1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከቅኝ ግዛት ወደ ተወዳጅ አጋርነት

ቅዳሜ፣ መጋቢት 24 2008

ለረዥም ጊዜ ተቀዛቅዞ የነበረው የቶጎ እና የጀርመን ግንኙነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነቃቃት ጀምሯል። ፖለቲከኞች እና ባለ ሐብቶች በሁለቱ ሃገራት ተባብሮ የመሥራቱ እንቅስቃሴ አጀማመሩ ጥሩ በመሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል። ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ቶጎ የጀርመን የቀድሞ ቅኝ ግዛት ነበረች።

https://p.dw.com/p/1IO9V
Togo Außenminister Robert Dussey und Frank-Walter Steinmeier
ምስል Imago/ZUMA Press

ከቅኝ ግዛት ወደ ተወዳጅ አጋርነት

የጀርመን ምክር ቤት አባላት እና የኢኮኖሚ ልዑካን በሚቀጥለው ሣምንት ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ትንሽ ሀገር ቶጎን ይጎበኛሉ። ቶጎ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1884 እስከ 1914 ድረስ በነበሩት 30 ዓመታት፥ በዘመኑ በዘውዳዊ አገዛዝ ትመራ የነበረችው ጀርመን ቅኝ ግዛት ነበረች። ዛሬም ድረስ ታዲያ የጀርመን ቶጎን ቅኝ አገዛዝ ዘመን ለመመስከር በሚመስል አስደናቂው የያኔው አገረ-ገዢ ቤተ-መንግሥት ሕንፃ ደረቱን ለምዕራብ አፍሪቃዊቱ ፀሐይ ገልብጦ በመዲናይቱ ሎሜ ተገሽሯል።

ቶጎ እና ጀርመን በቅኝ አገዛዝ ዘመን
ቶጎ እና ጀርመን በቅኝ አገዛዝ ዘመንምስል Getty Images/Hulton Archive/Three Lions

ያኔ በቅኝ አገዛዙ ዘመን ቶጎ በጀርመን «ለአብነት የምትጠቀስ ቅኝ ግዛት» እየተባለች ነበር የምትጠራው። በወቅቱ የሀገሬው ሰዎች የተዳረጉበት የግዳጅ ሥራ እና ይከፍሉት የነበረው ከፍተኛ ግብር ቅኝ ግዛቱን በጀርመን ዐይን እጅግ አጓጊ አድርጎት ነበር። ያ ካከተመ ከ100 ዓመት በላይ በተቆጠረበት በአሁኑ ጊዜ ግን በሎሜ ጎዳናዎች ስለያኔው ቅኝ ገዢ ጀርመን መጥፎው አይሰማም። ሎሜ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የጀርመኑ ጎተ የባሕል ተቋም ኃላፊ ኤደም አቶግቤ፦

«የጀርመን ቅኝ አገዛዝ የዛሬ ስንት እና ስንት ዓመት አክትሞለታል። በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎችም በአሁኑ ጊዜ እምብዛም አይታዩም። የአሁኑ ዘመን ወጣቶችም ስለዛ ዘመን ቅኝ አገዛዝ ያን ያኽል የሚያውቁ አይመስለኝም። ስለዛ ዘመን የሚያወሩ ሰዎች በዛን ወቅት ስለነበረው ዝርዝር መረጃ የላቸውም። እነሱ ስለጀርመናውያኑ የሚያውቁት ከዚያን ጊዜ ወዲህ ስላለው ቀና ነገር ብቻ ነው ነው። ለእነሱ ጀርመኖች ትጉህ፤ ጥብቅ፣ ታታሪ፣ ለመርኅ የሚገዙ ናቸው። ሲመስለኝ ይኽ የሆነው ከሌሎች ቅኝ ገዢዎች ጋር በማነጻጸር ነው።»

እንደ ኃላፊው ከሆነ፦ የዘመኑ የቶጎ ወጣቶች ስለ ያኔው የቅኝ አገዛዝ ዘመን እምብዛም አለማውራታቸው ጀርመን ቶጎን ከ30 ዓመታት በላይ ቅኝ ስላልገዛቻት ብቻ አይደለም። የጀርመንን እግር ተከትላ ቅኝ አገዛዙን የተረከበችው ሌላኛዋ አውሮጳዊት ሀገር ፈረንሣይ የቶጎ ቆይታዋ እጅግ ጥላ ያጠላበት በመሆኑም ጭምር እንጂ።

ቶጎ ነፃነቷን የተቀዳጀችው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1960 ነው። ወቅቱ የጀርመን ቶጎ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የያዘበት ነበር። በተለይ በ70ዎቹ እና በ80ዎቹ ዓመታት የጀርመን እና የቶጎ መቀራረብ ጠንከር ብሎ የወጣበት ነበር። በወቅቱ የቶጎ አምባገነን መሪ ኛሲንግቤ ኢያዴሜ እና በጀርመን የባየርን ግዛት ጠቅላይ ሚንሥትር የነበሩት ፍራንትስ ዮሴፍ ሽትራውስ መካከል ወዳጅነቱ ላቅ ያለ ነበር። እንደውም የባየርኑ ጠቅላይ ሚንሥትር ቶጎን ለጀርመን እጅግ ጠቃሚ የማዕዘን ደንጊያ በማለት ነበር የሚጠሯት።የቀድሞ ቅኝ ግዛት ቶጎንም «የአፍሪቃ ማሳያ» ሲሉ ያንቆለጳጵሷትም ነበር።

እውነታው ግን ከገበሬ ቤተሰቦች የወጡት እና ቶጎን ለ40 ዓመታት ግድም ቀጥቅጠው የገዟት ፕሬዚዳንት ኛሲንግቤ ኢያዴሜ ወደ ሥልጣኑ መፈንቅለ-መንግሥት አድርገው በአቋራጭ መምጣታቸው ነው።

ፍራንትስ ዮሴፍ ሽትራውስ
ፍራንትስ ዮሴፍ ሽትራውስምስል picture-alliance/nph

የያኔው የባየርኑ ባለሥልጣን ወደ ቶጎ ሲያመሩ ቅልጥ ባለ የቶጎ መንግሥት ድግስ እና የሚዳቋ አደን ላይ በተደጋጋሚ ቢታደሙም በወቅቱ የማያወዛግቡ አልነበሩም ማለት አይቻልም። በአንድ ወቅት እንደውም እዛው ቶጎ ሳሉ «እኛ ጥቁሮች መደጋገፍ አለብን» ሲሉ ፕሬዚዳንቱን በቀልድ መልክ ወረፍ ማድረጋቸው ይነገርላቸዋል።

ከድኅረ ቅኝ አገዛዝ ማግስት አንስቶ ጦፎ የነበረው የጀርመን እና የቶጎ ግንኙነት በ1990ዎቹ መንደርደሪያ ላይ መቀዛቀዝ ታይቶበት ነበር። የሀገሪቱን ሕዝብ ሠጥ ለጥ አድርገው ይገዙ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኛሲንግቤ ኢያዴሜ መንግሥት ይፈጽም የነበረው የመብት ረገጣ እና በሀገሪቱ የታየው የዲሞክራሲ ዕጦት ለረጅም ጊዜ ጀርመን ይበልጥ ለመቀራረብ ታደርግ የነበረው ጥረት እንዲገታ አድርጎታል።

እንደ ጎርጎሪዮስ አጣጠር ከ2005 ዓመት ጀምሮ ግን የቀድሞው አምባገነን ልጅ የሆኑት ፎር ኛሲንግቤ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሻሻል መታየቱ የጀርመን እና የቶጎ ግንኙነት እንደ አዲስ እንዲቃቃ ቃቃ አድርጓል። ሁለቱ ሃገራት በፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ዘርፍ ግንኙነታቸውን ማጠናከር ጀምረዋል። የቶጎ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሮበርት ዱሴ

«መዋዕለ-ንዋይ አፍሳሾችን እጃችንን ዘርግተን ነው የምንቀበላቸው። ፈፅሞ አይፀፀቱም።»

የቶጎ ፕሬዚዳንት ፎር ኛሲንግቤ በትረ-ሥልጣኑን የጨበጡት የአምባገነኑ አባታቸው ናሲንግቤ ኢያዴሜ መሞትን ተከትሎ ነበር። በወቅቱ በነበረው ተቃውሞ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን የለቀቁ ሲሆን፤ ብዙም ሳይቆይ በተከናወነው ምርጫ ግን አወዛጋቢ ቢሆንም አሸንፈው የቶጎ ፕሬዚዳንት መሆን ችለዋል።

የቶጎ ወደብ በመዲናዪቱ ሎሜ
የቶጎ ወደብ በመዲናዪቱ ሎሜምስል picture alliance/Godong/P. Deloche

ጀርመን ከቶጎ ጋር ለ20 ዓመታት ግድም ተቋርጦ የነበረውን የልማት ትብብርን ዳግም የጀመረችውም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 ነበር። ሀገሪቷንም የጀርመን የልማት ትብብር ሚንሥትር ዶክተር ጌርድ ሙይለር ከታኅሣሥ 24 እስከ 26 ድረስ ለሦስት ቀናት ጎብኝተዋል።

ሚንሥትሩ በጉብኝታቸው ወቅት የቶጎ አስፈላጊነትን አስረግጠው ተናግረዋል። «ቶጎ በምዕራብ አፍሪቃ የተረጋጋች አንዲት ሀገር ናት። ያ በዚሁ መቀጠል አለበት» ብለዋል። እንደ ሚንሥትሩ አባባል ቶጎ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ኑሮዋቸው እንዲሻሻል ጀርመን ትጥራለች። «የተሻለ ትምህርት እንዲስፋፋ፣ በግብርናው ዘርፍ የበለጠ ተሳታፊነት እንዲጎለብት፣ በኢኮኖሚው ላይ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው እንተባበራለን» ሲሉም የልማት ሚንሥትሩ ተደምጠዋል።

በእርግጥም የጀርመናውያን መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች የቶጎ እንቅስቃሴያቸው እየተጠናከረ እንዲመጣ ሁኔታዎች እንደተመቻቹለት ይነገርለታል። ከቅርብ ዓመታት አንስቶ እያደገ የመጣው የቶጎ ኢኮኖሚ በ2016 ዓመት 4,9 ከመቶ እንደሚሆን የዓለም ባንክ ተንብዮዋል። ጥልቅ የባሕር ወደቦች እና የአየር መንገዶች ግንባታን ጨምሮ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እንዲቀላጠፍ አጋዥ የሆኑት መሠረተ-ልማት አውታሮች ይዘታቸው ጥሩ እንደሆነም ተገልጧል። የጀርመን ኩባንያዎች ቶጎ ውስጥ ስኬታማ ናቸውም ተብሏል።

ያም ብቻ አይደለም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የቶጎ ወጣቶች ለጀርመን እና የጀርመንኛ ቋንቋ ፍላጎታቸው ከፍ እያለ መምጣቱን በመዲናይቱ የሚገኘው የጀርመኑ ጎተ የባሕል ተቋም ኃላፊ ተናግረዋል።

የጀርመኑ ጎተ የባሕል ተቋም በሎሜ
የጀርመኑ ጎተ የባሕል ተቋም በሎሜምስል Goethe-Institut/Michael Friedel

«ከቅርብ ጊዜ አንስቶ በጎቷ የባሕል ተቋማችን የጀርመንኛ ቋንቋ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። በየዓመቱ እስከ 1600 የሚደርሱ ተማሪዎች አሉን። ፍላጎቱ በየጊዜው እየጨመረ ነው። ተማሪዎቻችን ለጀርመንኛ ቋንቋ ፍላጎቶቸው ከፍተኛ ነው። አንዳንዶቹ ተማሪዎች ጀርመን ሀገር ሄደው መማር ነው ግባቸው። በጀርመን የቤተሰብ ውኅደት ሕግ መሠረት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ቋንቋውን የሚያጠኑም አሉ።»

በዚህ የአውሮጳው የመጸው ወራት በሚቀጥለው ሣምንት ወደ ቶጎ የሚያቀኑት የጀርመን ልዑካን ጉብኝት በቶጎ እና በጀርመን መካከል እንደ አዲስ እያበበ ለመጣው ግንኙነት ይበልጥ አጋዥ እንደሚሆን ይጠበቃል። የጀርመን ምክር ቤት አባላት እና የኢኮኖሚ ልዑካን በቶጎ የሚጠብቃቸው የጋራ አውደ-ርእይም «በቶጎ እና በጀርመን መካከል የትብብር መጸው» የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ከረዥም ጊዜ በኋላ ከስሞ የነበረው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ዳግም ማበብን የሚያመላክተውን አውደ-ርእይ ኤደም አቶግቤ «የወደፊቱን ቀና ነገር መመልከት የሚያስችል አውደ-ርእይ ይመስለኛል» ሲሉ ገልጠውታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ