1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከስፖርቱ ዓለም

ሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2005

በዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ መድረክ የትናንቱ ሰንበትም ቀደም እንዳሉት ሁሉ የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡበት ሆኖ አልፏል።

https://p.dw.com/p/18GDt
ምስል dapd

በሮተርዳም ማራቶን ጥላሁን ረጋሣ አንደኛ ሲወጣ ሩጫውን በሁለተኝነት የፈጸመውም ኢትዮጵያዊው አትሌት ጌቱ ፈለቀ ነበር። ጥላሁን ረጋሣ በሁለተኛ የማራቶን ሩጫው ግሩም በሆነ የሁለት ሰዓት ከአምሥት ደቂቃ ከ 38 ሤኮንድ ጊዜ ከግቡ ሲደርስ ያሸነፈውም የቅርብ ተፎካካሪዎቹን በ 39ኛው ኪሎሜትር ላይ አምልጦ ከሄደ በኋላ ነው።

ጥላሁን ረጋሣ ባለፈው ዓመት ቺካጎ ላይ ባደረገው የመጀመሪያ የማራቶን ተሳትፎ ከትናንቱ 11 ሤኮንዶች ብቻ ዘግየት ያለ ጊዜ ማስመዝገቡ ይታወሳል። በዚሁ ኢትዮጵያውያን በተከታተሉበት ሩጫ ሶሥተኛ የወጣው ኬንያዊው ሣሚይ ኪትዋራ ነበር። በሴቶች በአንጻሩ ድሉ የኬንያ ሲሆን ጄሚና ጄላጋት አሸናፊ ሆናለች። አበበች አፈወርቅ ሁለተኛ ስትወጣ የኔዘርላንዷ ተወዳዳሪ ሂልዳ ኪቤትም ሶሥተኛ ሆናለች።

የውድድሩ አዘጋጆች በወንዶቹ ሩጫ አዲስ ክብረ-ወሰን ለማየት ተሥፋ ቢያደርጉም ይሄው በሙቀትና ነፋሻ አየር ሳቢያ ዕውን ሊሆን ሳይችል ቀርቷል። የሮተርዳም ማራቶን ክብረ-ወሰን ከአራት ዓመታት በፊት በሁለቱ ኬንያውያን በደንካን ኪቤትና በጀምስ ኩዋምባይ የተመዘገበው የሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከ 27 ሤኮንድ ጊዜ ነው።

Haile Gebrselassie gewinnt Berlin-Marathon
ምስል AP

በትናንትናው ዕለት አውስትሪያ ውስጥም የቪየና ማራቶን ሩጫ ሲካሄድ በወንዶች ኬንያውያን ከአንድ እስከ አምሥት በመከታተል በታላቅ ልዕልና አሸናፊ ሆነዋል። ሆኖም ያስመዘገቡት ጊዜ ያን ያህል ጠንካራ የሚባል ሊሆን አልቻለም። አሸናፊው ሄንሪይ ሱጉት ሩጫውን በሁለት ሰዓት ከስምንት ደቂቃ ከ 19 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም ይህም ከሮተርዳሙ ሶሥተኛ ውጤት ላይ እንኳ የደረሰ አልነበረም። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ ኤዴዎ ማሞ ስድሥተኛ ወጥቷል።

በሴቶች ማራቶንም ኬንያዊቱ ፍሎሜና ቼዬች ስታሸንፍ መስከረም አሰፋና ኢየሩሣሌም ኩማ ሁለተኛና ሶሥተኛ በመሆን ግሩም ውጤት አስመዝግበዋል። የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች በማራቶን ሩጫ ባለፉት ወራት እየጠነከሩ መምጣታቸው የሚታወቅ ነው። ቪየና ላይ ከ 42ቱ ኪሎሜትር ሌላ ግማሽ ማራቶን ውድድርም ሲካሄድ ሃይሌ ገ/ስላሤ በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ አሸናፊ ሊሆን በቅቷል። ኬንያዊው ሆሤያ ኪፕኬምቦይ ሁለተኛ ሲወጣ ሶሥተኛ የሆነው ደግሞ መኳንንት አየነው ነው። በሴቶች ደቡብ አፍሪቃዊቱ ታኒት ማክስዌል አሸናፊ ሆናለች።

Fußball Bundesliga 29. Spieltag Bayern München gegen 1. FC Nürnberg
ምስል picture-alliance/dpa

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር ከጀርመኑ ክለብ ከባየርን ሙንሺን ቀጥሎ ማንቼስተር ዩናይትድና ባርሤሎናም ከሰንበቱ ድላቸው በኋላ ሻምፒዮንነታቸውን ለማረጋገጥ በጣሙን ተቃርበዋል። ባየርን ሙንሺን ባለፈው ሣምንት የቡንደስሊጋው ውድድር ሊያበቃ ገና ስድሥት ጨዋታዎች ቀርተው በሃያ ነጥቦች ልዩነት ሻምፒዮንነቱን በአስደናቂ ሁኔታ ማረጋገጡ የሚታወስ ነው። ቡድኑ ባለፉት አራትና አምሥት ዓመታት ውስጥ የዘንድሮውን ያህል ጠንክሮ የታየበት ጊዜ አይታወስም።

ክለቡ በዚህ ሣምንት አጋማሽ በጀርመን ፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያውን የሚያካሂድ ሲሆን ከዚያም በሣምንቱ ባርሤሎናን ከመሰለ ታላቅ ቡድን ጋር የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ይጠብቀዋል። ባየርን ዘንድሮ ከነዚህ ውድድሮች ቢቀር አንዱን ዋንጫ መጠቅለል መቻሉ በብዙዎች የሚጠበቅ ነው። ለነገሩ ጥቂት ከቀናው በሶሥቱም ውድድሮች ቁንጮ መሆን የማይችልበት ምክንያትም የለም።

በሌላ በኩል ጥንካሬው የራሱ ማየል ወይም የሊጋው መዳከም ይሁን አይሁን ጉዳዩ አንዳንድ ታዛቢዎችን ማነጋገሩ አልቀረም። የክለቡ ፕሬዚደንት ኡሊ ሄነስ ራሱ ትልቅ በጀርመን ቡንደስሊጋ ውስጥ ዘንድሮ ሰፊ የብቃት ልዩነት መኖሩን በእርግጠንነት ነው የሚናገረው። ለማንኛውም ቡንደስሊጋው ውስጥ ባርሤሎናና ሬያል ማድሪድ የዋንጫውን ዕድል ለብቻቸው ይዘው ዓመታት ያሳለፉበት የፕሪሜራው ዲቪዚዮን ሁኔታ እንዳይፈጠር ስጋት ያደረባቸው ጥቂቶች አይደሉም።

ወደተቀሩት ሊጋዎች እንሻገርና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ሰንበቱን ስቶክ ሢቲይን 2-0 በመርታት ሻምፒዮንነቱን ለማረጋገጥ ጠቃሚ ዕርምጃ አድርጓል። ዩናይትድ በ 32 ግጥሚያዎች 80 ነጥቦች ሲኖሩት ማንቼስተር ሢቲይ በ 15 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። እርግጥ ማንቼስተር ሢቲይ በትናንቱ የፌደሬሺን ዋንጫ የ FA ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ የተነሣ አንድ ጨዋታ ይጎለዋል። ቢሆንም ከእንግዲህ ማኒዩ ላይ ለመድረስ ያለው ተሥፋ የመነመነ ነው።

ማንቼስተር ሢቲይ በሌላ በኩል በፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ትናንት ቼልሢይን 2-1 በማሸነፍ ለፍጻሜ መድረሱ ተሳክቶለታል። የዋንጫ ተጋጣሚው አንድ ቀን ቀደም ሲል ሚልዎልን 2-0 አሸንፎ የነበረው ዊጋን አትሌቲክ ነው። እናም ማንቼስተር ሢቲይ የፕሬሚየር ሊጉን ሻምፒዮንነት መድገሙ ቢቀርበት የፌደሬሺኑን ዋንጫ የማግኘት ትልቅ ዕድል ነው ያለው። በሊጉ ውድድር በጎል አግቢነት የሊቨርፑሉ ሉዊስ ሱዋሬስ 22 አስቆጥሮ የሚመራ ሲሆን የማንቼስተር ዩናይትድ አጥቂ ሮቢን-ፋን-ፐርሢ በሃያ ግቦች ሁለተኛ ነው።

Fußball Champions League Real Madrid gegen Galatasaray Istanbul
ምስል picture-alliance/dpa

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ቀደምቱ ባርሤሎና ሊዮኔል ሜሢንና ሌሎች ኮከቦቹን ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያቸው እንዲያገግሙ ቢያሳርፍም በተቀያሪ ተጫዋቾች ሣራጎሣን 3-0 ማሸነፉ ሆኖለታል። ሁለተኛው ሬያል ማድሪድም ቢልባዎን በተመሳሳይ ውጤት ሲረታ ባርሣ በ 13 ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ከሬያል ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሶሥተኛው አትሌቲኮ ማድሪድ ነው። በጎል አግቢነት የባርሣው ሊዮኔል ሜሢ እስካሁን 43 በማስቆጠር አቻ የለሽ ሆኖ ሲቀጥል የሬያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በ 31 ና የአትሌቲኮው ራዳሜል ፋልካኦ በ 24 በርቀት ተከታዮቹ ናቸው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ሻምፒዮናው ከለየለት ከሣምንት በኋላ ፉክክሩ ያተኮረው ለአውሮፓ ሊግ ውድድር ተሳትፎ ለመብቃትና ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ላለመከለስ በሚደረገው ትግል ላይ ነበር። ሻምፒዮኑ ባየርን ሙንሺን ኑርንበርግን 4-0 እንዲሁም ሁለተኛው ዶርትሙንድ ፉርትን 6-1 ማሸነፋቸው ለመጪዎቹ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያዎች የልምምድን ያህል ሆኖ ነው የታየው። ሁለቱም ክለቦች ጥንካሬ አሳይተዋል።

በአውሮፓው ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ የማክሰኞና የረቡዕ ሣምንት ዶርትሙንድ ከሬያል ማድሪድና ባየርንም ከባርሤሎና የሚጋጠሙ ሲሆን የጀርመን ወይም የስፓኝ የእግር ኳስ ጥበብ ያሸንፍ በጊዜው የሚታይ ይሆናል። ለጀርመን ግን ከወዲሁ ሁለት ክለቦቿ ለሻምፒዮና ሊጋው ግማሽ ፍጻሜ መድረሳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ይህ ራሱ ትልቅ ዕርምጃ ሆኖ የሚታይ ነው። በአንጻሩ ሻምፒዮናው ሊጋ በአጭሩ ለተቀጩት ለእንግሊዝና ለኢጣሊያ ክለቦች ዘንድሮ የቁጭት መሆኑ አልቀረም።

Champions League Achtelfinale 2013 Valencia CF Paris St Germain
ምስል Getty Images

ወደ ቀደምቱ ሊጋዎች ውድድር እንመለስና በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ስድሥት ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ የቅርብ ተፎካካሪው ኦላምፒክ ማርሤይ ከሊል በእኩል ለእኩል ውጤት በመወሰኑ አመራሩን ወደ ዘጠኝ ነጥቦች ሊያሰፋ በቅቷል። ቱሉዝን 3-1 የረታው ኦላምፒክ ሊዮን ሶሥተኛ ነው። በጎል አግቢነት የፓሪሱ ቀደምት ክለብ አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች 26 አስቆጥሮ ይመራል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አም ናፖሊና ኤ ሢ ሚላን እኩል ለእኩል መለያየታቸው ለጁቬንቱስ በጅቷል። ጁቬንቱስ አንድ ግጥሚያ ቢጎለውም በወቅቱ በስምንት ነጥቦች ልዩነት አንደኛ ነው። በጎል አግቢነት 22 ያስቆጠረው የናፖሊው ኤዲንሶን ካባኒ ይመራል።

በኔዘርላንድ የክብር ዲቪዚዮን ደግሞ ቀደምቱ አያክስ አምስተርዳም ከአምሥት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይንድሆፈንን 3-2 በማሸነፍ አመራሩን ወደ አምሥት ነጥቦች ማስፋቱ ሰምሮለታል። ውድድሩ ሊጠቃለል አራት ግጥሚያዎች ሲቀሩ አርንሃይም ሁለተኛ ነው፤ አይንድሆፈን አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ በሶሥተኝነት ይከተላል። የሊጋው ቀደምት ጎል አግቢ 30 ያስቆጠረው የአርንሃይሙ አጥቂ ዊልፍሪድ ቦኒይ ነው።

Formel Eins Großer Preis von China 2013
ምስል picture-alliance/dpa

በትናንትናው ዕለት ሻንግሃይ ላይ የተካሄደው የቻይና የፎርሙላ-አንድ ዓለምአቀፍ እሽቅድድም አሸናፊ የፌራሪው ዘዋሪ ፌርናንዶ አሎንሶ ሆኗል። ድሉ ለአሎንሶ 31ኛው የግራን-ፕሪ ድል መሆኑ ነው። የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮነን ሁለተኛ ሲወጣ የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተንም እሽቅድድሙን በሶሥተኝነት ፈጽሟል። ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል ምንም እንኳ ከዘጠነኛ ቦታ ተነስቶ ወደፊት ቢራመድም በመጨረሻ በአራተኝነት መወሰኑ ግድ ነው የሆነበት።

እሽቅድድሙ ለዘንድሮው የውድድር ወቅት ሶሥተኛው ሲሆን በመጀመሪያው ራይኮነንና በሁለተኛውም ፌትል አሸናፊ እንደነበሩ ይታወሳል። በአጠቃላይ ነጥብ ፌትል በ 52 ነጥቦች አንደኛ ሲሆን ራይኮነን በ 49 በሁለተኝነት ይከተላል፤ ፌርናንዶ አሎንሶም በ 43 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው።

Flash-Galerie Sport Jahresrückblick 2010
ምስል AP

አሜሪካዊው ጆን ኢስነር ትናንት ሂዩስተን ላይ ተካሂዶ የነበረው ዓለምአቀፍ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ አሸናፊ ሊሆን በቅቷል። ኢስነር ለድል የበቃው የስፓኝ ተጋጣሚውን ኒኮላስ አልማግሮን ጠንካራ በሆነ አጨዋወት በሁለት ምድብ ጨዋታ 6-3,7-5 በመርታት ነው። በፖላንድ-ካቶቪትሤ በተካሄደ የዓለም ቴኒስ ማሕበር የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ኢጣሊያዊቱ ሮቤርታ ቪንቺ የቼክ ተጋጣሚዋን ፔትራ ክቪቶቫን 7-6,6-1 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።ድሉ ቪንቺን በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ወደ 12ኛው ቦታ ከፍ የሚያደርግ ነው።

ሞሮኮ-ካዛብላንካ ላይ በተካሄደ የወንዶች ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ የስፓኙ ቶሚይ ሮብሬዶ የደቡብ አፍሪቃ ተጋጣሚውን ኬቪን አንደርሰንን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 በማሸነፍ ለአሥረኛ የውድድር ድሉ በቅቷል። በተቀረ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነው ሰርቢያዊ ኖቫክ ጆኮቪች በእገሩ ላይ ከደረሰበት ጉዳት ለማገገም በመታገል ላይ ሳለ በዚህ ሣምንት የሞንቴ ካርሎ ማስተርስ ውድድር መሳተፍ መቻሉ እያጠያየቀ ነው።

በቡጢ ለማጠቃለል የዓለም የቡጢ ማሕበር WBA የቀላል ክብደት ሻምፒዮን የኢንዶኔዚያው ክሪስ ጆን ትናንት ጃካርታ ላይ ጃፓናዊ ተጋጣሚውን ሣቶሺ ሆሶኖን በማሸነፍ ክብሩን እንዳስጠበቀ ሊቀጥል ችሏል። እስካሁን ተሸንፎ የማያውቀው ክሪስ በሶሥተኛው ዙር ላይ በሆሶኖ አናት ተመትቶ በዓይኑ አጠገብ በደረሰበት ጉዳት ለጊዜውም ቢሆን ማዕረጉን የማጣት አደጋ ላይ ደርሶ ነበር። ሆኖም የ 33 ዓመቱ ኢንዶኒዚያዊ ለ 18ኛ ጊዜ ሻምፒዮንነቱን ሊያስከብር በቅቷል።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ