1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን ለኮሮና መድኃኒት ፍለጋ በተክል ላይ የሚደረግ ምርመራ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 1 2012

የኮሮና ወረርሽን በዓለም ላይ ከተከሰተ ወዲህ ስርጭቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መድሃኒቶችና ክትባቶችን ለማግኘት በርካታ ምርምሮች በመካሄድ ላይ ናቸው።የጀርመን ተመራማሪዎችም የኮቪድ-19 በሽታን ለማከም የሚያስችል መድሃኒት ለመቀመም በአንድ ተክል ላይ ተስፋ ሰጪ የተባለ ምርምር እያደረጉ መሆኑን ከሰሞኑ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/3exPp
China World Malaria Day
ምስል picture-alliance/dpa/T. Kaixing

ተክል ላይ የሚደረገው ሳይንሳዊ ጥናት የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው

ማክስ ፕላንክ ተብሎ የሚጠራው የጀርመን የምርምር ተቋም በርሊን ከሚገኘው ፍሪ ዩንቨርሲቲና ከሌሎች የምርምር ተቋማት ጋር በመሆን በፖስትዳም ከተማ በሳይንሳዊ መጠሪያው «አርትሚዚያ አኑዋ» የተባለ ተከል  ለኮሮና ፈውስ ይሆን እንደሁ ለሳምንታት ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል። ምርምር የሚደረግበት ይህ ተክል በተለያዩ ሀገራት በሻይ መልክ ለባህላዊ ህክምና ሲያገለግል ቆይቷል።ቀጫጭን ቅጠሎች ያሉት ይህ ፅድ መሳይ ተክል በእንግሊዝኛ አጠራሩ «ስዊት ዉድወርም»የሚባል ሲሆን በማንኛውም የአትክልት ቦታ በቀላሉ የሚበቅልና በሽታ የመቋቋም አቅሙም ከፍተኛ ነው።

«አርትሚዚያ አኑዋ» በአብዛኛው እስያ ውስጥ የሚገኝ ጥሩ ማዓዛ ያለው ተክል ሲሆን፤ ዝርያው ከሱፍ አበባ  የሚመደብና ለሽቶ፣ ለምግብና ለመጠጥ  ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል ነው።ለረጅም ጊዜም የወባ በሽታ መድሃኒትን ለመቀመም ጥቅም ላይ ሲውል የነበረ  ነው። የማክስ ፕላንክ የጥናት ቡድን መሪ ፒተር ዚቡርገር  እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ደግሞ ይህንን ተከል ለኮቪድ-19 በሽታ ህክምና ይውል ዘንድ ምርምር በማድረግ ላይ ናቸው።ምንም እንኳ  ውጤታማነቱን የሚያረጋግጥ  ይፋዊ መረጃ በአሁኑ ወቅት ባይኖርም። «እስካሁን ያንን ሊያረጋግጥ የሚችል ይፋዊ  መረጃ የለም። ጥናቱን መስራት የጀመርነው ባለፈው በመጋቢት ወር መጀመሪያ ነው።በአብዛኛው የህዋስ ጥናት ነው ያካሄድነው ነገር ግን የሚያስደንቅ ውጤት አግኝተናል።አጠቃላይ ውጤቱን ለመግለጽ ግን ጊዜው አሁን ገና ነው።»

BG: Das ländliche Ecuador steht vor Corona-Ausbruch ohne ärztliche Versorgung
ምስል Reuters/S. Arcos


ጥናቱ ለአቻ የምርምር ቡድኖች ለግምገማ ያልቀረበ ቢሆንም  እኝህ መሰሎቹን ዕፅዋት በማዋሀድና በመቀመም ልምድ ያካበቱት ፒተር ዚቡርገር  በተዋህሲ አማካኝነት የሚመጡትን ጨምሮ የተለያዩ  በሽታዎችን በማከም ረገድ ከዕፅዋት አስደናቂ ውጤት ሲገኝ መቆየቱን አመልክተዋል።በዚህ የተነሳ እሳቸውና የስራ ባልደረቦቻቸው ምርምሩ የኮቢድ-19 በሽታን በማከም ረገድ ትርጉም ያለው ውጤት ሊያስገኝ ይችላል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል። ለጥናቱ ጥቅም ላይ የዋሉት ዕፅዋት ከአሜሪካ ኬንታኪ ግዛት የመጡ ሲሆን ፤ተመራማሪዎቹ እንዳረጋገጡት «የአርትሜዚያ»ን ቅጠል ከንፁህ ከሰልና ከተጣራ ውሃ ጋር በተቀላቀለበት ወቅት  የፀረ-ተዋህሲነት ባህሪ አሳይቷል ፡፡ይህ የፀረ-ተዋህሲነት እንቅስሴ ከሰሉ ከቡና ጋር በተደባለቀበት ወቅት የበለጠ እየጨመረ መሄዱንም ተመራማሪዎቹ አረጋግጠዋል።በፍሪ ዩንቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ክላውስ ኦስትራይደር በተገኘው ውጤት መገረማቸውን ገልፀዋል።

ምንም እንኳ ምርምሩ ተጨማሪ ጥናቶችን የሚጠይቅ በመሆኑ  ውጤቱን በአሁኑ ወቅት አስረግጦ መናገር ባይቻልም፤ ሲበርገር  እንደሚሉት በሰውነት ውስጥ የበሽታ መከላከል አቅምን በማሳደግ ረገድ ጥቅሙ የጎላ ነው። «ትክክለኛ ውጤቱ አይታወቅም። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በሰውነት ውስጥ ያለን የኮሮና ተዋህሲ ስርጭት የሚገታ ሳይሆን የመከላከያ አቅምን ለማሳደግ የሚችል መድሃኒት ነው ብለን እናምናለን።ያ ማለት የበሽታ መከላከያ አቅምን በማሳደግ የሰውነት ትኩሳትን በተለይ በተዋህሲው ሳቢያ የመጣ ትኩሳትንና ህመምን ያክማል።ይህ የበለጠ ትርጉም ይሰጣል። ምክንያቱም ዕፅዋትን በተለያዩ ሀገሮች  ትኩሳትን የሚያመጡ ወባን የመሳሰሉ በሽታዎችን ለማከም ከቻይና ጀምሮ እስከ ደቡብ አሜሪካ  ሲጠቀሙባቸው ኖረዋል።»

Migration - Ocean Viking im Mittelmeer
ምስል picture-alliance/dpa/SOS Mediterrane/L. Bondard

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት በዚህ ተክል ላይ የሚደረገው ሳይንሳዊ ጥናት የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው።ያም ሆኖ ማደጋስካርን የመሳሰሉ የአፍሪቃ ሀገራት  ፍቱን መድሃኒት ነው በሚል ሲያሚካሹት ይታያል።ባለፈው ሚያዝያ ወርም የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊና ፣ከዚሁ ተክል የተመረተ  «ኮቪድ ኦርጋኒክ» ተብሎ የሚጠራ  መጠጥ  አስተዋውቀዋል።ሆኖም ግን መጠጡ በጥናት ያልተረጋገጠ በመሆኑ አደገኛ ነው በሚል  በተመራማሪዎች ዘንድ  ድጋፍና ዕውቅና አላገኘም። ሲበርገርም ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ሳይገኝ ፈዋሽነቱን መግለፅ አስቸጋሪ ነው ይላሉ።
«እንዲህ ዓይነቱን ቃል መግባት አስቸጋሪ ነው ብዬ አስባለሁ ፡፡ ሆኖም የማደጋስካሩ ፕሬዝዳንት በተናገሩት ላይ ሀሳብ መስጠት አልችልም ፡፡ ምክንያቱም ምርቱ  በእጃችን የለም ፡፡ ነገር ግን ለእኛ ስለምርምሩ መግለጫ ከመስጠታችን በፊት ተጨማሪ ጥናቶችን ማየት መልካም ነው።በመሆኑም ሙከራዎቻችን በበቂ ሁኔታ አስደናቂ ናቸው።ተጨማሪ ጥናቶችና ሰዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ ክሊኒካዊ ሙከራ እንካሂዳለን።ይህም ሰዎች እፅዋቱን ቢጠቀሙ የሚመጣውን ውጤት ለመፈተሽ ይረዳል።» የማደጋስካሩ «ኮቪድ ኦርጋኒክ» መጠጥ እስካሁን ክሊኒካዊ ሙከራዎች ያልተካሄደበት ሲሆን፤ ይህን መሰሉን በባለሙያ ያልተረጋገጠ ምርት መጠቀም አደገኛ ነው በሚል  የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አጥብቆ ሲያስጠነቅቅ የቆየ ሲሆን የአርትሜዚያ ተክል ውጤት የሆነ ኮቪድ-19ን የሚከላከልም ሆነ የሚፈውስ መድሃኒት ስለመኖሩ እስካሁን የተረጋጋጠ መረጃ አለመኖሩንም ድርጅቱ አሳስቧል።

የዕፅዋት ተዋፅኦዎች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለማከም ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ውለዋል።«አርትሜዚያ»ም ባህላዊ በሆነ መንገድ ትኩሳትን ለማከም ሲያገለግል ቆይቷል።በአሁኑ ወቅትም  ይህ ተክል በየአመቱ  በሚሊዮን የሚቆጠሩ አዋቂዎችንና ህፃናትን በተሳካ ሁኔታ ለማከም የሚረዳ  የፀረ-ወባ መድሃኒት ውህድ መሰረት ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።ኮቪድ-19ን በተመለከተ ፈዋሽነቱ ውጤታማ ከሆነና  ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ካገኘ ከዚህ ቀደም በባህላዊ መንገድ ለተለያዩ በሽታዎች ሲጠቀሙ የቆዩ ደቡብ አፍሪቃን ለመሳሰሉ ሀገሮች ጥቅሙ በርካታ ነው። «እኔ እንደማስበው በጣም ጥሩ ነው። ምክንያቱም  አንዳንድ በሽታዎችን ለማከም የሚያገለግል አገር በቀል  ተክል ነው። ይህ ተክል ለፀረ ወባ መድሃኒት በጣም አስፈላጊ መሠረት ነው። እንዲሁም ካንሰርን በማከም እና በመከላከል ረገድ  ተዓማኒነት ያለውና ተስፋ ሰጪ ንጥረ-ነገሮችን ይዟል። ስለዚህ ይህ ተክል ለኮቪድ -19 ብቻ የሚያገለግል ነገር አይደለም።» 

Afghanistan Coronavirus und traditionelle Medizin
ምስል DW/S. Tanha

ከጀርመን በተጨማሪ የአሜሪካው ኬንታኪ ዩኒቨርስቲ የአርቲሜዚያ ተከል ከሻይና ከቡና  ጋር በተያያዘ ያለውን  ውጤት ለመገምገም  ክሊኒካዊ ጥናቶችን ለመጀመር ተዘጋጅቷል ፡፡
የሜክሲኮ ተመራማሪዎችም እንዲሁ በአርቲሜዚያ ላይ ክሊኒካዊ ሙከራዎችን የማድረግ ፍላጎት አላቸው ፡፡እናም በቤተ-ሙከራ ምርምሮችና እና ግልጽ ውጤቶች ላይ ብቻ በመመርኮዝ ይህ ተክል ኮቪድ-19ን ለማከም ውጤታማ በሆነ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ መወሰን ይቻላል ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ይላሉ ተመራማሪው ፒተር ዚበርገር  የኮሮና ተዋሲን በተመለከተ በዚህ ተክል ላይ የሚሰጡ ማስጠንቀቂያዎችን ሰዎች ልብ ሊሏቸው ይገባል። 

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ