1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮንጎና የሰላሙ ስምምት ይዞታ፣

ዓርብ፣ መጋቢት 6 2005

ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ 11 የአፍሪቃ መንግሥታት፣ የኪንሻሳ ጭምር፤ አዲስ አበባ ውስጥ ለኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ሰላም የሚበጅ ውል መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። ሁሉም በጋራ ፣ ለኮንጎ ሰላምና ጸጥታ እንዲሠፍን አጥብቀው ሲሹ ፣

https://p.dw.com/p/17ykX
ምስል Reuters

በዋናነት የፈለጉት በምሥራቃዊው ኮንጎ፤ የሰሜን ኪቩን ጠ/ግዛት አንድ ዓመት ገደማ ያህል ያመሠቃቀለው ውጊያ ፣ ለዘለቄታው መፍትኄ እንዲገኝለት ነው። ውስብስብ ስለሆነው የምሥራቅ ኮንጎ የሰላም ጥረት የሆነው ሆኖ ኑዋሪዎቹ እስከዚህም የሚያውቁት ጉዳይ የለም። ስለኮንጎው የሰላም ስምምነት ፣ የዶቸ ቨለ ባልደረባ፣ ፊሊፕ ሳንድነር ያቀረበውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

Foto: John Kanyunyu / DW
ምስል DW/J.Kanyunyu

በምሥራቅ ኮንጎ አምና ባገረሸው ውጊያ ሳቢያ፣ ኮብልለው ሩዋንዳ የገቡት፣ ሊና ባሴንጌ የተባሉት የአካባቢው ተወላጅ፤ ስለ ሰላም ሂደት ሲወሳ ምን ላይ ማትኮር እንደተፈለገ የሚያውቁት ጉዳይ አለመኖሩን ነው እንዲህ ሲሉ ነው የገለጡት።

«ሲወሳ ሰምተናል፤ ግን ምንን እንደሚመለከት የምናውቀው ነገር የለም። የምንፈልገው ቢኖር፣ ሰላም ነው»።

ዓለም አቀፉ ድርድር ፣ የሰሜን ኪቩን ተወላጆች ችግርና ዕጣ ፈንታቸውን ወደ ጎን ገፍቶት ይሆን? የኮንጎ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት የዓለም አቀፉ የአወዛጋቢ አካባቢዎች አጥኚ ቡድን ባልደረባ Thierry Viercoulon---

«በሰሜን ኪቩ የሆነው ምንድን ነው---አዎ፤ በዲፕሎማሲው ውይይት በኮንጎም መንግሥትም ቢሆን እንዲሁ ችላ ነው የተባለው። የኪንሻሳ መንግሥት፣ እምብዛም በጉዳዩ አልተጨነቀበትም። ጣልቃ ለመግባትምእስከዚህም አልፈለገም። እናም ታጣቂዎቹ ኃይላት በነጻ እንዲንቀሳቀሱ ትቶአቸዋል። »

Gespräche zwischen Kongo und M23 in Kampala
ምስል DW/J.Kanyunyu

ኤም 23 በመባል የታወቁት አማጽያን ለድርድር አዲስ አበባ እንዲገኙ አልተጋበዙም ነበር። በምሥራቅ ኮንጎ እንዳሻቸው በመሠማራት አካባቢው ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ሰበብ መሆናቸው እሙን ነው። በመሆኑም የኮንጎ መንግሥት ካለፈው ታኅሳስ አንስቶ በአጎራባች ሀገር በዩጋንዳ ሲያካሂድ የነበረውን ድርድር ፣ዛሬ ካምፓላ ውስጥ ውል በመፈራረም እልባት እንዲያገኝ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። የኮንጎ መንግሥት ቃል አቀባይ ላምበርት ሜንደ በበኩላቸው ከመንግሥታቸው በኩል ሳይሆን ከሌላው ተደራዳሪ በኩል ችግር መኖሩን እንዲህ ጠቁመዋል።

«መንግሥት ተግባሩን አከናውኗል። ውሉ ይፈረም ዘንድ፣ ከሌላው አካል ይጠባበቅ ነበር ምን እንድርግ? ተፈራራሚ ሲታጣ እኛው ሌላ እንጥራ! የውል ተፈራራሚ መኖር ነበረበት ግን አልተገኘም። ለፊርማው የሚፈለጉት እርስ-በርስ በመራኮት ጊዜ አላገኙም።»የ M-23 አማጽያን፤ የጦር ኃይል አመራር አባላት፤ በአንጃዎች በመከፋፈላቸውና ከመካከላቸውም አንደኛው ቦስኮ እንታንጋንዳ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መርማሪ ፍርድ ቤት የሚፈለጉ መሆናቸው ሁኔታውን ይበልጥ እንዳወሳሰበው ይገኛል። አሁንም ቲሪ ቪርኩሎን--

Kongo M23 Rebellen ziehen aus besetzen Gebieten
ምስል AP

«የሚፈረመው ውል፣ ለ M-23 ተዋጊዎች ምህረት ተደርጎላቸው ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር እንዲቀላቀሉ የሚል ነው። እንዲህ ዓይነቱ ውል ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ተፈርሞ ነበር። ከ CNDP ም ጋር ተመሳሳይ ውል ነበረ የተፈረመው። መንግሥት ያን ከመሰለው ውል ምን የሚያተርፈው ነገር ይኖራል? »

የኮንጎ ዴሞካራቲክ ሪፓብሊክ መንግሥት የሆነው ሆኖ፣ በጉዳዩ ቸልተኝነት ያሳየበት ምክንያት ሳይኖረው አይቀርም።

«እንዲህ ዓይነቱ ቸልተኝነት የመንግሥት ስልት ሊሆን ይችላል። የ «ሳዴክ» ወታደሮች በውሉ መሠረት ገብተው እንዲሠማሩ ለማብቃት! የኮንጎ መንግሥት ጊዜ ለማግኘት ነው የሚጥረው፣ አቅሙ እስኪጠናከር!»

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ