1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ7 ሺሕ በላይ የሰሜን ዕዝ አባላት ነፃ መውጣታቸውን ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ ተናገሩ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 19 2013

የኢትዮጵያ መንግሥት "ታግተው የነበሩ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የሰሜን ዕዝ ኦፊሰሮች" ነፃ እንደወጡ አስታውቋል። ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ መቀሌን የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ ጦር "የሰሜን ዕዝ ጠቅላይ መምሪያን ቢሮ ተቆጣጥሯል። ከሠራዊታችን የዘረፋቸውን ታንኮች፣ መድፎች፣ ብረት ለበሶች እና ከባድ መሳሪያዎች ሁሉ አስመልሷል" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3lxxq
Äthiopien General Birhanu Jula Gelalcha
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ (ከፋይል)ምስል Office of the Prime Minister

የኢትዮጵያ ጦር የመቀሌ ከተማን ሲቆጣጠር "በሺሕዎች የሚቆጠሩ የታገቱ የሰሜን ዕዝ ኦፊሰሮች" ማስለቀቁን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ። ባለፈው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ዕኩለ ለሊት ገደማ በተፈጸመ ጥቃት በህወሓት ታማኞች እጅ የቆየውን የሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ ጦር "ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን" መንግሥት ገልጿል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት በመቀሌ ከተማ የሚገኘው የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የክልሉ የአስተዳደር ቢሮ እና ሌሎች ቁልፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ጦር እጅ ገብተዋል።

ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ የኢትዮጵያ ጦር "በጁንታው የህወሓት ኃይል የታወጀበትን ጦርነት መክቶ ከሰባት ሺሕ በላይ የሰሜን ዕዝ አባላትን ነፃ አውጥቷል።" ሲሉ ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

ጄኔራል ብርሀኑ "የሰሜን ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የነበረውን ቢሮ ተቆጣጥሯል። ከሠራዊታችን የዘረፋቸውን ታንኮች፣ መድፎች፣ ብረት ለበሶች እና ከባድ መሳሪያዎች ሁሉ አስመልሷል። ከዚህ በተረፈ በየቦታው የነበረውን የሠራዊታችንን ዴፖ በሠራዊታችን ቁጥጥር ሥር እንዲሆን አድርጓል" ብለዋል።

ከ500 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ያሏት የመቀሌ ከተማ ላለፉት ሶስት ሳምንታት ከኢትዮጵያ የፌድራል መንግሥት ውጊያ የገጠመው የህወሓት ዋንኛ መቀመጫ ሆና ቆይታለች።

ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በከተማዋ የሚደረግ ውጊያ አስግቶት እንደነበር ያስታወሱት ጄኔራል ብርሀኑ "ሕዝቡ በየቤቱ ሆኖ መቀሌ ያለ ምንም ዕልቂት" በጦሩ ቁጥጥር ሥር መግባቷን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

ጄኔራል ብርሀኑ "ሠራዊታችን ከመንግሥት የተሰጠውን ሕገ-መንግሥትን የማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ ራሱንም የመከላከል ተልዕኮ የመጨረሻውን አጠናቋል" ብለዋል።

"ጦርነቱ ከአሁን በኋላ የሚሆነው በፖሊስ እና የተበታተነ፣ በየጎሬው የተደበቀ ኃይል የመለቃቀም እና ወደ ሕግ የማቅረብ ነገር ነው የሚሆነው። በወሳኝ መልኩ ጦርነቱ ቆሟል። የወያኔ አመራር በመደምሰሱ ምክንያት፣ የመጨረሻ ምሽጉ በመደርመሱ ምክንያት፤ የመከላከያ ሠራዊታችን እጅ በመግባቱ ምክንያት ወሳኙ ጦርነት አልቋል።" ሲሉ ተደምጠዋል።