1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እና ኢስላማዊ ባንኮች 

ረቡዕ፣ ሐምሌ 10 2011

በኢትዮጵያ ከአመታት በፊት ተሞክሮ በመንግሥት እምቢተኝነት የከሸፈው ኢስላማዊ ባንክ የማቋቋም ጥረት ዘንድሮ ሊሳካ ይመስላል። ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ግልጋሎት ለመስጠት ያቀዱ ባንኮች በምሥረታ ሒደት ላይ ይገኛሉ። አደራጆቹ ሐይማኖትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከባንክ ውጪ የሚገኝን ገንዘብ ወደ ሥርዓቱ ይመልሳሉ የሚል ተስፋ አድሮባቸዋል።

https://p.dw.com/p/3MCdK
Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

አራት ኢስላማዊ ባንኮች በምሥረታ ላይ ናቸው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሰኔ መገባደጃ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች እንዲመሠረቱ መንገድ የሚጠርግ መመሪያ አስተላልፏል። በባንኩ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ የተፈረመው ይኸ መመሪያ ከወለድ ነፃ የባንክ ሥራ ለላቀ የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽነት ሊበረታታ እንደሚገባ ያትታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ረዘም ላሉ አመታት በጉዳዩ ላይ ይዞት የነበረውን አቋም ሲቀይር በርከት ያሉ ባንኮች የምሥረታ ሒደታቸውን በማፋጠን ላይ ይገኛሉ።

ዘምዘም ባንክ በምሥረታ ላይ ከሚገኙ መካከል ይገኝበታል። የባንኩ የሸሪዓ አማካሪ ዶክተር እድሪስ መሐመድ እንደሚሉት የድርሻ ሽያጭን ጀምሮ የዝግጅት ሥራው እየተካሔደ ይገኛል።

«እኛ ሰፊ የአባላት ቁጥር ስላለን ለአባላቶቻችን ጥሪ እያቀረብን ነው» የሚሉት ዶክተር እድሪስ  «ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የሰው ኃይል፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ የውስጥ ዝግጅቶች ያስፈልጉታል። ከተፈቀደ ጀምሮ እኛ እየሰራን ያለንው የአዋጪነት ጥናታችንን እየከለስን ነው። ለአዳዲስ አባላቶቻችን በሁሉም ባንኮች አካውንት ተከፍቶ ድርሻ መሸጥ ተጀምሯል» ሲሉ ስለ ዘምዘም ባንክ የምሥረታ ሒደት ተናግረዋል።

በምሥረታ ላይ የሚገኘው ሒጅራ ባንክ የአደራጆች ምክትል ሰብሳቢ እና የፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ሙከሚል በድሩ እንደሚሉት ሒጅራ ባንክን የማቋቋሙ ሐሳብ ከተጠነሰሰ አመት ገደማ ቢሆነውም በይፋ እንቅስቃሴ የተጀመረው ግን ከአራት ወራት በፊት ነው።

«ባንኩ ወደ ፊት የሚሰራበትን አቅጣጫ የሚያሳይ ጠቅለል ያለ ሰነድ ያስፈልግ ነበር። እሱን ሰነድ አዘጋጅተን ለብሔራዊ ባንክ አስገብተን ድርሻ መሸጥ የሚገልጽ ፈቃድ ካገኘን ሶስት ሳምንት ሆኖናል። ከወለድ ነፃ የባንክ ሥራ እንደተለመዱት ባንኮች አይደለም፤ ለዚህ አገር አዲስ ነው። ሐሳቡም ትንሽ ለየት ስለሚል በየክፍለ ሀገሩ እየሔድን ማኅበረሰቡን የማንቃት ሥራ ላይ ነው ያለንው። የፊታችን እሁድ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እናካሒዳለን» ሲሉ አቶ ሙከሚል አስረድተዋል።

Äthiopien Commercial Bank of Ethiopia in Addis Abeba
ምስል DW/E. Bekele

አቶ ሙከሚል እንዳሉት በመጪው እሁድ ከሚካሔደው የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በኋላ ሒጅራ ባንክ በይፋ ድርሻዎቹን መሸጥ ይጀምራል። ዛድ እና ነጃሺ የተባሉ ሌሎች ሁለት ባንኮች የማደራጀት ሥራዎቻቸውን ለማካሔድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝተዋል።

ለመሆኑ በእስላማዊ ሕግጋት የሚመራው ወለድ አልባ የባንክ ሥራ ምን አይነት ነው? በምሥረታ ላይ የሚገኘው የዘምዘም ባንክ የሸሪዓ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ዶክተር እድሪስ «በብዙኃን የእስልምና ዑለማዎች እና አዋቂዎች ዘንድ የሚነገረው በዘመናዊ የባንክ አገልግሎት እየተሰራበት ያለው የወለድ ምጣኔ በሐይማኖቱ እንደማይፈቀድ ነው። በገንዘብ ፤በእህል ወይም በአይነት በሚገለጽ ነገር ላይ የሚደረግ ማንኛውም አይነት ጭማሪ ወለድ ተብሎ ይጠራል። ጭማሪው ለይስሙላም ሊሆን ይችላል፤ ትክክለኛ ጭማሪም ሊሆን ይችላል። ያ የተደረገ ጭማሪ ወለድ ብለን እንጠራዋለን። ቢያንስም ቢበዛም፤ ቢደራረብም ባይደራረብም ወለድ ተብሎ ይጠራል » ሲሉ ሐይማኖታዊውን ትርጓሜ ገልጸዋል።

አቶ ሙከሚል የኢትዮጵያን መንግሥት ሰነዶች እና ከወለድ ነፃ ባንክ በዓለም ገበያ ያሳየውን ዕድገት እያጣቀሱ ኢትዮጵያ መሰል ተቋማት ፈቃድ ለመሥጠት መዘግየቷን ይተቻሉ።

«በ2008 ብሔራዊ ባንክ ስለ ወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚያወራ አንድ ሰነድ ነበረው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለዚህ አይነት የባንክ ሥርዓት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ በጥናት እንዳረጋገጡ እዚያ ሰነድ ውስጥ አስቀምጠዋል። እንዲሁም ለአካዳሚክ የሚሆኑ የጥናት ግብዓቶች ስናይ ለእንደዚህ አይነት የባንክ ሥርዓት ትልቅ ፍላጎት አገር ውስጥ እንዳለ የሚያሳዩ ውጤቶች አሉ። ዓለም ላይ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በደንብ ተጠናክሮ ሥራ ላይ ከዋለ 50 እና 60 አመት ሆኖታል። ዕድገቱንም ከተለመደው የፋይናንስ ሥርዓት አንፃር ብናይ  ወደ አምስት እጥፍ ገደማ እያደገ ነው። የተለመደው የፋይናንስ ሥርዓት በአማካኝ ሁለት በመቶ እያደገ ይኸኛው በእነ ዓለም ባንክ ጥናት ከ10 እስከ 15 በመቶ እያደገ ያለን የፋይናንስ ሥርዓት ወደ ፋይናንሱ ለማካተት ትንሽ ዘግይታለች ብዬ ነው የምለው» ሲሉ አቶ ሙከሚል ይናገራሉ።

አሁን በኢትዮጵያ ገበያ ከተሰማሩ ባንኮች አስሩ ከወለድ ነፃ የሆነ አገልግሎት በጎንዮሽ ይሰጣሉ። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ እስከ 3 ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ። ባንኮቹ የተሰማሩባቸው ዋንኛ የሥራ ዘርፎች ግን ወለድን መሰረት ያደረገ ነው። ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ የሆነ ግልጋሎት የሚሰጡ ባንኮች ለምን እስከዛሬ የሏትም? በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ ግልጋሎት የሚሰጥ እስላማዊ ባንክ የመመሥረት ውጥኑ ግን የዛሬ አይደለም።  

የጨነገፈው ዘምዘም ባንክ

አሁን በምስረታ ላይ የሚገኘው ዘምዘም ባንክ በ1998 ዓ.ም. ገደማ ተወጥኖ በመንግሥት እምቢተኝነት የተጨናገፈ የረዥም ጊዜ እቅድ ነው። ከወለድ ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነ ባንክ የመመሥረት ዕቅድ በተለያዩ ባለሙያዎች ዘንድ የነበረ ቢሆንም ጥያቄው ዶክተር ናስር ዲኖ እና ዶክተር አሕመድ ሑሴን አቅራቢነት በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የእስልምና እምነት ተከታዮች አማካኝነት በወቅቱ ሥልጣን ላይ ለነበሩት ጠቅላይ ምኒስትር መለስ ዜናዊ እንዲቀርብ ተደረገ። ከሌሎች ጥያቄዎች ጋር ተዳምሮ ሚያዝያ 1999 ዓ.ም. ከወለድ ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነ ባንክ የማቋቋም ሐሳብ የቀረበላቸው ጠቅላይ ምኒስትር መለስ ዜናዊ  «ከወለድ ነፃ ባንክ ለማቋቋም የከለከለ ሥርዓት በአሁኑ ሰዓት የለንም። ማቋቋም አቅሙ ካላችሁ እኛ በሕግ በኩል ያሉትን አንዳንድ ጉዳዮች እናስተካክላለን። እናንተ ብቻ እንዲህ አይነት የልማት ተሳትፎ ለማድረግ ያብቃችሁ» የሚል ምላሽ ለልዑካን ቡድኑ መስጠታቸውን ዶክተር እድሪስ ያስታውሳሉ።

ከወቅቱ ጠቅላይ ምኒስትር አዎንታዊ ምላሽ ከተገኘ እና የባንክ ሥራን የተመለከተው የመንግሥት መመሪያ ከተሻሻለ በኋላ ዘምዘም ባንክ በይፋ ወደ ምሥረታ ገባ። በወቅቱ ከባንኩ አደራጆች መካከል አንዱ የነበሩት ዶክተር ኢድሪስ እንደሚሉት ከወለድ ነፃ ባንክ ለመመስረት የተያዘውን ውጥን በይፋ በማስተዋወቅ 6800 ኢትዮጵያውያን ድርሻዎች በመግዛት የዘምዘም ባንክ መስራቾችን ተቀላቀሉ። የባንኩ ካፒታል ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን 137 ሚሊዮን ብር የሚሆነው የተከፈለ ነበር። ከኢትዮጵያ ባሻገር በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአሜሪካ ጭምር የተዋወቀው ዘምዘም ባንክ በሚያዝያ 2003 ዓ.ም. የመሥራች ጉባኤውን በማካሔድ የአደራጆች ሥራ ተጠናቀቀ። አክሲዮን ማኅበሩ ተመሰረተ፤ የባንኩ የቦርድ አባላትም ተመረጡ። «ቀጣዩ ሥራ ብሔራዊ ባንክ የተመረጡትን የቦርድ አባላት አፅድቆ ሥራውን በኃላፊነት እንድንመራ እና በዝግ ሒሳብ  የተቀመጠው ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንድንችል እንዲፈቅድልን ማመልከቻ ፃፍን፤ ያን ማመልከቻ ከፃፍን በኋላ ያልታሰበ ነገር መጣ። በወቅቱ የነበሩት የባንኩ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ‘እባካችሁን ስህተት ተሰርቷል’ አሉን። ምን አይነት ሥህተት አልናቸው። ‘ከአቶ መለስ ጋር የተነጋገርው በመስኮት እንዲሰራ እንጂ ሙሉ አቋም ያለው የወለድ ነፃ ባንክ እንዲቋቋም አልነበረም’ የሚል ሐሳብ አቀረቡ።  እኛ በጣም ገረመንም ተደናገጥንም» ሲሉ ምሥረታው የገጠመውን ዱብእዳ ዶክተር እድሪስ ይገልጹታል።

የዘምዘም አደራጆች በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበሩ ጉምቱ ሹማምንትን ሁሉ እንዳነጋገሩ ያስታውሳሉ። ለአደራጆቹ «ለምን እንደተከለከለ ለእኛም እንቆቅልሽ ነው» የሚል መልስ የሰጡት ሹማምንቱ መፍትሔ ማበጀት ተስኗቸው በምስረታ ላይ የነበረው ፈረሰ። በብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ባንኩን ለመመስረት የተሰበሰበው ገንዘብ አክሲዮን ለገዙ ኢትዮጵያውያን ተመለሰ። ኩነቱ በበርካቶች ዘንድ ሐዘን እና ቁጣን ጭሮ ማለፉን ዶክተር እድሪስ ያስታውሳሉ።

አዳዲሶቹ ባንኮች ምን ይፈይዳሉ?

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ቁጥር ጭማሪ ቢያሳይም ዛሬም የባንክ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር እጅጉን አነስተኛ ነው። የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚጠቁመው በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. የባንክ ደብተር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ከአጠቃላይ የአገሪቱ ዜጎች 35 በመቶ ገደማ ብቻ ነበር። ይኸ በዚያው ዓመት ከዜጎቿ 82 በመቶ የባንክ ደንበኞች ከሆኑባት ኬንያ አኳያ ሲነፃጸር እጅጉን አናሳ ነው። የመብራት፣ የስልክ እና የውሐ አገልግሎቶች ክፍያዎች በባንክ በኩል የሚፈፅሙ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም እጅግ ጥቂት ነው። አቶ ሙከሚል ከወለድ ነፃ ግልጋሎት የሚሰጡት እንደ ሒጅራ ያሉ ባንኮች ለኢትዮጵያ ላቅ ያለ ጠቀሜታ ይዘው እንደሚመጡ ይናገራሉ።

አቶ ሙከሚል በድሩ «አንደኛ በእምነት ሊሆን ይችላል፣ በግል ምልከታው ሊሆን ይችላል ወለድን አልነካካም ያለ ሰፊ ማኅበረሰብ አለ። እነዚህ ሲመጡለት ወደ ባንክ የመምጣት ሒደቱ፣ እምነቱ መተማመኑ ያድጋል። ያ የአገራችንን የፋይናንስ አካታችነት ከፍ ያደርጋል። እንዲሁም ብሩን በተለያየ ጥጋ ጥግ ያስቀመጠ እና ወደ ፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ ያላስገባውን የማኅበረሰብ ክፍል፤ ብሩን ወደ ሥርዓቱ እንዲያስገባ እና ያ ብር ውጤታማ ሆኖ በአገር ውስጥ እንዲዘዋወር ያደርጋል። ሁለተኛው አሁን ያሉት ባንኮች የሚሰሩት ብር ላይ ተመስርተው ነው። ብድር ስትፈልግ የወረቀት ገንዘብ ይሰጡሃል፤ወለዳቸውን ጨምረው ያን የወረቀት ገንዘብ ይቀበሉሃል። በወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ሙዳረባህ እና ሙሻረካህ የምትላቸውን አገልግሎቶች ብትወስድ እነ ሒጅራ ባንኮች የሚሰሩበት ሒደት ትርፍ እና ኪሳራን በመጋራት ላይ ይመሰረታል። ያ ማለት ምንድነው ሐሳብ ያላቸው፣ አቅም ያላቸው ጉልበቱ ያላቸው ሰዎች ያዋጣል የሚባል ዕቅድ ይቀርጹ እና ከባንኩ ጋር በጋራ የሚሰሩበት ሒደት ነው» ብለዋል።

ዶክተር እድሪስ መሐመድ በበኩላቸው «የባንክ አገልግሎት እያገኘ ያለው ማኅበረሰብ በለመደው መንገድ ይቀጥላል ብለን እናስባለን። የእኛ የጎደለን ማሟላት ነው፤ ተፎካካሪ ስሜት አይደለም እኛ ያለን። ክፍተት አለ ያንን ክፍተት እንሞላለን ብለን እናስባለን። በተለይ ክፍተቱ ከከተማ ራቅ ብለው ያሉ ቦታዎች ላይ ገንዘብ ባንክ ማስቀመጥን እንደ ሐራም ስለሚቆጥሩት ብዙ አዕምሯቸው ላይ ገና ሰላም አልሰጣቸውም። በየትራሱ ሥር የተቀመጠ፤ በየካዝናው ስር የተቀመጠ ያልወጣ ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲሔድ እድል ይኖረናል» ሲሉ ተስፋቸውን አስረድተዋል።

አሁን በምሥረታ ላይ ከሚገኙት አራት ባንኮች በተጨማሪ ኩሽ እና ሑዳ የተባሉ ሌሎች ከወለድ ነፃ ግልጋሎት የሚሰጡ ተቋማት የመመሥረት ውጥን መኖሩን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ