1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የክረምት ዕረፍትን ለኮምፒውተር ሳይንስ ስልጠና

ረቡዕ፣ ነሐሴ 2 2010

በኢትዮጵያ ያሉ አዳጊዎች መሰረታዊ የኮምፒውተር ሳይንስ ዕውቀት እንዲጨብጩ በግለሰቦች እና ድርጅቶች የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። “አዲስ ኮደር” በሚል ስያሜ ተመሳሳይ ስልጠናዎች እየሰጡ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ትኩረታቸውን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/32qrA
Äthiopien Summer Shool Addis Coder in Addis Abeba
ምስል Addis Coder

ኮምፒውተር ሳይንስ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች

ሃያኛ ዓመቱን ሊደፍን አንድ ፈሪ የቀረው ዳዊት ፍቅሩ በደቡብ ኮሪያዊቷ የወደብ ከተማ ቡሳን ከከተመ አምስት ወር አለፈው።  በዚያ የሀገሬውን ቋንቋ ይማራል። ከመፈንቅ በኋላ በመዲናይቱ ሶል የሚጀምረውን የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ለመከታተል ቋንቋ መማር ግድ ነውና ነው ለዚያ ቅድሚያ የሰጠው። አምስት ዓመታት የሚወስደውን ይህን የውጭ ሀገር የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ግን እንዲያው በዋዛ አላገኘውም። ከሶስት ክልሎች እና ከአዲስ አበባ ከተውጣጡ 11 ተማሪዎች ጋር መፎካከር ግድ ብሎት ነበር። 

ከዚያ ቀደም በብሪታንያ እና አሜሪካ ባሉ ተቋማት ለመማር ያደረገው ጥረት አንድም በቪዛ ክልከላ፤ አንድም ተቀባይነት በማጣት ከሽፎበታል። ዳዊት እንዲህ የባጀለት ኮምፒውተር ሳይንስ ከዓመታት በፊት የመጀመሪያ የትምህርት ምርጫው እንኳ አልነበረም። የግል መገልገያ ኮምፒውተር ያልነበረው ዳዊት ስለ ኮምፒውተር መሰረታዊ ዕውቀት የጨበጠው በሐረር ይማርበት በነበረው አቡበከር መሰናዶ ትምህርት ቤት ነው።

Äthiopien Summer Shool Addis Coder in Addis Abeba
ምስል Addis Coder

ለሂሳብ ልዩ ዝንባሌ የነበረው ዳዊት በ2008 ዓ.ም የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለ በትምህርቱ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡ ያልተጠበቀ ዕድል አመጣለት። እንደ እርሱ በትምህርታቸው ላቅ ያለ ውጤት ካላቸው 84 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጋር የኮምፒውተር ሳይንስ ስልጠና እንዲወስድ ተመረጠ። ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ እነዚህ ተማሪዎች የክረምት እረፍታቸውን ስልጠናውን በመውሰድ እንዲያሳልፉ በአዲስ አበባ ተሰባሰቡ።  

ጎበዞቹን ተማሪዎች በአንድ ላይ እንዲሰባሰቡ ዕድሉን የፈጠረላቸው “አዲስ ኮደር” በሚል ስያሜ የተጀመረ የስልጠና መርኃ ግብር ነው። በ2003 ዓ. ም. የተጀመረው ይህ መርኃ ግብር የተጠነሰሰው በዕውቁ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ሃርቫርድ መምህር በሆነ አንድ ኢትዮ-አሜሪካዊ ወጣት ነው። ወጣቱ ጄላኒ ኔልሰን ይባላል። በሃርቫርድ በተባባሪ ፕሮፌሰርነት እያገለገ ያለው ይህ ወጣት የሚያስተምረውን እና ጥናት የሚያካሄድበትን የኮምፒውተር ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለማጋራት ያቅዳል። ዕቅዱንም “አዲስ ኮደር” የሚል ስያሜ ይሰጠውና ስልጠና ይጀምራል። ከዚህ ቀደም ባካሄዳቸው ሁለት ስልጠናዎች 164 ተማሪዎች መሳተፋቸውን የሚናገረው ጄላኒ ስለስልጠናው ተልዕኮ ያስረዳል። 

Äthiopien Summer Shool Addis Coder in Addis Abeba
ምስል Addis Coder

“የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ስለ ኮምፒውተር ሳይንስ እና አልጎሪዝም እንዲያውቁ ይረዳል። እኔ እንደማስበው ብዙ ተማሪዎች ስለምንነቱ ግንዛቤ የላቸውም። በኢትዮጵያ ያሉ አብዛኛዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በቤተሰቦቻቸው ህክምና እንዲያጠኑ  ይመከራሉ።  ምናልባት የተወሰኑት ምህንድስና ወይም ህግ እንዲያጠኑ ተነግሯቸው ይሆናል። ነገር ግን ስለ ኮምፒውተር ሳይንስ እና ስለለው የስራ ዕድል በቂ ግንዛቤ የለም። ይህ መርኃ ግብር ለዚህ የትምህርት አይነት ያለውን ፍላጎት እንደሚያነቃቃ ተስፋ አለን” ይላል ጄላኒ።

ለአንድ ወር የሚቆየውን ስልጠና በእርግጥም ተማሪዎች ለኮምፒውተር ሳይንስ ፍላጎት እንዲያሳድሩ የሚያደርግ እንደነበር ዳዊት ይናገራል። እርሱ እና ሌሎች ተማሪዎች እንዲህ አይነት ስልጠና ቀደም ሲል ባለመውሰዳቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ከብደዋቸው እንደነበር ያስታውሳል። ተባባሪ ፕሮፌሰር ጄላኒን ጨምሮ ትምህርቱን የሚሰጧቸው ባለሙያዎች ባደረጉላቸው እገዛ ግን በስተኋላ በቀላሉ ትምህርቱን ይከታተሉ እንደነበር ያስረዳል። ስልጠናውን ሲያጠናቅቅም ህክምና ለማጥናት የነበረውን ሀሳብ በመተው ወደ ኮምፒውተር ሳይንስ ፊቱን ማዞሩን ይገልጻል። 

በ“አዲስ  ኮደር” የሰለጠኑ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሲቀላቀሉ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ለማጥናት መወሰናቸው የመርኃ ግብሩን ውጤታማነት ያመላክታል። በ“አዲስ ኮደር” ጠንሳሽ እና ተባባሪዎቹ በኩራት የሚነሳው ሌላው ስኬት ከስልጠናው ተሳታፊዎች ውስጥ ጥቂቶቹ በአሜሪካ እና በሌላም ሀገራት ባሉ ዕውቅ ዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውን ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን እንደ ጉግል እና ፌስ ቡክ ባሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የስራ ዕድል ያገኙም አሉ።  

ዳዊት ለዚህም ቢሆን አዲስ ኮደር ትልቅ ሚና ተጫውቷል ይላል። በተባባሪ ፕሮፌሰር ጄላኒ አማካኝነት በኦንላይን በተከፈተ የመወያያ መድረክ የስልጠናው ተሳታፊዎች እና መምህራኖቻቸው የትምህርት ዕድልን ጨምሮ በርካታ መረጃዎች ይለዋወጡ እንደነበር ይጠቅሳል። የቀድሞ ሰልጣኞች ለማመልከቻዎች ከሚያስፈልጉ ፈተናዎች ዝግጅት እስከ ገንዘብ ድጋፍ ድረስ ያገኙ እንደነበር ይናገራል። ጄላኒ ስለ ተማሪዎቹ ስኬት ሲጠየቅ ከአዲስ ኮደር ይልቅ የተማሪዎቹ ጥንካሬን ማንሳት ይመርጣል። “በዩኒቨርስቲ ተቀባይነት በማግኘትም ሆነ በስራ ረገድ ጥሩ ውጤት ማስመዘገባቸው እውነት ነው። ነገር ግን እነዚህ ተራ ተማሪዎች አይደሉም። የ2016ቱ ቡድን አባላት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ናቸው። የተመለመሉትም በትምህርት ሚኒስቴር ነው። ከመላው ኢትዮጵያ የ12ኛ ክፍል ማትሪክ ተፈታኞች ከፍተኛውን ውጤት ካስመዘገቡት ሶስቱ ውስጥ ሁለቱ በአዲስ ኮደር ተሳትፈዋል። ከመላው ሀገሪቱ ሁለተኛ የወጣው እና ከደብረማርቆስ የመጣው ዩሴፍ እናውጋው በአዲስ ኮደር ነበር ። ለዩኒቨርስቲ መግቢያ በሚያስፈልገው ፈተና እና ማመልከቻ ላይ ጥሩ ሰርቷል። ማመልከቻውን ሀርቫርድ፣ ኤም .አይ. ቲ፣ ፕሪንስተን እና ኮሎምቢያ ተቀብለውታል። አሁን MIT ገብቷል። በዘንድሮው የአዲስ ኮደር የክረምት ስልጠና የመምህራን ረዳት ሆኗል። 

Äthiopien Summer Shool Addis Coder in Addis Abeba
ምስል Addis Coder

ከመላው ሀገሪቱ ሶስተኛ የነበረው የደሴው ዮናታን ወሰንየለህም አዲስ ኮደር ነበር። አሁን ጥቁር አንበሳ የህክምና ትምህርት ቤት እየተማረ ነው ግን በቅርቡ ካይስ በተሰኘው የደቡብ ኮሪያ ትልቅ የኢንጂነሪንግ ዩኒቨርስቲ የመማር ዕድል አግኝቷል። የቅድመ ምረቃ ትምህርቱን ለመከታተል በሁለት ሳምንት ውስጥ ወደ ደቡብ ኮሪያ ይበራል። ማጥናት የሚፈልገው ኤልክትሪካል ኢንጂነሪንግ ነው።  የትምህርት ዕድሉ አስናቂ ቢሆንም ተማሪዎቹም አስናቂ መሆናቸውን መናገር እፈልጋለሁ። የትኛው አዳጊ ነው በክረምት እረፍት መውሰዱን ወይም መጫወቱን ትቶ የአንድ ወር የኮዲንግ እና የአልጎሪዝም ስልጠና የሚወስደው? የትኛው አዳጊ ነው ማርክ ባይሰጥበትም፤ ሰርትፍኬት ባይኖርበም ለስልጠና ፍቃደኛ የሚሆነው? እንዲህ የሚያደርጉ አዳጊዎች የተለመዱ አይነት አይደሉም። እነዚህኞቹ በጣም ተነሳሽነት ያላቸው ናቸው። ”  

Äthiopien Summer Shool Addis Coder in Addis Abeba
ምስል Addis Coder

ኢትዮ-አሜሪካዊው ጄላኒ እና ተባባሪዎቹ ዘንድሮም ለሶስተኛ ጊዜ ስልጠና እየሰጡ ነው። በዚህ ዓመቱ ስልጠና ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ 150 ተማሪዎች ስለ ኮምፒውተር ሳይንስ መሰረታዊ ዕውቀቶችን እየቀሰሙ ይገኛሉ። የዛሬ ሁለት ዓመት እንደነበረው ሁሉ በዘንድሮውም ስልጠና የዋና አስተማሪነቱን ሚና የሚከወኑት ሶስት ሰዎች ናቸው። 

በሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) ምርምር የተከበረ ስም ያላት ኢትዮጵያዊቷ ዶ/ር ትምኒት ገብሩ ወጣቶቹን ለማስልጠን በድጋሚ ሀገሯ ከትማለች። ጄላኒ እና ከስታንፎርድ ዮኒቨርስቲ የመጣው ዳንኤል ካንግ ሌሎቹ መምህራን ናቸው። እነዚህን መምህራን የሚያግዙ 20 ረዳት አስተማሪዎች በዘንድሮው ስልጠና እየተሳተፉ ነው። ከረዳቶቹ ውስጥ የቀድሞ የአዲስ ኮደር ሰልጣኞች ባስይላል ኢማና እና የደብረ ማርቆሱ ዮሴፍ እናውጋው ይገኙበታል። 
ደቡብ ኮሪያ በመሆኑ ይህን ዕድል ያላገኘው ዳዊት በአዲስ ኮደር እየሰለጠኑ ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለመጪው የኮሌጅ ህይወታቸው ትልቅ ስንቅ ይዘው የሚወጡበት እንደሚሆን እምነት አለው። 

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ 

አርያም ተክሌ