1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከባድ ዝናብ እና የጎርፍ አደጋ በምስራቅ አፍሪቃ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 2 2008

በወላይታ ዞን ኪንዶ ኮሻ ወረዳ በአምስት ቀበሌዎች የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት 39 ሰዎች መሞታቸውን ለኢትዮጵያ መንግስት ቅርበት ያለው መገናኛ ብዙሃን ዘገበ። በባሌ ዞን የጣለው ከባድ ዝናብ በፈጠረው ጎርፍ ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸውም ተሰምቷል።

https://p.dw.com/p/1IlHh
Überschwemmungen in Paraguay Asuncion
ምስል Reuters/J. Adorno/Files

[No title]

የምስራቅ አፍሪቃ አገሮች መልኩን በሚቀያይረው የኤል ኒንኖ የአየር ጠባይ ባስከተላቸው ድንገተኛ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተትን በመሰሉ አደጋዎች እየተናጡ ነው። ለወራት በዝናብ እጥረት እና ድርቅ የተሰቃዩት አገሮች የጎርፍ አደጋ በሚያስከትል ከፍተኛ ዝናብ መጥለቅለቅ ይዘዋል። በኢትዮጵያ፤ ኬንያ፤ ታንዛኒያ እና ርዋንዳ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ በፈጠረው ጎርፍ የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ንብረት ወድሟል። በኢትዮጵያ የሶማሌ፤አፋር፤ኦሮሚያ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልሎች በተከሰቱት አደጋዎች የሰዎች ህይወት ጠፍቷል።

Kenia Einsturz Gebäudekomplex nach schweren Regenfällen
ምስል Getty Images/AFP/STR

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ በርዋንዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት 49 ሰዎች መሞታቸውን እና 500 የመኖያ ቤቶች መውደማቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል። በከባድ ዝናብ ምክንያት በተፈጠረው የመሬት መንሸራተት በሰሜናዊ ርዋንዳ ጋኬንኬ የተሰኘ መንደር ከሁሉም የከፋ አደጋ የደረሰበት ሲሆን 34 ሰዎች ሞተዋል። ለሁለት ቀናት በአገሪቱ በጣለው ዝናብ ኪጋሊን ከሰሜናዊ እና ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ተዘጋግተዋል። በርዋንዳ የመሬት መንሸራተት የተለመደ ቢሆንም የዚህ ዓመቱ ግን የከፋ ነው።

በኬንያ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የዋና ከተማዋ ናይሮቢ እና ሌሎች ትልልቅ ከተሞች ጎዳናዎች በጎርፍ ተጥለቅልቀው ታይተዋል። ለቀናት የጣለው ከባድ ዝናብ በፈጠረው ጎርፍ ምክንያት ባለፈው ወር መገባደጃ የመኖሪያ ህንጻ ተደርምሶ 50 ሰዎች ሞተዋል። በሞምባሳ በትናንትናው ዕለት ባለስድስት ፎቅ ህንጻ ተደርምሷል።

Simbabwe Dürre Maisfeld
ምስል picture alliance/Photoshot

በኢትዮጵያ ለወራት በዘለቀው ድርቅ እና አሁን በተከሰተው ጎርፍ ምክንያት ምርት ባለመኖሩ ለእርዳታ ድርጅቶች አስጊ ሁኔታ ፈጥሯል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 10.2 ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ ጠባቂ ለመሆን መገደዳቸውን አስታውቆ ነበር። «እንዲህ አይነት ድርቅ ፈጽሞ ሰምተንው የማናውቀው ነው» ይላሉ በሶማሌ ክልል የዴሬላ ወረዳ አገር ሽማግሌ የሆኑት ሞሐመድ አደን። ለሶስት ተከታታይ አመታት በኤል ኒንዮ ምክንያት የጣለው ዝናብ እጅጉን አነስተኛ ነበር። አሁን ደግሞ አደገኛ ጎርፍ ተከትሎታል። ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ በመጪው የግንቦት ወርም እንደሚጥል የሚናገሩት አቶ ምትኩ ካሳ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች አካባቢውን ጥለው እንዲወጡ እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እና የእርዳታ ድርጅቶች ከአስር ሚሊዮን የሚልቁ የዕለት ምግብ ፈላጊዎችን ለመመገብ አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቀዋል። ለቀውሱ መፍትሔ ለማበጀት 1.4 ቢሊዮን ዶላር (1.2 ቢሊዮን ዩሮ) የሚያስፈልግ ቢሆንም የተገኘው ግን ግማሽ ያክሉ ብቻ ነው።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ