ ነው።                                                                    

በቻይና-ኦፕን አንደኛ ዙር የሴቶች ነጠላ ግጥሚያዎች ፖላና ሄርሶግ ከስሎቬኒያ ሩሢያዊቱን አናስታዚያ ፓቭሉቼንኮቫን፤ ጀርመናዊቱ ዛቢነ ሊሢስኪ የስፓኟን አናቤል ሜዲናን፤ የስፓኝ ላራ ቬቺኖ ቻይናዊቱን ሼንግ ዪን፤ እንዲሁም ሶራና ሢርስቴያ ከሩሜኒያ  ስዊድናዊቱን ሶፊያ አርቪድሶንን አሸንፈዋል። በወንዶች ደግሞ ዛሬ የሩሜኒያው ማሪዩስ ኮፒል የክሮኤሺያውን ማሪን ቺሊችን ሲያሸንፍ በጃፓን-ኦፕን አንደኛ ዙርም ሉካስ ላስኮ ከስሎቫኪያ የስፓኙን አልበርት ራሞስን ረትቷል።

በቡጢ ለማጠቃለል የሩሢያው አሌክሳንደር ፖቬትኪን ባለፈው ቅዳሜ ምሽት የአሜሪካ ተጋጣሚውን ሃሢም ራህማንን በሁለተኛ ዙር በበቃን በማሸነፍ የዓለም ቡጢ ማሕበር የ WBA የከባድ ሚዛን ሻምፒዮንነቱን መልሶ አረጋግጧል። ፖቬትኪን በ 25 ግጥሚያዎች እስካሁን አልተሸነፈም።

መሥፍን መኮንን     

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ