1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ምን ይዞ መጣ?

ረቡዕ፣ ሐምሌ 27 2014

ገንዘብ ማንቀሳቀስና ዓለም አቀፍ ሐዋላ መቀበል የመሳሰሉ ሥራዎች ላይ ሊሰማራ ያቀደው ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ገበያው ለመግባት እየተንደረደረ ነው። የባንኮችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ግልጋሎት የራቀውን የማኅበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ያቀደው ኩባንያ ያለ መያዣ ብድር የመስጠት ሐሳብ አለው

https://p.dw.com/p/4F4hf
Äthiopien Kacha Digital Financial Services SC
ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ባካሔደው የማስተዋወቂያ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል።ምስል Kacha Digital Financial Services SC

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ምን ይዞ መጣ?

ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተሰጠው ፈቃድ መሠረት ሥራ ለመጀመር እየተንደረደረ ነው። በኢትዮጵያ ገበያ በተንቀሳቃሽ ስልኮች የተለያዩ የገንዘብ አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችል ፈቃድ በማግኘት ከግሉ ዘርፍ ቀዳሚ የሆነው ኩባንያ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ከ60 ለማይበልጡ ቀናት ሙከራ ያከናውናል።

"የሙከራ ትግበራችንን እንደ ጨረስን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መዝኖ ሙሉ በሙሉ ወደ ገበያ መግባት ትችላላችሁ የሚለውን ፈቃድ እንደሰጠን ወደ ገበያ ለመግባት እየሰራን ነው" ሲሉ የኩባንያው የገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ይገርማል መሸሻ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ይገርማል ኩባንያው በተግባር ሥራ የሚጀምርበትን ጊዜ ይኸ ነው ብሎ ለመናገር ቢቸግራቸውም "እጅግ በጣም አጭር" እንደሚሆን ግን እምነታቸው ነው።

ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በ50 ሚሊዮን ብር የተከፈለ በ200 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል የተቋቋመ ነው። የካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ሰባት የቦርድ አባላት እና መሥራች ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አብርሐም ጥላሁን ሹመት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደጸደቀ የኩባንያው መግለጫ ይጠቁማል።

"ከ65 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት ችግር አሁንም አለበት። ከብድር አኳያ 83.3 ሚሊዮን አካባቢ የቁጠባ ሒሳብ ባለበት አገር ውስጥ ከ360 ሺሕ የማይዘልቅ ቁጥር ያለው ተበዳሪ ነው ያለው" የሚሉት አቶ ይገርማል የካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ባለድርሻዎች "በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት እና አካታችነት" ረገድ ያለውን ጉድለት ለመፍታት ኩባንያውን እንደመሠረቱ ያስረዳሉ።  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ከእጁ ያስገባው ካቻ በኩባንያው አስራ ሶስት ባለ ድርሻዎች "በሐሳብ ደረጃ" የተጠነሰሰው ከሶስት ዓመታት በፊት ነው። ያለፉትን ዓመታት የህግ እና የቴክኖሎጂ መመዘኛዎችን ለማሟላት ሥራ ላይ የቆየ ሲሆን አቶ ይገርማል እንደሚሉት በራሱ ባለሙያዎች "ከፍተኛ ጊዜ እና መዋዕለ-ንዋይ የፈሰሰበት ቴክኖሎጂ" አዘጋጅቷል።

Äthiopien Kacha Digital Financial Services SC
ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ይገርማል መሸሻ፣ የኩባንያው የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ተሾመ በርሔ እና የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብርሐም ጥላሁን (ከግራ ወደ ቀኝ)ምስል Kacha Digital Financial Services SC

ኩባንያው "የታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጋር የሚገኝ ማንኛውም ሲም ካርድ ተጠቅሞ አገልግሎት ሊሰጥ በሚችል የሞባይል ቀፎ ገንዘብ ማስቀመጥ፣ ገንዘብ ማውጣት፣ ሐዋላ መቀበል፣ ሐዋላ መላክ፣ ዓለም አቀፍ ሐዋላ መቀበል፣ ክፍያ መክፈል የአውቶቡስ ትኬት መግዛት እና የአገልግሎት ክፍያ መፈጸም የሚያስችል አገልግሎት" ሊሰጥ መዘጋጀቱን አቶ ይገርማል ተናግረዋል። ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በአጭር የጽሁፍ መልዕክት፣ ለአንድሮይድ እና ለአይኦኤስ ስልኮች በሚዘጋጁ መተግበሪያዎች እንዲሁም በድረ-ገጽ አገልግሎቶቹን ለደንበኞቹ ያቀርባል። አቶ ይገርማል "ለአይነ ስውራን ለአጠቃቀም የሚመች በድምጽ ታግዞ የሚሰጥ አገልግሎት ይኖረናል" ብለዋል።

የካቻ መወዳደሪያ ምንድነው?

ካቻ ሥራ ሲጀምር ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመተባበር የመድን ዋስትና የማቅረብ ውጥን አለው። ለስልክ የአየር ሰዓት መሸመት እና የካርድ ክፍያዎች መፈጸም የሚያስችሉ አገልግሎቶችም ይኖሩታል።  "ካቻ እንደ አንድ ማሸነፊያ ወይም መወዳደሪያ አገልግሎት አድርጎ የሚያቀርበው" ግን አቶ ይገርማል እንደሚሉት "ምንም ዓይነት መያዣ የማይጠየቅባቸው ብድሮችን ማቅረብ" ነው። ይኸ ኩባንያው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሊሰማራባቸው ከተፈቀዱለት የሥራ ዘርፎች መካከል ይገኝበታል።  

"በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ምክንያት ከአንድ ወር ደሞዙ ሌላኛው ወር ደሞዙ ለመድረስ የሚቸገረውን ማኅበረሰብ" ኩባንያው ማገልገል እንደሚሻ የሚናገሩት አቶ ይገርማል "ከመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ምንም ዓይነት መያዣ የማይጠየቅባቸውን ፈርጀ ብዙ የሆኑ ችግሮችን የሚፈቱ የብድር አገልግሎቶችን እናቀርባለን" በማለት ገልጸዋል። "ከመደበኛው የባንክ ብድር አገልግሎት በተለየ መንገድ ለሁሉም እንደ የፍላጎቱ" ብድር ለማቅረብ የወጠነው ይኸ ኩባንያ የእስልምና ሐይማኖት የሸሪዓ ሕግን የተከተለ የብድር አገልግሎቶች ይኖሩታል።  

ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ሊያበድር የሚችለው የገንዘብ መጠን እስካሁን አልተወሰነም። ነገር ግን ኩባንያው ለደንበኞቹ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችለው "የብድር ትንተና እና ምዘና ሰርቶ ውሳኔ የሚያሳልፍ" ቴክኖሎጂ አዘጋጅቷል። "ሥርዓቱ በመረጃ ደህንነት ጥበቃ መሠረት ደንበኛው የፈቀደለትን መረጃ በሙሉ ወስዶ፤ ተንትኖ ሲስተሙ ራሱ ´ለእርስዎ ካቻ ሊበድርዎት የሚችለው ገንዘብ ይኸን ያህል ነው´ ብሎ ገደብ ያሳያል። በዚህ መሠረት ሁሉም ሰው በሚፈልገው ልክ ከዚያ ላይ እያቀናነሰም ቢሆን ወይም አንድ ላይ መውሰድ የሚችልበትን ዕድል እናመቻቻለን" ሲሉ አቶ ይገርማል ኩባንያቸው ተስፋ የሰነቀበትን ዘርፍ አሰራር አስረድተዋል።

Äthiopien Währung Birr
"በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ምክንያት ከአንድ ወር ደሞዙ ሌላኛው ወር ደሞዙ ለመድረስ የሚቸገረውን ደሞዝተኛ ማኅበረሰብ" ኩባንያው ማገልገል እንደሚሻ የሚናገሩት አቶ ይገርማል "ከመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ምንም ዓይነት መያዣ የማይጠየቅባቸውን ፈርጀ ብዙ የሆኑ ችግሮችን የሚፈቱ የብድር አገልግሎቶችን እናቀርባለን" በማለት ገልጸዋል።ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

በኢትዮጵያ እንዲህ የብድር አቅርቦትን ጨምሮ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት እና አካታችነት የማዳረስ ጉዳይ ለረዥም ዓመታት ለባንኮች እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተተወ ሆኖ ቆይቷል። ከዚህ ቀደም ሥራ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ በሞባይል እና በወኪሎች አማካኝነት የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ የፋይናንስ አገልግሎት የማቅረብ ሥራ ለባንኮች እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብቻ የሚፈቅድ ነበር። ሔሎ ካሽ፣ ኤም ብር፣ ሲቢኢ ብር እና አቢሲኒያ ፔይን የመሳሰሉ አገልግሎቶች የኢትዮጵያ ባንኮች እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሥራውን ለማከናወን ከሞከሩባቸው መንገዶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

በተባበሩት መንግሥታት ካፒታል ደቨለፕመንት ፈንድ (UNCDF) የዲጂታል የገንዘብ አገልግሎት ባለሙያው አቶ እንዳሻው ተስፋዬ "የቴክኖሎጂ ተቋማት ፈቃድ ማግኘት ስለማይችሉ አገልግሎቱን መስጠት አይችሉም። ባንኮች እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እንደነበረው የመረዳት መጠን አገልግሎቶቹን ለተጠቃሚ ሲያደርሱ ቆይተዋል" ሲሉ ከዚህ ቀደም የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።

እንደ ሔሎ ካሽ እና ኤም ብር ያሉ አገልግሎቶችን መጠቀም የጀመሩ የኢትዮጵያ ባንኮች እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ደንበኞቻቸው ከመደበኛ አካውንታቸው በሞባይል ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንዲችሉ የሚፈቅድ አሰራር ቢከተሉም ዘርፉ በቅጡ አልደረጀም። ተቋማቱ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ጥቅም ላይ ያዋሉት የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የሥራቸው ማከናወኛ እንጂ ራሱን ችሎ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት እና አካታችነት ማሳኪያ መንገድ እንዳልሆነ ይተቻል። አቶ እንዳሻው እንደሚሉት ግን ተቋማቱ ሥራ ላይ ባዋሏቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን ለማስተማር እና ለማስተዋወቅ ግፊት አድርገዋል።

Äthiopien Mobiler Geldservice
ሔሎ ካሽ፣ ኤም ብር፣ ሲቢኢ ብር እና አቢሲኒያ ፔይን የመሳሰሉ አገልግሎቶች የኢትዮጵያ ባንኮች እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሥራውን ለማከናወን ከሞከሩባቸው መንገዶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።ምስል DW/M. Gerth-Niculescu

"የባንክ እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሥራ በዋንኛነት ቅርንጫፎች ላይ የተመሠረቱ አገልግሎቶች ለደንበኞች የሚቀርቡበት ነው" የሚሉት ባለሙያው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ከተለመደው የባንክ አገልግሎት የሚቃረን መሆኑን ይጠቅሳሉ። አቶ እንዳሻው እንደሚሉት "የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ከቅርንጫፎች ወጥቶ በስልክ ወይም የሸቀጥ ሱቆች፣ ነዳጅ ማደያዎች፣ መድሐኒት መሸጫዎች እና ሱፐርማርኬቶች የመሳሰሉ የሥርጭት ሰንሰለቶችን በመጠቀም በቀላሉ ከኅብረተሰቡ አጠገብ ባሉ ተቋማት የፋይናንስ አገልግሎትን በማቅረብ ደንበኞች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥርዓት መገንባት ነው።" በዚህ ምክንያት "እንደ አንድ የአገልግሎት አይነት ለማቅረብ ሲሞከር ስለነበረ የሚገባውን ያህል ትኩረት አግኝቶ ሁሉም ጋ ተደራሽ መሆን ሳይችል ቀርቷል" ሲሉ አቶ እንደሻው አስረድተዋል።

ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ወደ ገበያው መግባት የሚያስችለውን ፈቃድ ያገኘው ሁለት መመሪያዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመጋቢት እና በነሐሴ 2012 ይፋ ካደረገ በኋላ ነው። መመሪያዎቹ የክፍያ መፈጸሚያ መንገዶች እና አገልግሎቶቹን ለማስተዳደር የወጡ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ለባንኮች እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብቻ ተዘግቶ የቆየውን ዘርፍ እንደ ካቻ ላሉ ኩባንያዎችም ክፍት አድርገውታል።

 የኢትዮ-ቴሌኮም ቴሌ-ብር ምን ይዞ መጣ?

"ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው ዓመት ቴሌ ብር አገልግሎት የጀመረበት ምክንያትም ከፖሊሲ አንጻር ለቀቅ ከማለት የተነሳ ነው። ሌሎች የክፍያ አገልግሎት የሚያሳልጡ እንደ ቻፖ እና አሪፍ ፔይ የመሳሰሉ ድርጅቶች ፈቃድ አግኝተዋል" ያሉት አቶ እንዳሻው ይኸ ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን መሰል ኩባንያዎች ወደ ገበያው እንዲገቡ በር መክፈቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ እንደ ካቻ ላሉ ኩባንያዎች ካቀረበው ዕድል መካከል አንዱ በወኪሎች አማካኝነት ሥራቸውን እንዲከውኑ መፍቀዱ የሚጠቀስ ነው። ደንበኞች ወደ ባንክ ቅርንጫፎች መሔድ ሳያስፈልጋቸው ባንኮች፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እና እንደ ካቻ ያሉ ኩባንያዎች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በወኪሎች ማግኘት ይችላሉ።

Äthiopien Kacha Digital Financial Services SC
ምስል Kacha Digital Financial Services SC

አቶ ይገርማል "ካቻ ከሁለት ከፍተኛ ወኪሎች (Super Agents) ጋር ሥምምነት አድርጎ ወደ መሬት የማውረድ ትግበራ ላይ ነው የሚገኘው። እነዚህ ከፍተኛ ወኪሎች 30 ሺሕ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ በሌሎች አገልግሎቶች ከእነሱ ጋር የተሳሰሩ ወኪሎች በመላ ሀገሪቱ አሏቸው። እነሱን ተጠቅመን ህብረተሰቡን እንደርሳለን ብለን እናስባለን" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኩባንያው ከባንኮች፣ ከማይክሮ ፋይናንሶች እና ከኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ተጣምሮ አገልግሎቶቹን የማቅረብ ዕቅድ አለው።

የደንበኞቹን ቁጥር ከ21 ሚሊዮን በላይ ያደረሰው ቴሌ ብር አሁን ካቻ በሚገባበት የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ አለው። መንግስታዊው ኢትዮ ቴሌኮም ያስጀመረው ቴሌ ብር ከ13 ባንኮች ጋር የሚሰራ ሲሆን ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ዝውውር ተፈጽሞበታል። በመጪው ነሐሴ በድሬዳዋ ሥራውን አንድ ብሎ የሚጀምረው ሳፋሪኮም በተመሳሳይ አገልግሎት እንዲሰማራ ከመንግስት ፈቃድ እንደሚሰጠው ይጠበቃል።

የካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ የገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ይገርማል "እዚህ አገር ከፍተኛ የሆነ የእውቀት እና የግንዛቤ ችግር አለ። አስቀድሞ ወደ ገበያ የገባው የኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያን ጨምሮ ሁሉም የፋይናንስ ዘርፍ ላይ እየሰራን ያለን ኩባንያዎች ተረባርበን ከፋይናንስ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ የኅብረተሰባችንን ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።  "በተግባር አካታችነትን ወደ ገበያው እናምጣ የእኛ መርኅ ነው" የሚሉት የካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የገበያ ልማት ዳይሬክተር "ያንን ለማድረግ ከሁሉም አካላት ጋር እንተባበራለን" ሲሉ አክለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ካፒታል ደቨለፕመንት ፈንድ (UNCDF) የዲጂታል የገንዘብ አገልግሎት ባለሙያው አቶ እንዳሻው ተስፋዬ ገበያው ገና እንዳልተነካ ይስማማሉ። ዘርፉ በአገሪቱ ባሉ መሠረተ-ልማቶች ላይ ብቻ እንኳ በቅጡ ከተስፋፋ ከዚህ ቀደም አመርቂ የፋይናንስ አገልግሎት ያላገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ተቃጠቃሚ ማድረግ ይቻላል። ኩባንያዎቹ ለገበያው የሚያቀርቧቸው ግልጋሎቶች ኅብረተሰቡን እና ቋንቋውን ታሳቢ ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባ አቶ እንዳሻው ይመክራሉ። የኅብረተሰቡን የቴክኖሎጂ እውቀት እና የአጠቃቀም ክኅሎት ማዳበር እና ተዓማኒነት ያላቸው አገልግሎቶች ማቅረብ ከኩባንያዎቹ እና ከተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የሚጠበቅ ነው።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ