1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከቡዳፔስት ወደ ሙኒክ

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 5 2007

ቅጥልጥሉ ባቡር በአልፕስ ተራራዎች ስር እየተምዘገዘገ እና እየተወረወረ በደረቱ ይሳባል። ምሽቱ ለዐይን ያዝ ሲል ባቡሩ ወደ ሊንስ እና ዛልስቡርግ እየገሰገሰ ነው። አሁን ሙኒክ ዋናው የባቡር ጣቢያ ደርሷል። ስለጨለመ ግን ስጦታዎችን የሚያከፋፍሉ፣ «እንኳን ደህና መጣችሁ» የሚሉ የከተማይቱ ነዋሪዎች የሉም። በእነሱ ፈንታ ፖሊሶች ተደርድረዋል።

https://p.dw.com/p/1GTtf
Budapest nach München Passkontrolle Flüchtlinge Zug Bahnhof
ምስል DW/Ben Knight

[No title]

«ባለፈው ሳምንት ተግሬዋለሁ። ጀርመንም በሌሎች ሃገር ለሚኖሩ በርካታ ሰዎችም ተስፋ የሚያደርጉባት ሀገር በመሆንዋ ደስተኛ ነኝ። ታሪካችንን መለስ ብሎ ለቃኘው ይኽ እጅግ ዋጋ ያለው ነገር ነው።» ሲሉ የተናገሩት የጀርመን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ናቸው። በርካታ ስደተኞች ወደ ጀርመን መትመማቸውን ተከትሎ ነበር ሜርክል ባለፈዉ ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይኽን የተናገሩት።

መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በርሊን ላይ ይህን ጋዜጣዊ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት ሶሪያዊው ሙስጣፋ ከሐንጋሪ ቡዳፔስት ወደ ጀርመን ሙኒክ በሚምዘገዘገው ባቡር ዉስጥ በሚገኘዉ ሪስቶራንት ዉስጥ ተቀምጦ በመጓዝ ያል ነበር። ደማስቆስ ውስጥ ፖሊስ የነበረው ሙስጣፋ ባቡሩ ውስጥ ከሚገኘው ምግብ ቤት የዶሮ አሩስቶ ከጥቂት ሰላጣ ጋር ለመብላት 9 ዩሮ መክፈል እንዳለበት ሲያውቅ ግን ማመን አልቻለም። ባቡሩ ላይ ለተሳፈሩት ሌሎች ሶሪውያን፣ ኢራቃውያን እና አፍጋኒስታውያን ስደተኞች በአውሮጳ የኑሮ ውድነቱንም እንደሚጋፈጡት ከወዲሁ ሳይገለጥላቸው አልቀረም። ድንገት ባቡሩ ላይ ሦስት ፖሊሶች ተሳፈሩ። የሐንጋሪ፣ የኦስትሪያ እና የጀርመን ፖሊስ ናቸው።

ፖሊሶቹ ተሳፋሪ ስደተኞቹ መታወቂያቸው አለያም የጉዞ ሠነዳቸውን እንዲያሳዩ ይጠይቃሉ። ከዓሊ በስተቀር አንድም ሰው እንግሊዘኛም ጀርመንኛም የሚያውቅ ያለ አይመስልም። ኢራቃዊው ዓሊ ኑሮው በኦስትሪያ መዲና ቪዬና ነው። ወደ ሐንጋሪ ቡዳፔስት የመጣው የአክስቱ ልጅን ለመርዳት እንደሆነ ይናገራል።

«የአክስቴ ልጅ ደወሎልኝ ነው የመጣሁት። የአክስቴ ልጅ፦ ቡዳፔስት ከገባሁ ዘጠኝ ቀኔ ነው፣ ገንዘብ የሚባል ነገር የለኝም፣ ለኹለት ቀናትም ምግብ በአፌ አልዞረም አለኝ። ከዚያ በሚቀጥለው ቀን ተሳፍሬ ወደ ቡዳፔስት መጣሁ። እናም ለመርዳት ሞከርኩ። ከእሱ ጋር ሦስት ጓደኞቹም ነበሩ። ለሁሉም ምግብ ገዛሁላቸው። ብዙ ግን ላደርግላቸው አልቻልኩም፤ ምክንያቱም እኔ እራሴ በአሁኑ ወቅት ሥራ የለኝም።»

ስደተኞቹ ከባቡር ወጥተው፤ የደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች ከአጠገባቸው ቆመውn
ስደተኞቹ ከባቡር ወጥተው፤ የደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች ከአጠገባቸው ቆመውምስል Getty Images/AFP/A. Messinis

ዓሊ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2007 ዓም ጀምሮ ኑሮው ቪዬና ከተማ ውስጥ ነው። የዛሬ ስምንት ዓመት ግድም ወደ ኦስትሪያ የመጣውም የቤተሰቡ አባላትን በጦርነት ካጣ በኋላ ነው።

«ቤተሰቦቼ በአጠቃላይ ቪዬና ነው ያሉት። እናቴ፣ ወንድሜ እና እህቶቼ እዛው ቪዬና ናቸው። አባቴ እና ወንድሜ በ2007 ዓም በጦርነት ተገድለዋል። ከእዛ በኋላ ነው ወደ አውሮጳ የተሰደድኩት»

ዓሊ መላ ቤተሰቡ እስኪሰባሰቡ ድረስ መታገስ አለበት። ዛሬ የአክስቱ ልጅ በዚህኛው ባቡሩ ላይ መሳፈር አልተሳካለትም። ሆኖም በሚቀጥለው ባቡር ሊሳፈር እንደሚችል ዓሊ ተስፋ ሰንቋል።

ስደተኞች ሐንጋሪ ሮስኬ ውስጥ
ስደተኞች ሐንጋሪ ሮስኬ ውስጥምስል Reuters/M. Djurica

ቅጥልጥሉ ባቡር በአልፕስ ተራራዎች ስር እየተምዘገዘገ እና እየተወረወረ በደረቱ ይሳባል። ምሽቱ ለዐይን ያዝ ሲል ባቡሩ ወደ ሊንስ እና ዛልስቡርግ እየገሰገሰ ነው። አሁን ሙኒክ ዋናው የባቡር ጣቢያ ደርሷል። ስለጨለመ ግን ስጦታዎችን የሚያከፋፍሉ፣ «እንኳን ደህና መጣችሁ» የሚሉ የከተማይቱ ነዋሪዎች የሉም። በእነሱ ፈንታ ሙሉ የፖሊስ ደንብ የለበሱ ፖሊሶች ተደርድረዋል። ፖሊሶቹ ከባቡሩ ከሚወርዱ ተሳፋሪዎች መካከል ስደተኞቹን እየለዩ ወደ ሌላ ባቡር እየወሰዷቸው ነው።

በጀርመን የባየርን ግዛት ዋና ከተማ ሙኒክ ከእንግዲህ ወዲህ ለስደተኞች በቂ ቦታ እንደሌለ ባለሥልጣናቱ እየተናገሩ ነው። «ሙኒክ ሞልታለች» ሲሉ አንድ ባለሥልጣን ለማብራራት ሞከሩ። እናም ስደተኞቹ በሌላኛው ባቡር ጉዞዋቸውን መቀጠል አለባቸው። ረዥም ጉዟቸው ገና አላበቃም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ