1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ካራቱሪ ኩባንያ ከሰረ መባሉ

ማክሰኞ፣ ጥር 19 2007

በኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል 100 ሺ ሄክታር መሬት ለእርሻ ስራ የተኮናተረዉ የህንዱ ካራቱሪ ኩባንያ መክሠሩን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ። ኩባንያው ከተረከበዉ መሬት ያለማው 1,340 ሄክታር ብቻ ነው።

https://p.dw.com/p/1ER6i
Indonesien Borneo Regenwald Abholzung Rodung
ምስል Imago

መቀመጫውን በህንድ ባንግሎር ያደረገው ካራቱሪ ግሎባል ሊሚትድ የተሰኘው ኩባንያ በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል 300ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ሲሰጠው በአመት አንድ ሚሊዮን ቶን በቆሎ፤ ሩዝ፤የፓልም ተክልና ሌሎች የግብርና ውጤቶችን ሊያመርት ነበር። ኩባንያው ከሰባት አመታት በፊት የወሰደው መሬት ወደ 100 ሺ ሄክታር ዝቅ ተደርጓል። ይሁንና ማልማት የቻለው 1340 ሄክታር ብቻ ነው። አቶ አበራ ሙላት የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ሃላፊ ናቸው።

«መሬት ከመንግስት በዝቅተኛ የሊዝ ዋጋ ነው የቀረበለት። በርካታ የእርሻ ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ተደርጎ ተደርጎለታል። የባንክ ብድር ተመቻችቶለት ከመንግስትም ከግልም ባንክ ተበድሮ እንቅስቃሴ ያደረገበት ሁኔታ ነው ያለው። ከቀረጥ ነጻ የገቡ የእርሻ ማሽነሪዎች ለሌላ ለማንም አልተሰጠም። የእርሻ ማሽነሪ የማከራየት ስራ ለሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ የተፈቀደ ነው። ያለውን የገንዘብ ችግር ከመቅረፍ አንጻርም ውይይት ተደርጎ እንዲያከራይ ተፈቅዶለት ነበር። እነዚህን ሁሉ እድሎች ተጠቅሞ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም።»

Flash-Galerie Äthiopien Land Grab
ምስል DW/Schadomsky

የኩባንያው የ100 ሺ ሄክታር መሬት የግብርና ስራ ለአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀል ምክንያት መሆኑን ሁማን ራይትስ ዎች እና የኦክላንድ ማዕከልን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያን መንግስት ይወቅሳሉ። ኩባንያውም ለአካባቢው ነዋሪዎች ቃል የገባውን የስራ አድል መፍጠር፤የጤናና የትምህርት መሰረተ ልማት ማቅረብ ተስኖት ቆይቷል። አቶ አበራ ሙላት እንደሚሉት ኩባንያው የከሰረው በውስጣዊ ችግሮቹ ነው።

«ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ስልሳ ሚሊዮን ብር ብድር ወስዷል። ከሌሎች ባንኮችም ተጨምሮ ወደ 170 ሚሊዮን ብር ብድር ነው የወሰደው።በኢንቨስትመንት ምክንያት ሊገኝ የሚችለው የውጭ ምንዛሪ፤የአገር ውስጥ ኢንደስትሪዎች ግብዓት አቅርቦት እንደዚሁም የስራ እድል ፈጠራ ከግምት ውስጥ ገብተው ነበር ድጋፍ ሲደረግለት የነበረው።አሁን አጠቃላይ ከውጤት አንጻር ፍሬያማ ብለን የምንወስደው ውጤት የለም። ለምን የሚለው ኩባንያው የራሱ አስተዳደራዊ እና የውስጥ ችግሮች ያሉ ነው የሚመስለን።»

ኩባንያው ከኢትዮጵያ ባንኮች የወሰደውን ብድር ለመመለስ ከቀረጥ ነጻ ያስገባቸው መሳሪያዎች እየሸጠ ነው።በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የህንድ ኩባንያዎች ከአካባቢው ነባር ነዋሪዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ያጠኑ ቢክሩም ጊል የተባሉ የኢኮኖሚ ባለሙያየአካባቢውን የምግብ አቅርቦት ያሻሽላል፤ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን እና የግብርና ዘዴዎችን ያስተዋውቃል የተባለው ካራቱሪ በብዙ መንገድ ስኬታማ አይደለም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ባለሙያው የካራቱሪ የእርሻ ስራ የአካባቢውን ነባር ነዋሪዎች ያገለለ መሆኑን እና ሰፊ መሬት በአንድ ጊዜ ለማልማት በተደረገ ጥረት የብዝሃ ሃብት ጥፋት መከሰቱን በጥናታቸው ይገልጻሉ።

100 ሺ ሄክታር መሬት እና ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ እዳ ያለበት የካራቱሪ ኩባንያ በጉዳዩ ላይ ያለውን አስተያየት ለማካተት ያደረግንው ሙከራ አልተሳካም። የኢትዮጵያ መንግስት በኩባንያው ቀጣይ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን ጉዳዩን በጥንቃቄ እየተከታተለ መሆኑን አቶ አበራ ሙላት ጨምረው አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ