1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባለፈው ሐሙስ በተቀሰቀሰው ግጭት ከዐሥር በላይ ሰዎች ተገድለዋል

እሑድ፣ ጥቅምት 12 2010

በኦሮሚያ ክልል በኢሉባቦር ቡኖ በደኔ ዞን ጥቃት ተፈፅሞ የሰዎች ሕይወት ካለፈ በኋላ ውጥረት መንገሱን ነዋሪዎች ተናገሩ። ባለፈው ሐሙስ በቡኖ በደኔ ዞን ዴጋ፣መኮ እና ጮራ ወረዳዎች በከተሞች የተጀመረው ግጭት ወደ ገጠራማ አካባቢዎች መስፋፋቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገልጠዋል።

https://p.dw.com/p/2mK5O
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

በኢሉባቦር ቡኖ በደኔ ዞን በተፈጸሙ ጥቃቶች ከዐስር በላይ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተገለጠ። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በግል የፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ሐተታ ድርጊቱን የፈጸሙት የክልሉ አመራር የወሰዳቸው  "ጠንካራ ርምጃዎች ያላስደሰታቸዉ አካላት" ናቸው ብለዋል። ኃላፊው ዐሥራ አንድ ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠዋል።

በዴጋ ወረዳ በትንትናው ዕለት የሦስት ሰዎች የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸሙን የአዴስ አበሩ ቀበሌ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ነዋሪው እንደሚሉት ሐሙስ እና አርብ ዕለት በተከታታይ ንብረት ወድሟል።

«ሰላማዊ ሰልፍ ብለው ተሰለፉ ማለት ነው። አሁን ሲሰለፉ እንዳለ ወጣቱ ጭፈራ ሲደልቅ በከተማ መሐል ጭፈራውን ተውና እንደገና ሱቅ የተባለን መጋዘን የተባለን እንክትክት አድርገው ሰብረው ንብረቱን አወደሙ። እንደገና ደግሞ ሐሙስ አዳር በገጠር ገቡ። በገጠር ደግሞ የዛን ጊዜ ብዙ ንብረት ሲያወድሙ አደሩ። አሁን ደግሞ ጁምዓ ደግሞ እንደገና ተመልሰው እከተማው ያን ድርጊት ሲፈጥሙ ዋሉ» ሲሉ ለዶይቸ ቬለ።

ግጭቱ በዴጋ፣ መኮ እና ጮራ ወረዳዎች መበርታቱን የተናገሩት ሌላኛው የአዴስ አበሩ ቀበሌ ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው የወረዳ አመራሮችም ይሁኑ የጸጥታ አካላት ሊያቆሙት አለመቻላቸውን ጨምረው ገልጠዋል። አንድ ሔክታር የሚሆን ቡና በተቃዋሚዎች እንደወደመባቸው የተናገሩት የዓይን እማኝ የደኅንነት ሥጋት የተሰማቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ከለላ ለማግኘት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተጠግተዋል ሲሉ አክለዋል።

"ኩሳዬ የምትባል አካባቢ አለች። ትግሬ እና አማራ ያለባት ናት። እሷ አካባቢ ብቻ ሰዎች እየደወሉ የሚነግሩኝ መቶ ሰው እንሆናለን ሕጻናት እና ሴቶችን አባዎራዎችን በአጠቃላይ ጨምረን ያው ጫካ ውስጥ መቶ ነን ብለው ነው አሁን እየደወሉልኝ ያሉት» የዐይን እማኙ «ከየቀበሌው ከገጠርም ከከተማም ከተማ ውስጥ ያሉት ራሱ ዋስትና የለንም እቤታችን ለማደር እና የወረዳ ፖሊስም ሆነ መንግሥትም ያስገድለን ብሎ የወረዳ ፖሊስ መምሪያ ጽ/ቤት አለ ግቢ ሞልቶ ነው ያለው» በማለት አክለዋል።

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት በስልክ ለማግኘት ያደረግንው ጥረት አልተሳካም።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፦«ሲደረግ የነበረዉ ሰልፍ ወደ ሁከት እና ብጥብጥ እንዲያመራ በማድርግ በሰዎች ሕይወት፥ አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ» ተሞክሯል ብለዋል። ኃላፊው ድርጊቱን «የኦሮሞ እና የአማራ ወንድማማች ሕዝቦችን የማይወክል» ብለውታል።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው በግጭቱ የሞቱት ሰዎች 12 መድረሳቸውን እና 14 ሰዎች መቁሰላቸውን 52 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ገልጠዋል። 

«የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦችን ዘመን ተሸጋሪ ሰላማዊ እና በፍቅር የተሞላ ግንኙነት ለማሻከር እና ወደ ከፋ ብጥብጥ ለማምራት ያለመ መሆኑን ተረድተናል» ሲሉ አቶ ንጉሡ በግል የፌስቡክ ገጻቸው ጽፈዋል።

አሶሺየትድ ፕሬስ በበኩሉ አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ጠቅሶ፦ «የዐሥራ አንድ ሰዎች ሕይወት ከመጥፋቱም በተጨማሪ ንብረት ለመውደሙና ሰዎች ለመፈናቀላቸው ምስክሮች አሉን» ማለታቸውን ዘግቧል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ