1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«1.7 ሚሊዮን ሰዎች እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ»

ሰኞ፣ ሰኔ 5 2009

ድርቅ፤ በኢትዮጵያ የከፋ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል ተባለ። በዘንድሮዉ አመት የተጠበቀዉን ያህል የበልግ ዝናብ ባለመገኘቱ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተፈለገ በኢትዮጵያ በድርቅ ሳቢያ የከፋ ሰብዓዊ ቀዉስ ሊያጋጥም እንደሚችል ያስጠነቀቀዉ «ሕፃናት አድን» የተባለዉ ዓለም አቀፉ የእርዳታ ድርጅት ነዉ።

https://p.dw.com/p/2eQaJ
Äthiopien Gode - Dürre-Krise
ምስል DW/J. Jeffrey

Millions Face Food shortage In Ethiopia. - MP3-Stereo

በኢትዮጵያ ለእርሻ ሥራ ወሳኝ የሆነዉ የሚያዚያና የግንቦት ወር የበልግ ዝናብ በሚፈለገዉ መጠን ባለመዝነቡ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የከፋ የምግብ እጥረት ሊያጋጥማቸዉ እንደሚችል ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣዉ ዘገባ አመልክቷል። በተለይ በደቡባዊና ምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች ሁኔታዉ አሳሳቢ በመሆኑ አፋጣኝ እርዳታ ካልተደረገ ሰብዓዊ ቀዉስ ሊያጋጥም እንደሚችል የ«ሕፃናት አድን» ድርጅት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ቻርሊ ሜሰን  ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብም የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ ጥሪ ማድረጉን ተናግረዋል።

«በሀገሪቱ ደቡብና ምሥራቃዊ ክፍሎች የነበረዉ የዝናብ ሁኔታ ጥሩ እንዳልሆነ በመገንዘብ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈዉ ሳምንት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የእርዳታ ጥሪ አቅርቧል። ምክንያቱም የምግብ አቅርቦቱ እሰከዚህ አመት መጨረሻ ድረስ እንዲዘልቅ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋል።»

የዝናብ እጥረቱ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሊቀጥል የሚችል በመሆኑ ከፍተኛ የምግብ አቅርቦት ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ ያ ካልሆነ ግን  በሚሊዮን የሚቆጠሩ እርዳታ ፈላጊዎች ሕይወት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል አሳስበዋል። የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ በአስተማማኝ ሁኔታ ካልተገኘም ተጎጅዎቹ  ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት፣ ለበሽታና ለሞት የሚዳርግ ከባድ አደጋ  ዉስጥም ሊወድቁ ይችላሉ ተብሏል።

የአደጋዉ መጠን በዚህ መልኩ እየጨመረ ቢመጣም በለጋሾች ዘንድ የሚደረገዉ እርዳታና ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱ ሌላዉ አሳሳሳቢ ችግር መሆኑም ነዉ የተገለጸዉ። በዚህም ሳቢያ በሶማሌ ክልል የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ 7 መቶ ሽህ ሰዎች በግንቦት ወር ሳያገኙ ቀርተዋል።«ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ዉስጥ አንድ ሚሊዮን ብቻ ናቸዉ እርዳታ ያገኙት። ያ ማለት ምግብ የሚያስፈልጋቸዉ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች አቅርቦቱን አላገኙም። የወደፊት ይዞታ ሲታይም የምግብ አቅርቦትም ሆነ የገንዘብ እርዳታዉ አሳሳቢ ነዉ፤ ዓለም ዓቀፉ የምግብ ድርጅት በሶማሌ ክልል የሚያደርገዉን እርዳታም ከሀምሌ ጀምሮ ያቋርጣል።
በኢትዮጵያ 4 ሚሊዮን ሕጻናትን ጨምሮ 7, 8 ሚሊየን ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊ ናቸዉ። ይህ ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ዳይሬክተሩ ጠቅሰዉ በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት ግን እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ነዉ ያመለከቱት።

Äthiopien Gode - Dürre-Krise
ምስል DW/J. Jeffrey

በሀገሪቱ መንግሥትና በዓለም ዓቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በተደረገ ድጋፍ እስካሁን ሕይወት ማዳን ቢቻልም ፍላጎቱ እየጨመረ በመምጣቱ ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልጋል ሲሉም ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።

«በዓለም ዙሪያ የእርዳታ ድርጅቶችን በገንዘብ ለሚደግፈዉ የዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ የምናስተላልፈዉ መልክት፤ በደቡብና ምሥራቅ ኢትዮጵያ ያለዉን ችግር አሳሳቢነት በመገንዘብ፤ ለቀረበዉ የእርዳታ ጥሪ ምላሽ መሰጠት ያስፈልጋል የሚል ነዉ።»

የኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተዉ ድርቅ በኬንያ ፣ በሶማሊያና ደቡብ ሱዳንን በመሳሰሉ ጎረቤት ሃገራት የተከሰተ ቢሆንም ኢትዮጵያ ዉስጥ ካለዉ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸዉ ሰዎች ቁጥር አንጻር ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ለወራት በእነዚህ የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት ላይ አድርጎት የነበረዉን ትኩረት ወደ ኢትዮጵያ ሊያዞር ይገባል ሲልም ድርጅቱ አሳስቧል ።

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሠ