1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮትዲቯር፤ የሞት ሽረት ፍትጊያ

ዓርብ፣ መጋቢት 23 2003

የአላሳኔ ዋታራ ታማኝ የሆኑት አማጺያን ቤተመንግስት ደጃፍ ደርሰዋል። በምርጫ የተሸነፉት ሎረን ባግቦ ምናልባት በሃይል ከስልጣናቸው ሊወገዱ የሚችሉበት ሰዓት የተቃረበ ይመስላል። ውጊያው በአቢጃን ቤተመንግስት አቅራቢያ ተፋፍሟል።

https://p.dw.com/p/REfX
ምስል picture-alliance/landov

የምዕራብ አፍሪካዊቷ ኮትዲቯር ቀውስ ከመሰንበቻው አይሎና ተጋግሎ ቀጥሏል። ዛሬ አቢጃን ቤተመንግስት አቅራቢያ ከፍተኛ ውጊያ ሲደረግ ነው የዋለው። ባለፈው ህዳር ወር በተካሄደው ምርጫ የተቃዋሚው ወገን የሆኑት አላሳኔ ዋታራ ቢያሸንፉም ፕሬዝዳንት ሎረን ባግቦ ከወንበሬ የሚነቀንቀኝ የለም ብለው ለገላጋይ እንዳስቸገሩ ነበር ያለፉትን አራት ወራት የዘለቁት። የተባበሩት መንግስታት አሸናፊነታቸውን በይፋ የተቀበለላቸው አላሳኔ ዋታራ ከአቢጃን ቤተመንግስት ለመግባት በዲፕሎማሲያዊው ጥረት ላይ ታች ቢሉም በባግቦ እምቢተኝነት የተነሳ እሳቸውም ሀገሪቱም መረጋጋት ሳይችሉ ቀርተዋል። በመጨረሻም የአላሳኔ ዋታራ ደጋፊ የሆኑት አማጺያን በምርጫ የተገኘውን ወንበር በሃይል ሊያስከብሩ ወደ አቢጃን መገስገስ ጀመሩ። ድል እየቀናቸው ሄዶ ዛሬ አቢጃን ቤተመንግስትን በተኩስ እሩምታ እያንኳኩ ናቸው። መሳይ መኮንን የኮትዲቯርን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተ ዘገባ አሰናድቷል።

በእርግጥ የባግቦ ፍጻሜ የደረሰ ይመስላል። በመጨረሻው ሰዓት ሁሉም ነገሮች ለባግቦ ጀርባቸውን መስጠታቸው አልቀረም።ላለፉት አራት ወራት ከጎናቸው የነበሩት 50 ሺህ ያህል ወታደሮቻቸው ሳይቀር የመሳሪያቸውን አፈ ሙዝ አዙረዋል። አሁን አጠገባቸው የቀሩት ቁጥራቸው 2000 የሚሆኑ ወታደሮች የሚገኙበት ታማኝ የሪፑብሊካን ጠባቂ የተሰኘው ልዩ ሃይል ብቻ ነው። ይህ ሃይልም ቢሆን የቀናት ጉዳይ እንጂ የባግቦን የስልጣን እድሜ የማራዘም አቅሙን ካሟጠጠበት ደረጃ ላይ ይገኛል። ምናልባት ጥቂት ሰዓታት ነገሮች በቅጽበት ሊለዋወጡ እንደሚችሉ ይገመታል። ወንበሩን የሙጥኝ ብለው የሰነበቱት ሎረን ባግቦ በሰላም እንዲለቁ የተደረገው ጥረት በእርግጥ አልተሳካም። ዲፕሎማሲያዊ ሩጫውና የማዕቅብ ጫናው ባግቦን የሚያንበረክኩ ሊሆኑ አልቻሉም። ሰሜኑን የኮትዲቯር ክፍል በእጃቸው ያስገቡት አማጺያን ከዚህ በኋላ ነበር ጠመንጃቸውን አንስተው ባግቦን ለመጣል መገስገስ የጀመሩት። የኮትዲቯር አማጺ ሃይል በሚል አዲስ ስያሜ የባግቦን ፍጻሜ ለማቃረብ ግስጋሴ የጀመሩት አማጺያን በሳምንታት ውስጥ በለስ እየቀናቸው ከባግቦ ደጃፍ ደረሱ። የፖለቲካው መዲና የሆነችውን ያማሱኩሮንና በዓለም የካካዋ ምርት ግንባር ቀደም የሆነችዋን የወደብ ከተማ ሳን ፔድሮን በቁጥጥራቸው ስር አስገቡ። ትላንት ምሽት ባግቦ ከመሸጉበት የአቢጃን ቤተመንግስት ደረሱ። ዛሬ በአማጺያኑና በባግቦ የቤተምግስቱ ሃይሎች መሃል ውጊያው ተፋፍሞ ቀጠለ። በእርግጥ ባግቦ ከቤተመንግስት ይኑሩ አልያም ሀገር ጥለው ይውጡ የሚታወቅ ነገር የለም። ትላንት አማጺያኑ ከአቢጃን ከመቃረባቸው በፊት ረቡ ምሽት የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ባግቦ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥሏል። በተባበሩት መንግስታት የናይጄሪያ አምባሳደር ጆይ ኦጉው ማዕቀቡ ባግቦ በአስቸኳይ ስልጣኑን እንዲለቁ የሚያስገድድ ነው ይላሉ።

Elfenbeinküste Fernsehrede von Alassane Ouattara
አላሳኔ ዋታራምስል dapd

«የውሳኔ ሀሳቡ ማዕቀብ የተጣለበት አገዛዝ ላይ የበለጠ ጫና የሚፈጥር ሲሆን በአንድ ድምጽ ባግቦ ስልጣኑን ለፕሬዝዳንት ዋታራ እንዲያስረክቡና የህዝቡን ፍላጎት እንዲያከብሩ የሚያደርግ ነው»

የመንግስታቱ ድርጅት በዚሁ ውሳኔው ባግቦ፤ ባለቤታቸው ወይዘሮ ሲሞኔ እና ሶስት ታማኞቻቸው ከሀገር እንዳይወጡና ንብረታቸው እንዲታገድ የሚደርግ ነው። ውሳኔው በእርግጥ ከባግቦ አንጻር የረፈደ ነው። አማጺያኑ ባግቦ የተም ሳይሄዱ ሊይዝዋችው የመቻላቸው አይቀሬነት አሁን ላይ በስፋት እየተሰማ ነው። ዛሬ አቢጃን ቤተመንግስት የተጧፏው ውጊያ የባግቦ ደጋፊ የሆኑት አማጺያን ድል ሊያደርጉ እንደሚችሉ ፍንጭ አሳይቷል። 2000ሺህ የሚሆኑት የባግቦ የመጭረሻ ሃይሎች አማጺያኑን መመከታቸው ሲበዛም ያጠራጥራል። የአሸናፊው ፕሬዝዳንት አላሳኔ ዋታራ እንደሚሉት አማጺያኑ ለባግቦ ሲሰራ የነበረን ቴሌቪዥን ጣቢያ ተቆጣጥረውታል። ጸሀይ ለባግቦ እየጠለቀች ባለችበት በዚህን ሰዓት የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሁለቱም ሃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን እየገደሉ መሆኑን በመጥቀስ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጠይቋል። በለስ እየቀናቸው ያሉትና ምናልባትም ቀጣዩ የኮትዲቯር ፕሬዝዳንት የሚሆኑት አላሳኔ ዋታራ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳይፈነዳ አማጺያኑ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ሆኖም ባግቦን በሚገባቸው ቋንቋ አናግሮ ማባረሩ ያልተፈለገ ግን አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል ዋታራ።

Elfenbeinküste Gbagbo
ሎረን ባግቦምስል AP

«አገራችን በታሪኳ ከአንድ ዓብይ የለውጥ ምዕራፍ ላይ ደርሳለች ። ሎሮን ባግቦ ሥልጣኑን በሰላም እንዲለቁ ምንም እንኳ በዛ ያለ ተማፅኖ ቢቀርብላቸውም የመረጡት የኃይል እርምጃ ነው ። ይህን የኃይል እርምጃ በሀገራችን ከነአካቴው ለማስቆም የሪፓብሊኳ ኃይሎች ቆርጠው በመሳት ዲሞክራሲን ፈር ለማስያዝና የህዝቡ ውሳኔ እንዲከበር ለማድረግ ወስነዋል »

የአቢጃን ቤተምንግስት በውጊያ በተወጠረበት በዛሬው ዕለት አሻፈረኝ ብለው ለወራት ያስቸገሩት ሎረን ባግቦ የት እንዳሉ የሚሰሙት ዘገባዎች የተምታቱ ናቸው። አንዳንድ ወገኖች ባግቦ ሀገር ጥለው ሳይፈረጥጡ አይቀሩም ሲሉ የዋታራ ቃል አቀባይ ፓትሪክ አቺ ግን ባግቦ ቸዋታው ያበቃ ስላልመሰላቸው የትም አይሄዱም። እርግጠኛ ነኝ አሁንም ከመኖሪያ ቤታቸው ይገኛሉ ብለዋል። በኮትዲቯር የፈረንሳይ አምባሳደርም ባግቦ ከቤተመንግስት እንዳሉ መግለጻቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። ሎረን ባግቦ በመጨረሻው ሰዓት ወዳጆቻቸው ሳይቀሩ ፊት ነስተዋቸዋል። አንዳንዶ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ባግቦ አቢጃን ያሉ የወዳጆቻቸውን ኤምባሲዎች ለመሸሸግ ጠይቀው እሺ የሚላቸው አላገኙም። አንዳንድ ሹሞቻቸው በየኤምባሲው እየተሸሸጉ የጦር አዛዦቻቸውም አማጺያንን እየተቀላቀሉ ናቸው። በምርጫውም በወታደራዊ ድሉ የቀናቸው አላሳኔ ዋታራ በመጨረሻም ለባግቦ ሰዎች መልዕክት አስተላልፈዋል። እያመነታችሁ ያላችሁም ጊዜው ሳይረፍድ ተቀላቀሉ። ሀገራችሁ ጥሪ አድርጋላችኃለች። ብለዋል ዋታራ።

መሳይ መኮንን

ተክሌ የኋላ