1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከስፖርቱ ዓለም

ሰኞ፣ ኅዳር 10 2005

የአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር የያገሩ በርካታ ክለቦች የተቀረረበ ነጥብ ይዘው ለሻምፒዮንነት የሚታገሉበት እንደሆነ ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/16lmQ
ምስል Getty Images

የአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር የያገሩ በርካታ ክለቦች የተቀረረበ ነጥብ ይዘው ለሻምፒዮንነት የሚታገሉበት እንደሆነ ቀጥሏል። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ባርሤሎና በእስካሁን 12 ግጥሚያዎቹ አንዴም ሳይሸነፍ 11ኛ ጨዋታውንም በድል ሲወጣ ኮከቡ ሊዮኔል ሜሢም ለሁለተኛ የውድድር ወቅት በተከታታይ በጎል አግቢነት የክለቡ አለኝታ እንደሆነ ነው። ባርሣ ባለፈው ሰንበት ሬያል ሣራጎሣን 3-1 ሲያሸንፍ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረውም ይሄው የአርጄንቲናው ዳግማዊ ማራዶና ነበር።

ባርሤሎና ከሰንበቱ ግጥሚያ በኋላ አሁን 34 ነጥቦች አሉት። ሊዮኔል ሜሢ ገና በ 11 ግጥሚያዎች ከአሁኑ 17 ጎሎችን ሲያስቆጥር በዚህ በያዝነው ዓመት 2012 ለክለቡና ለአገሩ በጠቅላላው 78 ጎሎች ማግባቱ ነው። እናም የሊጋው ውድድር ገና ትኩስ መሆኑ ሲታሰብ በዓመቱ መጨረሻ የጀርመኑ አጥቂ ጌርድ ሙለር ከአርባ ዓመታት በፊት አስመዝግቦት የነበረውን የ 85 ጎሎች ክብረ-ወሰን እንደሚያሻሽል ከወዲሁ እርግጠኛ መሆኑ ብዙም አያዳግትም።

በሌላው አርጄንቲናዊ በዲየጎ ሢሚዮኔ አሰልጣንነት የሚመራው አትሌቲኮ ማድሪድም ትናንት ግራናዳን 1-0 ረትቶ ሲመለስ ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ በ 31 ሁለተኛ ነው። ክለቡ በዲየጎ ሢሚዮኔ ተጫዋችነት ዘመን ከ 12 ዓመታት በፊት የስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሻምፒዮን ከሆነበት ጊዜ ወዲህ እንዳሁኑ የጠነከረበት ሌላ ጊዜ አይታወስም። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድ ምንም እንኳ በበኩሉ ግጥሚያ አትሌቲክ ቢልባዎን 5-1 ቀጥቶ ቢሸኝም በ 26 ነጥቦች ሶሥተኛ እንደሆነ ነው። አሁንም ከሊጋው ግንባር-ቀደም መሪ ከባርሤሎና ስምንት ነጥቦች ይለዩታል። ሌቫንቴ አራተኛ፤ ማላጋ አምሥተኛ በመሆን ይከተላሉ።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ ማንቼስተር ሢቲይ ኤስተን ቪላን 5-0 በመቅጣት በዘንድሮው የውድድር ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ አመራሩን ሊይዝ በቅቷል። እዚህም የአርጄንቲና ኮከቦች ካርሎስ ቴቬዝና ሴርጂዮ አጉዌሮ እያንዳንዳቸው ሁለት ጎል በማስቀጠር የድል ዋስትኖች ነበሩ። ክለቡ አመራሩን ሊነጥቅ የቻለው የቅርብ ተፎካካሪው ማንቼስተር ዩናይትድ በኖርቪች ሢቲይ 1-0 በመረታቱ ነው። ሢቲይ አሁን በ 12 ግጥሚያዎች 28 ነጥቦች ሲኖሩት ማኒዩ በ 27 ይከተላል፤ ቼልሢይ ደግሞ በ 24 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው።

Fußball Bundesliga 12. Spieltag Werder Bremen - Fortuna Düsseldorf
ምስል Getty Images

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን ምንም እንኳ ከኑርንበርግ 1-1 በሆነ ውጤት ብቻ ቢለያይም አመራሩን ወደ ስምንት ነጥቦች ከፍ ማድረጉ ተሳክቶለታል። ለዚህም ምክንያቱ ሁለተኛው ሻልከ ለዚያውም በገዛ ሜዳው በሌቨርኩዝን 2-0 መረታቱ ነው። ባየርን ከ 12 ግጥሚዎች በኋላ በ 31 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ሻልክና ፍራንክፉርት በ 23 ይከተላሉ። ያለፉት ሁለት ዓመታት ሻምፒዮን ዶርትሙንድም ደከም ካለ ጅማሮ በኋላ መልሶ በመጠናከር ሲቀጥል በአራተኛው ቦታ ላይ እንደተቆናጠጠ ነው።

ሆኖም በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር በዚህ ሰንበት ትልቁን ዕርምጃ ያደረገው ከ 12ኛ ወደ ሰባተኛው ቦታ ከፍ ያለው ቬርደር ብሬመን ነበር። ብሬመን ዱስልዶርፍን 1-0 ከተመራ በኋላ ለዚያውም በጎዶሎ ሰው 2-1 ሲያሸንፍ ቡድኑ ባሳየው የመንፈስ ጥንካሬ ከደጋፊዎቹ ባሻገር አሠልጣኙ ቶማስ ሻፍም በጣሙን ነው የተደሰተው።

«ጨዋታው ከተጀመረ ብዙ ሳይቆይ ጎል ቢቆጠርብንም ቡድኑ በሁኔታው ከመታገል አልተገታም። እንዲያውም ትግሉን ይበልጥ ነው ያጠናከረው። አንድ ሰው ከሜዳ ወጥቶበት እንኳ የማጥቃት አጨዋወቱን አልተወም። ለዚህ ወኔውና ቁርጠኛ ትግሉ ደግሞ በሚገባ ተክሷል»

ቬርደር ብሬመን የረጅም ጊዜ ማኔጀሩ ቶማስ አሎፍስ ባለፈው ሣምንት ክለቡን ለቆ ወደ ቮልፍስቡርግ በመሄዱ ተረጋግቶ መጫወት መቻሉን የተጠራጠሩት ብዙዎች ነበሩ። ግን የተፈራው አልደረሰም። በነገራችን ላይ ብሬመን በፊታችን ቅዳሜ ከቮልፍስቡርግ የሚጋጠም ሲሆን የረጅም ጊዜ ማኔጀሩን አሎፍስን ጭምር ለማሸነፍ ነው የሚጫወተው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ ከላሢዮ 0-0 ቢለያይም በአራት ነጥቦች ልዩነት ሊጋውን መምራቱን ቀጥሏል። ከ 13 ግጥሚያዎች በኋላ 32 ነጥቦች አሉት። ኢንተር ሚላንም ከካልጋሪይ 2-2 በሆነ ውጤት ሲለያይ በ 28 ነጥቦች ሁለተኛ ሆኖ ይከተላል። ፊዮሬንቲና አታላንታን 4-1 ሲያሸንፍ በዚሁ ስኬቱ በናፖሊ ፈንታ በሶሥተኛው ቦታ መተካቱ ሆኖለታል። ከኤ ሲ ሚላን 2-2 የተለያየው ናፖሊ አሁን አራተኛ ነው።

በፈረንሣይ ሊጋ ውድድር ደግሞ ኦላምፒክ ሊዮን ለዚያውም አንድ ጨዋታ ጎሎት በ 25 ነጥቦች ይመራል። ዢሮንዲን ቦርዶው አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ ሁለተኛ ነው። ፓሪስ ሣንት ዠርማን በ 23 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን አንድ ጨዋታ የሚጎለው ኦላምፒክ ማርሤይም በተመሳሳይ ነጥብ አራተኛ ነው። በአጠቃላይ ከአንደኛው እስከ ሰባተኛው ቦታ ያለው ልዩነት የሶሥት ነጥቦች ብቻ ሲሆን ፉክክሩ የጠበቀ ሆኖ የሚቀጥል ይመስላል።

በኔዘርላንድ ሻምፒዮና ሊጋውን ለረጅም ጊዜ ሲመራ የቆየው የትዌንቴ ኤንሼዴ ከኡትሬኽት በ 1-1 ውጤት መወሰን ለአይንድሆፈን አመራሩን ወደ ሶሥት ነጥቦች እንዲያሰፋ በጅቷል። አይንድሆፈን ለዚህ የበቃውም በበኩሉ ግጥሚያ አዶ ዴንሃግን 6-1 ካሸነፈ በኋላ ነው። ቪቴስ አርንሃይም ሶሥተኛ፤ አያክስ አምስተርዳም አራተኛ!

Olympia London 2012 Marathon Frauen
ምስል dapd

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት ጃፓን ውስጥ ተካሂዶ በነበረው ዓለምአቀፍ የሴቶች የዮኮሃማ ማራቶን ሩጫ ኬንያዊቱ ሊዲያ ቼሮማይ በሁለት ሰዓት ከ 23 ደቂቃ ሰባት ሢኮንድ ጊዜ አሸናፊ ሆናለች። ቼሮማይ ከ 14ኛው ኪሎሜትር በኋላ አመራሩን ስትይዝ ከዚያን ወዲያ የረባ ፉክክር ሳይገጥማት ነው ከግቧ የደረሰችው። ጃፓናዊቱ ሚዙሆ ናሱካዋ ሁለተኛ ስትወጣ የፖርቱጋሏ ተወዳዳሪ ማሪሣ ባሮስ ደግሞ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽማለች።

በሌላ የአትሌቲክስ ዜና World Anti-Doping Agency ወይም በአሕጽሮት WADA በመባል የሚጠራው የዓለም ጸር-ዶፒንግ ኤጀንሲ በሕገ ውጥ መንገድ የአካል ማዳበሪያ መድሃኒቶች በሚወስዱ አጭበርባሪ ስፖርተኞች ላይ ቅጣትን ለማጥበቅ የሚበጅ የሕግ ረቂቅ በትናንትው ዕለት አቅርቧል። ሕጉ ቢጸና ዋዳ ብሄራዊ አካላት ዕርምጃ አንወስድም በሚሉበት ጊዜ ጉዳዩን እንዲከታተል ጥርጊያን ሊከፍት የሚችልም ነው። ረቂቁ በፊታችን ታሕሣስ ወር ተመክሮበት በአዲሱ ዓመት የሚጸና ሲሆን እስካሁን የሚሰራበትን የሁለት ዓመት እገዳ መቀጮ ወደ አራት ከፍ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

Formel 1 Grand Prix in Austin USA
ምስል Getty Images

ፎርሙላ-አንድ

ጀርመናዊው ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ትናንት በአውስቲን-ቴክሣስ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የነበረውን ዕድል ሳያሳካ ቀርቷል። ፌትል እሽቅድድሙን ከመጀመሪያው ተርታ ቢጀምርም በመጨረሻ ከግቡ የደረሰው በሁለተኝነት ነው። የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን አንደኛ ሲወጣ ከሰባተኛው ቦታ የተነሣው የፌትል ዋነኛ ተቀናቃኝ ፌርናንዶ አሎንሶ ሶሥተኛ ሊሆን በቅቷል።

በዚሁ የዓለም ሻምፒዮናው ውሣኔ በመጪው ሣምንት ብራዚል ውስጥ ለሚካሄደው እሽቅድድም መሸጋገሩ ግድ ነው የሆነው። በጠቅላላ ነጥብ ዜባስቲያን ፌትል አሎንሶን በ 13 የሚመራ ሲሆን አሎንሶም ገና ሻምፒዮን የመሆን ዕድሉን እንደያዘ ነው። የ 25 ዓመቱ ፌትል በመጪው ሣምንት ከቀናው ሶሥቴ አከታትሎ የዓለም ሻምፒዮን በመሆን በታሪክ የመጀመሪያው ወጣት የፎርሙላ-አንድ ዘዋሪ ይሆናል።

London 2012 Tennis Regen
ምስል Reuters

ቴኒስ

ቼክ ሬፑብሊክ ታሪካዊ በሆነ ፍጻሜ ግጥሚያ ትናንት የዴቪስ-ካፕ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች። ቼክ ሬፑብሊክ የአምሥት ጊዜዋን ሻምፒዮን ስፓኝን 3-2 በመርታት ለድል የበቃችው የ 33 ዓመቱ አንጋፋ ተጫዋቿ ራዴክ ስቴፓኔክ ኒኮላስ አልማግሮን አራት ሰዓታት ያህል በፈጀ ነርቭን የጨረሰ ጨዋታ ካሸነፈ በኋላ ነበር። በቼክ በኩል ስቴፓኔክና ቶማስ ቤርዲች ለዴቪስ-ካፕ ቡድናቸው ሲሰለፉ የስፓን ተወዳዳሪዎች ደግሞ ዴቪድ ፌሬር፣ አልማግሮ፣ ማርሤል ግራኖሌርስና ማርክ ሎፔዝ ነበሩ። ቼኮች በቀድሞዋ ቼኮዝላቫኪያ አማካይነት ላለፈው የዴቪስ-ካፕ ሻምፒዮንነታቸው የበቁት ከሰላሣ ዓመታት በፊት እንደነበር ይታወሳል።

በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የእግር ኳስ ውድድር ለማጠቃለል ከምድብ ወደ ቀጣዩ ጥሎ ማለፉ ዙር ለማለፍ በሚደረገው ፉክክር ነገና ከነገ በስቲያ ምሽት በከፊል ወሣኝ የሆኑ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በምድብ-አምሥት ውስጥ ያለፈው ሻምፒዮን የእንግሊዙ ክለብ ቼልሢይ ከመጨረሻዎቹ 16 ክለቦች አንዱ ለመሆን በወቅቱ በፕሬሚየር ሊጉ የሚታይበትን ድክመት ማስወገዱ ግድ ነው። ቼልሢይ በነገው ምሽት ከኢጣሊያው ሻምፒዮን ከጁቬንቱስ ቱሪን የሚጋጠም ሲሆን ከሁለት ሣምንት በኋላ የመጨረሻ ጨዋታውን የሚያደርገውም ከኡክራኒያው ጠንካራ ቡድን ከሻህትዮር ዶኔትስክ ነው። ሶሥቱም ክለቦች በወቅቱ ከሞላ-ጎደል እኩል ናቸው።

በምድብ-ስድሥት እኩል ዘጠኝ ነጥብ ያላቸው ቫሌንሢያና ባየርን እርስበርስ የሚገናኙ ሲሆን ማንም ያሸንፍ ማን ሁለቱም ወደተከታዩ ዙር የሚያልፉ ነው የሚመስለው። ፖርቶ፣ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን፣ ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ባርሤሎናና ያስደንቃል ሌላው የስፓኝ ክለብ ማላጋም እስካሁን ባሳዩት ጥንካሬ ከወዲሁ እንዳለፉ የሚቆጠሩ ሲሆን ቀደምት ከሚባሉት መካከል በአንጻሩ አርሰናልን ኤ ሴ ሚላንንና ማንቼስተር ሢቲይን የመሳሰሉት እንዳይከስሩ በጣም ነው የሚያሰጋቸው።

አርሰናል በምድብ-ሁለት ውስጥ የጀርመኑን ክለብ ሻልከን ተከትሎ ሁለተኛ ሲሆን ወደፊት የመዝለቅ የተሻለ ዕድል እንዲኖረው በፊታችን ረቡዕ የፈረንሣዩን ክለብ ሞንትፔሊየርን መርታቱ የሚበጀው ነው። በምድብ-አራት ውስጥ የጀርመኑን ክለብ ዶርትሙንድን ተከትሎ በሁለተንነት የሚገኘው ታላቅ ክለብ ሬያል ማድሪድም እንዲሁ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ከማንቼስተር ሢቲይ ቢቀር እኩል-ለእኩል መውጣቱ ይጠቅመዋል። ለማንኛውም ከሁለት ሣምንት በኋላ የሚካሄዱት የመጨረሻ ግጥሚያዎች የምድቡ ዙር ተጠቃሎ ወደ ጥሎ ማለፉ ደረጃ የሚያልፉት 16 ክለቦች ማንነት በሙሉ የሚለይባቸው ይሆናሉ።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ