ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር የአፍሪቃ ትግል

ተፈጥሮ እና አካባቢ

ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር የምትታገለዉ አፍሪቃ

ለአየር ንብረት ለዉጥ አብዛኛዉን የCO2 ብክለት የሚለቁት በኢንዱስትሪ ያደጉት ሃገራት ናቸዉ። የመዘዙ ተጠቂዎችን ግን በደቡብ የሚገኙ ሃገራት ናቸዉ። አፍሪቃዉያን ድርቅ፣ የማዕበል ናዳ፤ የመሬት መከላት እና መራቆት ሀገራቸዉ ሲያጠፋ ዝም ብለዉ ማየትን አይፈልጉም።ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአየር ንብረት ለዉጥ የሚያስከትላቸዉም ተፅዕኖዎች ለመከላከል በራሳቸዉ ተነሳሽነት መንቀሳቀስ ጀምረዋል። በፎቶዉ ላይ የምትታየዉ ደቡብ አፍሪቃዊት ባለሙያ በፀሐይ ኃይል ዉኃ የሚያሞቅ መሣሪያ ከኬፕታዉን ወጣ ብሎ በምትገኘዉ ኩያሳ ከተማ መኖሪያ ቤት ላይ እየሰቀለች ነዉ።

ተፈጥሮ እና አካባቢ

የአየር ንብረት ለዉጥ ከአፍሪቃ 20 ሚሊየን ሰዎችን ያፈናቅላል፤

በሞዛምቢኳ ባይራ ከተማ ኗሪዎች ከአሁኑ የአየር ንብረት ለዉጥን ተፅዕኖ እየተሰማቸዉ ነዉ። የባህር ዉኃ መጠኑ ከፍ በማለቱ ጎርፍ በአካባቢዉ የሚገኘዉን እንዳለ አዉድሞታል። ግሪን ፒስ እንደሚለዉ በአየር ንብረት ለዉጡ ተፅዕኖ ምክንያት በየዓመቱ የሚሰደደዉ ሕዝብ ቁጥር በጦርነት እና ጥቃት ከሚፈናቀለዉ በእጥፍ ይበልጣል። ባለሙያዎች በቀጣይ አስር ዓመታት ዉስጥም በዚሁ ምክንያት አፍሪቃ ዉስጥ 20 ሚሊየን ሕዝብ እንደሚፈናቀል ከወዲሁ ገምተዋል።

ተፈጥሮ እና አካባቢ

የሞዛምቢክ የታይዳል ማዕበል መከላከያ ቢያራ፤

የመንግሥታት የአየር ንብረት መድረክ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2100ዓ,ም የባህር ወለል ከፍታዉ ከ40 እስከ 80 ሴንቲ ሜትር ሊጨምር እንደሚችል ግምት ሰንዝረዋል። እንዲያም ሆኖ ቢያራ በጎርፍ ልትሰጥም አትፈልግም። አዳዲስ ግድቦች እና የወጀብ መከላከያ የመገንባት ፕሮጀክቶችን ለአደጋ በተጋለጡ አካባቢዎች በማካሄድ ላይ ናት። ጎርፍ በሚመጣበት ጊዜ ከተማዋን ለመከላከል ማዕበል ማገጃዎቹ ይዘጋሉ። ከባድ ዝናብ ሲኖር ደግሞ ዉኃዉ በተገቢዉ መንገድ እንዲወገድም ይረዳል።

ተፈጥሮ እና አካባቢ

ሞሮኮ ሰሃራ

የሰሃራ በረሃ በአህጉሪቱ ያሉትን የእርሻ መሬቶች ሁሉ እየበላ እና እያጠፋ በመሄድ ላይ ነዉ። የአፍሪቃ ሃገራት ታዲያ 15 ኪሎ ሜትር ስፋት እና 7750 ኪሎ ሜትር ቁመት ያለዉ አረንጓዴ የደን ቀበቶ በማበጀት እየተስፋፋ ያለዉን በረሃማነት ለመከላከል ፈልገዋል። ይህም ከፍተኛ የካርቦን መጠን ለማስወገድ ይረዳል። ሰዎችም አዲስ የኑሮ ሁኔታ ያገኛሉ። የዘርፉ ምሁራንም ለአየር ንብረት ጥበቃ እንደተደረገ ዓለም አቀፍ ርምጃ ተመልክተዉታል።

ተፈጥሮ እና አካባቢ

የአፈር መከላትን መከላከል

በርካታ ገበሬዎች በአፈር መከላት እና በበረሃ መስፋፋት ምክንያት ማሳቸዉን በወጉ መጠቀም አልቻሉም። ለየት ባለ የመስኖ ስልት የኒዠር ዜጋ የሆነዉ ሳዑና ሞሳ የእርሻ ማሳዉን አፈር ዳግም ለም ማድረግ ችሏል። የሚጠቀመዉ ስልት ምዕተ ዓመታትን የዘለቀ ቢሆንም ፍፁም ተረስቷል። የዘርፉ ባለሙያዎችም ከዚህም ሌላ አንድ ዓይነት ሰብል ከማምረት በየጊዜዉ እየቀያየሩ መዝራትን ይመክራሉ።

ተፈጥሮ እና አካባቢ

ከድንጋይ ከሰል ይልቅ የዉኃ ኃይል

የቅኝ ገዢዎች ኃይልም አፍሪቃ ዉስጥ የዉኃ ግድብ ገንብተዋል። በተመሳሳይ ብዙዎቹም የአፍሪቃ መንግሥታት የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በየሀገራቸዉ ለማረጋገጥ በዉኃ ኃይል ላይ ገንዘብ እያፈሰሱ ነዉ። አሁንም አዳዲስ የዉኃ ግድቦች በመገንባት ላይ ናቸዉ። ከዉኃ የሚመነጭ ኃይል ለአየር ንብረት ተስማሚ ነዉ። እንዲያም ሆኖ አንዳንድ የግድብ ፕሮጀክቶች አወዛጋቢ ናቸዉ። በየጊዜዉም ደኖች ፈፅሞ እየተጨፈጨፉ የአካባቢዉ ኅብረተሰብ ይፈናቀላል።

ተፈጥሮ እና አካባቢ

አረንጓዴ ኃይል ለአፍሪቃ

እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 203ዓ,ም ድረስ እያንዳንዷ የአፍሪቃ ጥግ የኤኬልትሪክ ኃይል አቅርቦት ታገኛለች። ይህ ከፍተኛ ምኖች በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም በፓሪሱ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ ላይ 55ቱ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ለማሳካት ያቀዱት ግብ ነዉ። ታዳሽ ኃይልን ለአፍሪቃ ለማዳረስ የሚንቀሳቀሰዉ ፕሮጀክት 300 ጊጋ ዋት ፅዱ የኤሌክትሪክ ኃይል በዓመት ለማቅረብ አቅዷል። በኢትዮጵያ እንደሚታየዉ ያለ የንፋስ ኃይል ማመንጫ የመጀመሪያ መሆኑ ነዉ።

ተፈጥሮ እና አካባቢ

ራስን መቻል

በርካታ አፍሪቃዉያን በአሁኑ ጊዜ የራሳቸዉን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ስለሚችሉ ከመንግሥት የኤክትሪክ አቅርቦት ላይ መተማመናቸዉን እየተዉ ነዉ። ርካሽ የሆኑት ከፀይ ኃይል ማመንጫ መሳሪያዎች ከብክለት የፀዳ አረንጓዴ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ያስችላሉ። ብዙዎች ግለሰቦች በጀነሬተር ላይ መተማመናቸዉን አቁመዉ የፀኃይ ኃይልን ይጠቀማሉ። የረድኤት ድርጅቶች በፀሐይ ኃይል የሚጠቀሙ ትምህርት ቤቶችን፤ ሃኪም ቤቶችን ያንቀሳቅሳሉ ወይም ደግሞ አምፖሎችን ያቀርባሉ።

ተፈጥሮ እና አካባቢ

በጦብ ፋንታ የፕላስቲክ ጠርሙሶች

የአፍሪቃ ዕቃዎችን ዳግም የመጠቀም ልማድ ዓለምን እየተቆጣጠረ የመጣ ፋሽን ሆኗል። ናይጀሪያ ዉስጥ ያገለገሉ ጠርሙሶች ቤት ይገነባባቸዋል። እዚያ ጠርሙሱን ሲመልሱ የሚከፈል ገንዘብ የለም ወይም ደግሞ በቆሻሻነት በጥንቃቄ የማስወገዱ ስልት የለም። ጠርሙሶቹ በስብሰዉ ወደሌላ ነገር እስኪቀየሩ ድረስ ምዕተ ዓመት ይፈጃል። ጠርሙሶቹ በአፈር ወይም ፍርስራሽ ይሞሉ እና በሸክራ አፈር ይታሸጋሉ። ከዚያም ለግንባታ ዉድ የሆኑት ሸክላዎች ይተካሉ።

ተፈጥሮ እና አካባቢ

ታንዛኒያዊቷ ትንሽዬ የአየር ንብረት ጥበቃ ጀግና

የ16 ዓመቷ ታንዛዊት ገትሩደ ክሌመንት የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋች ሆናለች። በተወለደችባት ከተማ በሚገኝ ራዲዮ በሳምንት አንድ ቀን የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ዝግጅት ታቀርባለች። ለዶቼ ቬለ፤ «አድማጮቼ የአካባቢ ተፈጥሮን ለመጠበቅ እና ዉኃችንን ንጹሕ ለማድረግ አንዳች ነገር ያደርጋሉ ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ።» ብላለች። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2016ዓ,ም ኒዉዮርክ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝታ ንግግር አድርጋለች።

ተፈጥሮ እና አካባቢ

የአየር ንብረት ጉዳይ ምሁራን አህጉሪቷን ይፈልጓታል

የአየር ንብረት ለዉጥ ላይ ባነጣጠረዉ ጥረት የሚሰበሰቡ መረጃዎች ክምችት መዘጋጀት ይኖርበታል። በደቡብ አፍሪቃ የአየር ንብረት ለዉጥ የሳይንስ እና አማራጭ የመሬት አጠቃቀም ማዕከል የተሰኘዉ ተቋም ይህን በመሥራት ላይ ይገኛል። ያቋቋሙት አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ናሚቢያ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ ዛምቢያ እና ጀርመን ናቸዉ። ዓላማዉ በአካባቢዉ የአየር ንብረት ለዉጥ በግብርናዉ እና በዉኃ ላይ የሚያሳርፈዉን ተፅዕኖ መከላከል ነዉ። ሸዋዬ ለገሠ/ ነጋሽ መሐመድ