1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ130 በላይ የጀልባ ስደተኞች ኅልፈተ-ሕይወት

ሐሙስ፣ መስከረም 23 2006

የአደጋ ደራሽ ሰራተኞች ካገኙት 82 አስክሪን መካከል በርካታ ሴቶች እና ሁለት ህጻናት ይገኙበታል። እንደ ከተማዋ ከንቲባ የጀልባዋ ተሳፋሪዎች ዛሪ ማለዳ በጀልባዋ ዋ ላይ ሳሉ እሳት ከተነሳ በኋላ፤ ለብዙ ሰዓታት ባህሩ ዉስጥ ነበሩ።አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ከኤርትራ እና ከሶማልያ እንደሆኑ ፖሊስ ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/19tPg
ምስል picture-alliance/dpa

አንዲት 500 ያህል ሰዎችን የጫነች ጀልባ በጣልያን የባህር ጠረፍ አካባቢ በደረሰባት የእሳት አደጋ ሰበብ ቢያንስ የ133 ሰዎች ህይወት ጠፋ ፤ 200 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም ። ከአደጋው የ151 ሰዎች ህይወት ማትረፍ ተችሏል ። Ansa የተሰኘዉ የጣልያን የዜና አገልግሎት የላምፔዱዛን የባህር ወደብ ከተማ ከንቲባ፤ ጉይቺ ኒኮሊኒን ጠቅሶ ዛሪ እንደዘገበዉ፤ የአደጋ ደራሽ ሰራተኞች ካገኙት 82 አስክሪን መካከል በርካታ ሴቶች እና ሁለት ህጻናት ይገኙበታል። እንደ ከተማዋ ከንቲባ የጀልባዋ ተሳፋሪዎች ዛሪ ማለዳ በጀልባዋ ዋ ላይ ሳሉ እሳት ከተነሳ በኋላ፤ ለብዙ ሰዓታት ባህሩ ዉስጥ ነበሩ። ከአደጋዉ የተረፉት ግለሰቦችም ከፍተኛ ድንጋጤ ዉስጥ ይገኛሉ። የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤንሪኮ ሌታ ክስተቱን « ከባድ አደጋ » ብለዉታል። የጣልያን ምክር ቤት አባል ካሊድ ቹኪ አደጋዉን እንደሰሙ እንዲህ ነበር ያሉት
«በኛ ሀገር ዛሪ እንደተከሰተዉ አይነት የጀልባ ስደተኞች አደጋ ተከስቶ አያዉቅም። መልሳችን ጠንካራ መሆን አለበት፤ አዉሮጳ በስደተኞች ጉዳይ ያለዉን ፖለቲካ እንደገና ማጤን ይኖርበታል። ስለሰዎች ዝዉዉር እና ሽያጭ እንዲሁም በሰሜን አፍሪቃ ያለዉን ሁኔታ ሃላፊነት መዉሰድ ይኖርበታል» የአደጋ ሰራተኞች የሟቾችን ቁጥር ስንት እንደሆን መቁጠሩ እንደተሳናቸዉ መግለፃቸዉ ተመልክቶአል። የአካባቢዉ ፖሊስ፤ 500 ተሳፋሪዎችን አጭቃ የነበረችዉ አነስተኛ ጀልባ ከሊቢያ የባህር ጠረፍ መነሳትዋን አስታውቋል። በተጨማሪም አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ከኤርትራ እና ከሶማልያ እንደሆኑ ፖሊስ ጨምሮ ተናግሯል።ቱኒዝያን እና የጣልያንዋን የባህር ጠረፍ ሲሲሊያን የሚያዋስነዉ የላምፔዱዛ የባህር ጠረፍ በየዓመቱ በሽዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ አዉሮጳዉ ሕብረት ለመግባት የሚሞክሩበት የባህር በር ነዉ።
ባለፉት ሳምንታት ከግብፅ ከኤርትራ ከሶማልያ እና ከሶርያ የመጡ ስደተኞች ወደ ጣልያን ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ተመሳሳይ አደጋ እንደደረሰባቸዉ ይታወቃል።

Flüchtlinge ertrinken vor Lampedusa
ምስል picture-alliance/dpa

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ