1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ክትባትን የማዳረሱ ጥረት

ማክሰኞ፣ የካቲት 3 2007

በሕፃንነት ተገቢዉን ክትባት ማግኘት አስቀድሞ በመከተብ ለመከላከል ከሚቻሉ በሽታዎች፣ የአካል ጉዳት እንዲሁም ሞት ለመዳን እንደሚረዳ ይታመናል። ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት በሚሰጠዉ ክትባት የስድት ሚሊዮን ሕፃናትን ሕይወት ማትረፍ ተችሏል።

https://p.dw.com/p/1EV7X
Symbolbild Kinder Impfung Afrika Archiv 2014 Bangui
ምስል AFP/Getty Images/M. Medina

የዓለም የጤና ድርጅት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዓለም ደረጃ ለሕፃናት እንዲሰጥ የሚመከር ክትባትን ያገኙ ልጆች ቁጥር ባለበት የቆመ እንደሚመስል በድረ ገጹ ላይ ይፋ ባደረገዉ መረጃ ጠቁሟል። የዛሬ ሁለት ዓመት ተቅማጥ ቴታነስና ትክትክን ለመከላከል የሚያስችሉትን ክትባቶች 112 ሚሊዮን ሕፃናት አግኝተዋል። እነዚህ በሽታዎች ሕፃናትን በሚያደርሱት ጉዳት ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸዉን በቅጠፍና ለአካል ጉዳት በመዳረግ የሚታወቁ ናቸዉ። በዚሁ ዓመትም 129 ሃገራት እነዚህን በሽታዎች መከላከል የሚያስችለዉን ክትባት በጥቅሉ 90 በመቶ ማዳረሳቸዉ ተመዝግቧል። ለሕፃናቱ የሚሰጠዉ ክትባት በዓለም የጤና ድርጅት ዝርዝር መሠረት 12 የሚሆኑ የታወቁና መከላከል የሚቻሉ በሽታዎችን ይመለከታ። አምስት ዓመት ሳይሞላቸዉ የሚሞቱ ሕፃናትን ቁጥር ለመቀነስ የሚደረገዉ ጥረት በአንድ ወገን እንዳለ ቢሆንም በተፈላጊዉ መጠን ተፈላጊዎቹን ክትባቶች ለማዳረስ እንቅፋት የሆኑት ያለዉ አቅም ዉሱን መሆን፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸዉ የጤና ችግሮች መበላለጥ፣ ደካማ የሆነ የጤና አገልግሎት ሥርዓት እና ክትባቱ መዳረሱን ለማረጋገጥ የሚደረገዉ ክትትልና ቁጥጥር በቂ አለመሆን መሆናቸዉን የዓለም የጤና ድርጅት ይዘረዝራል። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም 21,8 ሚሊዮን ገደማ ሕፃናት ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ አልተቻለም። ከእዚህ ቁጥር ግማሽ ያህሉ ሕፃናት የሚገኙት በሶስት ሃገራት ነዉ፤ ህንድ፣ ናይጀሪ እና ፓኪስታን። እንደየዓለም የጤና ድርጅት ከሆነ በቀጣይ ከፍተኛ እና የተጠናከረ ጥረት የሚያስፈልግዉ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸዉ እና ክትባትን ባላዳረሱ ሃገራት መሆን ይኖርበታል።

GAVI Konferenz in Berlin 27.01.2015 Rede Merkel
በበርሊን ለክትባት ገንዘብ ያሰባሰበዉ ጉባኤምስል Reuters/F. Bensch

በመላዉ ዓለም ለሚገኙ ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ክትባት ለማዳረስ በእንግሊዘኛ ምሕፃሩ GAVI የተሰኘዉ ዓለም አቀፉ የበሽታ መከላከልና ክትባት ጉድኝት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም የተቋቋመዉ። በማይክሮሶፍት መስራች ቢል ጌትስ መሥራችነት የተቋቋመዉ GAVI ከተመሠረተ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2000 አንስቶ በተለያዩ ሃገራት በጥቅሉ 440 ሚሊዮን ሕፃናት ተፈላጊዎቹን ክትባት እንዲያገኙ ለማድረግ ተችሏል። በዚህም ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑትን አምስት ዓመት ያልሞላቸዉ ሕፃናት ከሞት መዳፍ እንደያመልጡ እንዳደረገ ይነገርለታል። ድርጅቱ ባለፈዉ ሳምንት ጀርመን ባስተናገደችዉ ለክትባት ገንዘብ የማሰባሰቢያ ጉባኤ ከለጋሾች በሚያሰባስበዉ ገንዘብ በቀጣይ በ73 ድሀ ሃገራት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ክትባት በወቅቱ እንዲያገኙ እንደሚጥር ተገልጿል። ቢልና ሚልኒዳ ጌትስትን ጨምሮ መንግሥታት እና የግል ለጋሾች በተገኙበት የበርሊኑ የGAVI ጉባኤ በቀጣይ አምስት ዓመታት ለሕፃናት ክትባትን ለማዳረስ 7,5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማዋጣት ቃል ተገብቷል። በዚህ ጉባኤ የሕፃናት ሞት እንዲገታ እንደሚሹ ዳግም የገለፁት ቢሊየነሩ ጌትስ 1,5 ቢሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ብለዋል። እንደእሳቸዉ የድሀ ሃገራት ሕፃናት ክትባት እንዲያገኙ ከሚሹት መካከል የብሪታኒያ መንግሥትም ተመሳሳይ መጠን ያለዉ ገንዘብ ነዉ እሰጣለሁ ያለዉ።

Bill Gates bei der GAVI Konferenz in Berlin 27.01.2015
ቢል ጌትስ በበርሊኑ ጉባኤምስል Reuters/F. Bensch

ኖርዌይ 969 ሚሊዮን ዶላር፣ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ 800 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል። የለጋሾቹን ጉባኤ ያስተናገደችዉ ጀርመን 600 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ብላለች። በጉባኤዉ ላይ የሚሠሩበትን ድርጅት ወክለዉ እንደተገኙ የገለፁልን በወርልድ ቪዥን የጤናና አመጋገብ ዳይሬክተር ዶክተር መስፍን ተክሉ ለሕጻናት ክትባትን ለማዳረስ ገንዘብ ባሰባሰዉ ስብሰባ የተገኙት የተለያዩ አካላት መሆናቸዉን ነዉ ያመለከቱት።

ጉባኤዉን ያስተናገደችዉ የጀርመን የልማት ሚኒስትር ጌርድ ሙለር የሀገራቸዉ የልማት መርህ ለጤና ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ በመጠቆም፤ ሀገራቸዉ ሕፃናት በክትባት ማጣት ምክንያት መሞታቸዉ እንዲያከትም ትሻለች ብለዋል።

GAVI Konferenz in Berlin 27.01.2015
ከበርሊኑ ጉባኤ ተሳታፊዎች ጥቂቱምስል Reuters/F. Bensch

«ከ2030ዓ,ም ድረስ ከአምስት ዓመት በታች ከሚገኙ ሕፃን አንዱም መከላከል በሚቻል በሽታ እንድሞት አንፈልግም። »

በክትባት ማጣት ምክንያት በአንድ በኩል በርካታ ሕፃናት ሕይወታቸዉ መቀጠፉ እንዳለ ሆኖ ለልጅነት ልምሻ ከሚጋለጡባቸዉ ሃገራት በግንባር ቀደምትነት ናይጀሪያ ትጠቀሳለች። በተቃራኒዉ ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ታንዛኒያ ክትባትን ለሕፃናት በማዳረስ የተሻለ ዉጤት ማስመዝገቧን የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ጃካያ ኪክዌቴ ባለፈዉ ሳምንት በርሊን ላይ በተካሄደዉ ለክትባት ገንዘብ የማሰባሰቢያ ጉባኤ ላይ በተገኙበት ወቅት ጠቁመዋል።

«ታንዛኒያ ዉስጥ በGAVI ደጋፍ በዓለም የጤና ድርጅት የተመዘገቡት 11ዱ ክትባቶች እንዲዳረሱ አድርገናል። በዚህም ታንዛኒያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑትን በመድረስ ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙትና የተሻለ ዉጤት ካስመዘገቡት ሃገራት አንዷ ለመሆን በቅታለች።»

ወርልድ ቪዥንን ወክለዉ በበርሊኑ ጉባኤ የተገኙት ዶክተር መስፍንም በበኩላቸዉ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገራት በተሻለ የሕፃናት ሞት መቀነስ የሚለዉን የተመድ የዓምዓቱን የልማት ግብ ከወዲሁ ለማሳካት ከቻሉት ሃገራት አንዷ እንደሆነች ጠቅሰዋል። ሌላዉ በዚህ ጉባኤ ላይ ከተገኙት የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች አንዱ የሆኑት የማሊዉ ፕሬዝደንት ኢብራሂም ኬይታ በበኩላቸዉ ሕፃናት በተገቢዉ እድሜ ክትባት እንዲያገኙ ማድረጉ ለአንድ ሀገር የጤናማ ትዉልድ ዋስትና እንደሆነ አመልክተዋል።

Deutschland Schweinegrippe Pandemie Impfung
ምስል AP

«በጤና፣ ሰላምና ፀጥታ መካከል ያለዉን ግንኙነት ለመግለጽ እንፈልጋለን። እኔ በግሌ ክትባት የልጆቻችንን ሕይወትና ጤና ብቻ ሳይሆን የሀገሬን የተሻለ መፃኢ የኤኮኖሚ እጣ ፈንታም እንደሚያረጋግጥ አጥብቄ አምናለሁ። እርግጥ ነዉ ጤናማ ልጆች ትምህርት ቤት የመሄድ እድላቸዉም የሰፋ ከመሆኑም ሌላ ሲያድጉም ምርታማ መሆናቸዉ አያነጋግርም። ሕፃናትን ማስከተብ ለወደፊት በሂደት ጥቅሙ ለሁሉም ነዉ።»

ክትባትን በማዳረስ በየዓመት ከሁለት እስከ ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሕፃናትን ሕይወት ማትረፍ እንደተቻለ የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ዶክተር መስፍን ክትባትን ለሁሉም ሕፃናት ለማዳረስ የሚደረገዉ ጥረት የየመንግሥታቱን አስተዋፅኦ እንደሚሻ ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ምንም እንኳን አምስት አመት ሳይሞላቸዉ የሚቀጠፉ ሕፃናትን ቁጥር ለመቀነስ የምታደርገዉ ጥረት አበረታች ቢሆንም ገና ብዙ መሥራት እንደሚገባ ዶክተር መስፍን አሳስበዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ