1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ክሪሚያ- የመሻኮቻ ምድር

ሰኞ፣ መጋቢት 1 2006

ያቺ ትንሽ ግን ሥልታዊ ምድር ሐያል ዓለም ለጦርነት እንዳሰለፈች ሁሉ-ሐያላንን ለሠላም ሰብስባም ነበር።የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት አሸናፊዎች የሶቬት ሕብረቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊን፥የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ፍራክሊን ሩዘቬልት እና የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዊንስተን ቸርችር ዓለም የሸነሸኑት-ክሬሚያ ላይ ነበር

https://p.dw.com/p/1BN18
ምስል picture-alliance/abaca


ለምሥራቅ-ምዕራብ ሐያላን ያደሩት ባላንጦች ፍጥጫ ላፍታም ቢሆን ወደ መጓሸም ንሮባታል።የግጭት ጦርነት ጭንቀት ያጨፈገገዉ ነፋሻማ አየርዋ ቅዳሜ ባፍታ ተኩስ ተናዉጦም ነበር።ክሪሚያ።ጦርነት ግን አልተጫረባትም።ሠላምም የላትም።የሞስኮ ዋሽንግተን ብራስልስ አንጦች ንግግር የሌለዉን ሠላም የማኖር ዲፕሎማሲ፤ ያልተጫረዉን ጦርነት በሚያስጭር ዉግዘት ቅጣት፤ ዛቻ፤ፉከራ እየተጣፋ በዜሮ ዉጤት ተቀስፏል።እንዴት? ለምን?


ክሪሚያ ዛሬ-ከቤልጂግ ትንሽ አነስ ትላለች።ሃያ-ሰባት ሺሕ ስኩዬር ኪሎሜትር።ወደ ደቡብ የሜድትራኒያን ባሕር እና አካባቢዉን ወደ ሰሜን ገሚስ አዉሮጳን ለመቆጣጠር እጅግ ጠቃሚ ሥልታዊ ልሳነ-ምድር ነች።ለእርሻ የምትመች ለም፥ ሐገር ጎብኚዎችን የሚስብ፥ አቅም ያለዉን የሚያማልል የአየር ፀባይ፥ ተፎጥሯዊ አቀማመጥ፥ የጥንታዊ ሥልጣኔ ዉጤት የተከማቸባት ዉብ ልሳነ-ምድር ናት።

በሁለት ሺሕ አንድ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በተደረገዉ ቆጠራ መሠረት ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ አላት።ሐምሳ-ስምንት በመቶዉ የሩሲያ ዝርያ ያለዉ ነዉ።ሃያ-አራት በመቶዉ የዩክሬን፥ አስራ-ሁለት በመቶዉ ደግሞ ታታሮች ናቸዉ።ለሩሲያ እና ለምዕራባዉያን ያደሩት የዩክሬን ፖለቲከኞች ከ1992 ጀምሮ ግራ ቀኝ ሲጓተቱ የትንሺቱን ልሳነ-ምድር ሕዝብ በዘር፥ ቋንቋ ባሕል እየሰነጠቁ፥ ያላትሙታል።ሃያ-ሁለት ዓመት።

በምዕራቦቹ የሚደገፉት የዩክሬን ፖለቲከኞች ያደራጁት ሠልፈኛ፥ ለሩሲያ የሚወግኑትን የዩክሬን ፕሬዝዳት ካበረረ ወዲሕ ሞስኮ እና ዋሽግተን-ብራስልሶች ሲወዛገቡ ያቺ ግዛት በንትርክ-ጭቅጭቅ ትጨስ ገባች።


«በዩክሬን (አስተዳደር) ሥር ያለፉት ሃያ-ሁለት ዓመታት የትግል ዘመኖች ነበሩ።ለነፃነታችን፥ ለማንነታችን፥ ለቋንቋችን፥ ለጀግኖቻችን መከበር የታገልንባቸዉ ናቸዉ።»

አሉ ቭላድሚር ኮንስታንቲኖቭ-ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ።ለሩሲያ የሚወግነዉ የክሪሚያ ምክር ቤት ሊቀመንበር ናቸዉ።ኮንስታንቲኖቭ የሚመሩት ምክር ቤት የክሪሚያ ሕዝብ ግዛቱ፥ አንድም የዩክሬን ራስ መስተዳድር እንደሆነች እንድትቀጥል አለያም ከሩሲያ ጋር እንድትቀየጥ የፊታችን ዕሁድ በድምፁ (ሪፈረንደም) እንዲወስን ወስኗል።

እሳቸዉ ባንፃሩ የምክር ቤቱን ዉሳኔ ከሚደግፉት ወገኖች ጋር ርዕሠ-ከተማ ሲምፌሮፖል-አደባባይ የተፋጣጠዉን ዉሳኔዉን የሚቃወመዉን ሕዝብ እንወክላለን ከሚሉት አንዱ ናቸዉ።

«አሁን ሕዝበ-ዉሳኔዉን እንደምንቃወም ማሳየት አለብን።አለበለዚያ (ዉሳኔዉን) የምንቀለብስበት መንገድ አይኖርም።አንዴ የሩሲያ አካል ከሆንን ሁሉም ነገር ይዘገያል።ሥለዚሕ አሁኑኑ ዉሳኔዉን በመቃወም በተቻለ መጠን በርካታ ሕዝብ አደባባይ መዉጣት አለበት።»

እኚሕኛዋ ግን ከዩክሬን በመቀየጣችን ምን አገኘን አይነት ይላሉ።«ክሪም ከሩሲያ ጋር ብትሆን ለምጣኔ ሐብቷም፥ ለፖለቲካዉም ጥሩ ነዉ።ሩሲያ ማለት መረጋጋት፥ ፀጥታ፥ ርካሽ የሐይል (ምንጭ)፥ (ሰፊ) የሥራ ዕድል፥ ሠላም ማለት ነዉ።ሥለዚሕ ክሪሚያ ከሩሲያ ጋር መሆን አለባት።»

እያለ-የክሪሚያ ሕዝብ እንደተጓሸመ-ሳምንቱ ሌላ ሳምንት ተካ።ጥንትም-እንዲሕ ነበረች።ሥልታዊ አቀማመጧ-የየዘመኑን ሐያላን አይን እያጓጓ ሲሜሪያዎች፥ ቡልጋሮች፣ ሐኖች፥ ካዛሮች፥ ሩሱች፥ ቤዛንታንያዎች፥ ግሪኮች፥ ታታሮች፥ ሞንጎሎች፥ ቱርኮች በየዘመናቸዉ ነግሰዉባታል።

የኦስማን ቱርኮች ተፅዕኖ ደከም፥ ቀዝ ቀዝ ማለቱን ያስተዋሉት የሩሲያዋ ንግሥት ዬካተሪና አሌክሲና ዳግማዊት ወይም ታላቋ ካትሪና በአስራ-ስምተኛዉ ክፍለ-ዘመን ያቺን ግዛት ተቆጣጠሩ።ወዲያዉ ሳቫስቶፖል በተባለዉ ወደቧ የሩሲያን ባሕር ሐይል ጦር ሠፈር መሠረቱ።

ሩሲያዎች ከዚያች ግዛት ተነስተዉ ወደ ደቡብ ሜድትራኒያንና እና ወደ ደቡብ ምሥራቅ አዉሮጳ መስፋፋታቸዉን ለመገደብ በ1853 ቱርኮች፥ ብሪታንያዎች እና ፈረንሳዮች ሌሎችን አስከትለዉ ከሩሲያ ጋር ለዚያ ዘመን ታላቅ የነበረዉን ጦርነት ገጠሙ።ከሁለቱም ወገን ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ሰዉ አለቀ።

ሩሲያ መሥፋፋቷ ቢገታም ክሪሚያን ግን አለቀቀችም። ጦርነቱ እስከዚያ ዘመን የነበረዉን የአዉሮጳን የሐይል አሠላለፍ መነቃቅሮ-ሐብታም፥ሥልጡኒቱን አሐጉር ኋላ አንደኛዉ እና የዓለም ለተባለዉ ዳግም ጦርነት አቂያቂሞ በ1856 አበቃ።በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ማብቂያ ክሬምሊን የተቆጣጠሩት የሩሲያ ኮሚንስቶች ሲጠናከሩ ክሪሚያንም፥ (ኋላ ዩክሬንንም) የሶቬት ሕብረት ሪፐብሊኮች አድርገዉ ጠቀለሏቸዉ።


ከዩክሬን የሚወለዱት ኒክታ ክሩስቾቭ የሶቬት ሕብረትን የመሪነት ሥልጣን በያዙ ባመቱ በ1954 የዚያቺን ግዛት የሪፐብሊክነት ሥልጣን ሽረዉ የትዉልድ ሐገራቸዉ የዩክሬን ሪፐብሊክ አካል እንድትሆን ወሰኑ።ሶቬት ሕብረት ሥትፈረካከስም ክሪሚያ የዩክሬን ብቸኛዋ ራስ-ገዝ መስተዳድር ግዛት ሆና ቀጠለች።

አዲሱ የዩክሬን ጊዚያዊ ጠቅላይ ሚንስትር አርሴኒ ያሴንዩክ ግን ክሬሚያ ጥንትም፥ ድሮም፥ የዩክሬን አካል ነበረች ይላሉ።

«ሐገራችን ናት።አባት አያቶቻችን ለዚች ሐገር ደማቸዉን አፍስሰዋል።እኛም ከዩክሬን ግዛት አንዲት ጋት መሬት አሳልፈን አንሰጥም።ይሕንን ሩሲያና ፕሬዝዳንቷ ሊያዉቁት ይገባል።»

ያዜንዩክ ያሉት የሆነበት ዘመን-መቼ ይሆን?።ብቻ አሉት።ያዜንዩክ ሞስኮዎችን ያስጠነቀቁት ከአዉሮጳ መሪዎች ጋር ብራስልስ ዉስጥ ሻይ-ቡና ባሉ ማግሥት ነዉ።የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዝዳት የባራክ ኦባማን የፖለቲካ ድጋፍ በምሳ-ራት ግብዣ ለማወራረድ ሰሞኑን ወደ ዋሽግተን ይሔዳሉ።


በ1937 የታላቅዋ ብሪታንያን የጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣን የያዙት ወግ አጥባቂዉ ፖለቲከከኛ አርተር ኔቪሌይን ቻምበርሌይን በዚያ ዘመን እብሪት አሳብጦ፤ ጭካኔ የወጠረዉን የናትሴ ጀርመንን መሪ የአዶልፍ ሒትለርን እኩይ አላማ-ግብ በቅጡ አልተረዱትም ተብለዉ ሥልጣናቸዉን በ1940 ለመልቀቅ ተገደዱ።

ቻምበርሌየን የሒትለርን አላማ አወቁም አላወቁት አዉሮጳን ለመሰልቀጥ በርሊንን ለሚያስደልቀዉ ለናትሴዎች የጦርነት ዛር ትናንሽ ሐገራትን ጭዳ በማድረግ (ናትሲዎች እንዲወስዱ) በመፍቀድ ትልልቆቹን ሐገራት በተለየም ብሪታንያን ከትልቆች ትልቅናት ሊሽቀነጥራት ከሚችለዉ ትልቅ ጦርነት ማዳን ይቻላል የሚል መርሕ ነበራቸዉ።አፒዝመንት ይሉታል-መርሁን።

ቻምበርሌይን ሥልጣን ከመያዛቸዉ ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጵያን የወረረዉ ቤኒቶ መሶሎኒ ከሒትለር ጋር እንዳያብር በሚል ሥሌት ሐበሻን በመርዝ ጋዝ ማንጨርጨሩን እንደ በጎ እምርጃ፤ የደከማይቱ ሐገር ገዢነቱን እንደ ሕጋዊ መብቱ ተቀበሉለት።የትልቂቱ ሐገር ትልቅ መሪ ትልቅ ሐገራቸዉን የሚሰጋ ትልቅ ጠላታቸዉን አቅጣጫ «ለማስቀየስ» የትንሺቱን ሐገር ነፃነት፥ የጥቁር ሕዝቧን ሕይወት «ቤዛ» በማድረጋቸዉን ከወገኖቻቸዉ የወቀሳቸዉ የለም።

ሒትለር ገሚስ ይጎዝላቪያን እንዲወስድ በ1938 ሙኒክ ጀርመን ላይ በፊርማቸዉ ካፀደቁ በኋላ ግን የቻምበርሌይን የዉጪ መርሕ እና እርምጃ ለዋሽግተን-ለንደን እና ለተከታዮቻዉ በጣሙን ለወግ አጥባቂ ፖለቲካኞች የፈሪዎች አብነት ሆኖ እስከ ዛሬ ይጠቀሳል።

የዩናይትድ ስቴትሱ ወግ አጥባቂ ፓርቲ የሪፐብሊካን የምክር ቤት እንደራሴ ሮበርት ፒተንገር በቀደም ደገሙት።

«ኔቪል ቻምበርሌይንን ሆነን፥-ሰዉዬዉ (ፕሬዝዳት ፑቲን) የሚያስበዉ ይኸ ብቻ ነዉ እንድልን አልፈልግም።ምን እንደሚያስብ አላዉቅም።»

ምዕራባዉያን ቻምበርሌይን ላለመሆን-ከመደራደር ዉጪ ያላቸዉ አማራጭ አንድም ሩሲያን መዉጋት፥ አለያም በማዕቀብ መቅጣት ነዉ።ሁለቱም መጥፎ አማራጭ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ከሁለቱ መጥፎ አማራጮች-ቀላሉን መርጣለች።ማዕቀብ።የሩሲያ ጦር ክሪሚያ እንዲሠፍር አድርገዋል ወይም ተባብረዋል በተባሉ የግዛቲቱና የሩሲያ ባለሥልጣናት ላይ የመዘዋወርና ገንዘብን የማዘዋወር ማዕቀብ እንዲጣል ፕሬዝዳት ኦባማ ባለፈዉ ሳምንት አዘዋል።

ሩሲያ ወትሮም ሳቫስቶፖል የጦር ሠፈሯ ከሠፈረዉ ጦሯ ዉጪ ክሬሚያ ግዛት ወታደር አስፍራለች የሚለዉን ወቀሳ ትችት ሁሌም እንዳስተባበለች ነዉ።ያምሆኖ ምዕራባዉያን እንደሚሉት የሩሲያ ጦር ክሪሚያ ከሠፈረ-የሩሲያ ፌደሬሽን ጦር ከጠቅላይ አዛዡ ትዕዛዝ ዉጪ ንቅንቅ አይልም።ጠቅላይ አዛዡ ቭላድሚር ፑቲን ናቸዉ።

አሜሪካኖች የጣሉት ማዕቀብ ግን ፑቲን እና ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸዉን አይነካም።የዋሽግተኖች እርምጃ-ከእዉነታዉ የመቃራኑ ሐቅ ለታዛቢዎች ድንቅ፥ ግራ-አጋቢ ለብዙዎቹ ደግሞ ግራ የመጋባት ዉጤት ነዉ የሆነዉ።

እንደራሴ ፒተንገር ግን አዉሮጳና አሜሪካኖች በሩሲያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ ከጣሉ ፑቲንን ማብረከክ አይገዳቸዉም ባይ ናቸዉ።

«በሩሲያ ላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ማዕቀብ ከጣልን (የፑቲንን) የገዛ ሐገሩን መበጥበጥ እንችላለን። ወደ ዉጪ መመልከትና ጠብ (መቆስቆስ) አይችልም።ወደ ዉስጥ ለመመልከት ይገደዳል።»

የፒተንገርን ምኞት የማይጋራ-የምዕራብ ፖለቲከኛ በርግጥ የለም።እዉነታዉ ፒተንገር እንደሚሉት ቀላል አለመሆኑ እንጂ ጭንቁ።የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ባንኮች ሩሲያ ዉስጥ አንድ መቶ ሰማን ቢሊዮን ዩሮ ያንቀሳቅሳሉ።የአንዲት ጀርመን ብቻ ስድስት ሺሕ ኩባብዮች ሩሲያ ዉስጥ ይሰራሉ።

ከስወስት መቶ ሺሕ እስከ አራት መቶ ሺሒ የሚሆኑ ጀርመናዉን ሩሲያ ዉስጥ ይሰራሉ።ባለፈዉ ዓመት ብቻ ጀርመን ከሩሲያ ጋር የሰባ-ስድስት ቢሊዮን ዩሮ የንግድ ልዉዉጥ አድርጋለች።ከጀርመን የጋስ ፍጆታ አርባ በመቶ ያሕሉ ከሩሲያ ቧምቧ የሚቀዳ ነዉ።የጀርመኑ የኢንዱስትሪና የንግድ ምክር ቤት ሐላፊ ማርቲን ቫንዝልቤን ፖለቲከኞች ለቅጣት ከመሯሯጥ ይልቅ ዉዝግብ ለማቀዝ እንዲጥሩ ቢማፀኑ እዉነት አላቸዉ።

«ሁኔታዉን ማቀዝቀዝ ተገቢ ነዉ።እኛ ማለት ፖለቲከኞቹ ከፕሬዝዳት ፑቲን እና ከቅርብ ባለሥልጣኖቻቸዉ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላዋ ሩሲያ ጋር ባጠቃላይ መነጋገር አለባቸዉ። የምንደራደርበት ሁኔታ መኖሩን ማወቅ ብልሕነት ነዉ።በስተመጨረሻዉ ከሆነ መቀራረብ ላይ መድረስ አለብን።»

የምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራትንየጋስ ጥማትን መቶ በመቶ የምታረካዉ ሩሲያ ናት።የነዚሕ ሐገራት አብዛኛ ንግድም ከሩያ ጋር የተቆራኘ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት መሪዎች ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ይጣል የሚለዉን ሐሳብ የገፉትም ለዚሕ ነዉ።በጀርመን ምክር ቤት የግራዎቹ ፓርቲ እንደራሴዎች መሪ ግሪጎር ግይሲ ደግሞ ማዕቀብ ለመጣል የሩሲያን ሐብት፥ ጉልበት መዘንጋት የለብንም አይነት ይላሉ።

«ሩሲያ በጣም ጠንካራ ናት።ደካማ ሸሪክን በማዕቀብ ማንበርከክ ይቻላል።ሩሲያን ግን አይደለም። መንገድ አያጡም።ቻይናንንም ከጎናቸዉ ማሠለፍ ይችላሉ።አቃለን መገመት የለብንም።»

የጃፓን መሪዎች ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ እንደሚያደርጉት ሁሉ የዩናይትድ ስቴትስ ታማኝነታቸዉን በቀደም ሲያረጋግጡ ቻይኖች ከሩሲያ ጋር መቆማቸዉን ለመናገር አልተጣደፉም።ከቻይና እስካሁን በይፋ የተነገረዉ የሞስኮ-ዋሽግተን-ብራስልስ ተቀናቃኞች ዉዝግብ ሽኩቻቸዉን በድርድር ይፍቱ የሚል ያስታራቂነት መልዕክት ነዉ።የከፋ ከመጣ ግን የቶኪዮችን አቋም አይቶ-የቤጂንጎችን መለየቱ አይገድም።

የሩሲያ የጦር መሳሪያ፥ የፖለቲካ፥ የተፈጥሮ ሐብት ተፅዕኖ ቤጂንግ ላይ አይቆምም።ከሶሪያ እስከ ኢራን፥ ከሰሜን ኮሪያ እስከ ቬኑዙዌላ ይተረተራል።ብዙዎች እንደሚሉት የሞስኮ፥ ዋሽግተን-ብራልስ ፖለቲከኞች የገጠሙትን እሰጥ አገባ ለማርገብ አብነቱ ድርድር ነዉ።የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ግን ጠየቁ «የማዕቀብ፥ የማግለል ዘመቻ-ዛቻ ፉከራዉ እንደቀጠለ መደራደር እንዴት ይቻላል?» ብለዉ።

ያቺ ትንሽ ግን ሥልታዊ ጥንታዊ፥ ታሪካዊት ዉብ ልሳነ-ምድር በ1850ዎቹ የያኔዉን ሐያል ዓለም ለጦርነት እንዳሰለፈች ሁሉ-የእስከ ዛሬዎቹን ሐያላንን ለሠላም ሰብስባም ነበር።የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት አሸናፊዎች የሶቬት ሕብረቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊን፥የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ፍራክሊን ሩዘቬልት እና የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዊንስተን ቸርችር እስከ ቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ድረስ የዘለቀዉን ዓለም የሸነሸኑት-ክሬሚያ ላይ ነበር።የካቲት 1945 ።ዘንድሮ-ጦርነት በርግጥ አልተጨረባትም።ሠላምም የላትም።1953-ወይስ 1945 ይደገምባት ይሆን።

Bildergalerie Krim Referendum 10.03.2014 Simferopol
ምስል Reuters
Ukraine pro-russische Demonstration in Simferopol 9.3.2014
ምስል Getty Images
Wladimir Konstantinow Ukraine pro-ukrainische Demonstration in Simferopol 9.3.2014
ምስል Reuters
Wladimir Putin und Barack Obama am Telefon
ምስል picture-alliance/dpa
Ukraine russische Soldaten Simferopol
ምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ


















ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ