1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮት ዲቯር እና የሎውሮ ባግቦ ተጛዳኞች መፈታት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 1 2005

የኮት ዲ ቯር የፍትሕ ሚንስቴር በእስር ከሚገኙት የቀድሞው የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሎውሮ ባግቦ ደጋፊዎች መካከል የቅርብ ረዳቶቻቸው ናቸው የሚባሉትን 14 ሰሞኑን በጊዜያዊ ሁኔታ ፈታ። ግለሰቦቹ የተፈቱበት ርምጃ በሀገሪቱ ለተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሂደት ዓቢይ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ቢገምቱም፣ የባግቦ ደጋፊዎች በቂ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/19Lhi
ምስል Getty Images

የኮት ዲ ቯር መንግሥት በ2010 ዓም በሀገሩ ከተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በኋላ በተሸናፊው የቀድሞ ፕሬዚደንት ሎውሮ ባግቦ እና ባሸናፊው አላሳ ዋታራ ደጋፊዎች መካከል ፣ ባግቦ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ዝግጁ ባልሆኑበት ጊዜ በ2011 ዓም ላጭር ጊዜ ከተካሄደው ውጊያ በኋላ ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ጥርጣሬ 100 ሰዎች የባግቦ ደጋፊዎችን አስሮዋል። በዚያን ጊዜው ደም አፋሳሽ ግጭት ወደ  3000 የሚጠጋ ሰው ሲገደል፣   በመቶ ሺ የሚቆጠር ደግሞ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎዋል ወይም ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰዶዋል።
የኮት ዲ ቯር ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ከታሰሩት መካከል ለባግቦ ቅርበት አላቸው የተባሉ 14  በጊዚያዊነት መፈታታቸውን አስታውቋል። ሆኖም፣ ተፈተዋል የተባሉት ግለሰቦች ክስ እንደሚቀጥል እና ፍርዳቸውም እስከተያዘው ዓመት መጨረሻ እንደሚሰጥ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
ከተፈቱት መካከል ወንድ ልጃቸው ሚሸል ባግቦ ፣ የኮት ዲ ቯር ሕዝብ ግንባር፣ በምሕፃሩ የኤፍ ፔ ኢ ምሪ ፓስካል አፊ ንጌሳን እና የቀድሞው የምዕራብ አፍሪቃ ባንክ ዋና አስተዳዳሪ ፊሊፕ ኦንሪ ዳኩሪ ታብሌ ይገኙባቸዋል።   
የ14ቱ መፈታትን የፖለቲካ ፓርቲዎች በደስታ ተቀብለውታል። ከነዚሁ አንዱ የሆነው የቀድሞው ፕሬዚደንት ሎውሮ ባግቦ የኮት ዲ ቯር ሕዝብ ግንባር፣ በምሕፃሩ ኤፍ ፔ ኢ  ግን መንግሥት ከዚህ የተሻለ ተጨማሪ ርምጃ መውሰድ አለበት ይላል። የኤፍ ፔ ኢ   ዋና ፀሐፊ ሪሻር ኮጆ፣
«ይህ ርምጃ በቂ ነው ብየ አልገምትም። ግለሰቦች ከምርጫው በኋላ የታሰሩበት ምክንያት ፖለቲካዊ ነውና። እና እኔ እንደምገምተው፣ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞቹን ነፃ ከመልቀቅ ባሻገር ሌላ ተጨማሪ ጠቅላላ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት የሚያስቸለውን የፖለቲካ ርምጃ መውሰድ አለበት።  ይህ ውጥረቱን ማርገብ እና ዕርቀ ሰላም ማውረድ ወደሚቻልበት ሁኔታ የሚያመራ ጥሩ መንገድ ነው። »
የኮት ዲ ቯር ፕሬዚደንት አላሳ ዋታራ የአሠርተ ዓመቱ ፖለቲካዊ ውዝግብ በህብረተሰቡ ውስጥ የተወውን መከፋፈል ለማስወገድ የጀመሩበት ሙከራ የሀገሪቱን ማህበራዊና ፖለቲካዊ መርጋጋት ያወርዳል በሚል ተስፋ ማድረጋቸውን የመንግሥቱ ቃል አቀባይ ብሩኖ ኮኔ ገልጸዋል።

ይሁንና፣ የኮት ዲ ቯር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ቃል አቀባይ ዱምቢያ ያኩባ ግለሰቦቹ በጊዚያዊነት የተፈቱበት ውሳኔ እንዲነሳ ጠይቀዋል።
«ግለሰቦቹ የተፈቱበት ምክንያት ሕጉን መሠረት ያደረገ ሳይሆን ፖለቲካዊ ምክንያት ነው ያለው። በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ምክንያትን ባላስቀደመ፣ በዚህ ፈንታ የፍትሑን ነፃነት እና ገለልተኝነትን በጠበቀ አሰራር  በሚወሰድ ርምጃ አማካኝነት ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ እንፈልጋለን። »
ዱምቢያ ያኩባ  እንደሚሉት፣ የኮት ዲ ቯር መንግሥት የባግቦ የቅርብ ረዳቶች በሚል ያሰራቸውን ግለሰቦች እስካልፈታ ድረስ በሀገሪቱ ዕርቀ ሰላም መውረዱን ይጠራጠሩታል። በፈረንሣይ እና በተመድ ጦር የተረዱ የአላሳን ዋታራ ደጋፊዎች ባግቦን በ2011 ካሰሩ በኋላ ባግቦን ዘ ሄግ ለሚገኘው ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት አስረክበዋል። ባግቦ በ2011 ግጭት ወቅት በስብዕና አንፃር ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው ባግቦ በዚያ ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ነው። ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በባግቦ ባልተቤት ሲሞንም ላይ ተመሳሳይ ክስ በመመስረት የእስር ማዘዣ አውጥቶዋል። የዋታራ መንግሥት ሲሞንን ለፍርድ ቤቱ በማስረከቡ ጥያቄ ላይ እስካሁን መልስ አልሰጠም።

Elfenbeinküste - Simone Gbagbo
ሲሞን ባግቦምስል Getty Images
Laurent Gbagbo
ፍርዳቸውን የሚጠባበቁት የቀድሞው ፕሬዚደንት ሎውሮ ባግቦምስል picture-alliance/dpa
Senegal Dakar ECOWAS Gipfel Ouattara
ፕሬዚደንት አላሳ ዋታራምስል Reuters


አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ