1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደፊት መራመድ የተሳነው የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር

ሰኞ፣ ነሐሴ 11 2007

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ከተቀናቃኛቸው ከአማፅያኑ መሪ ሪክ ማቻር ጋር ዛሬ ይፈርማሉ ተብሎ ይጠበቅ የነበረውን የሰላም ውል ሳይፈርሙ ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል ። ኪር የሰላም ስምምነቱን ለመፈረም ተጨማሪ ሁለት ሳምንታት መጠየቃቸውን አደራዳሪው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን፣ በምህፃሩ ኢጋድ አስታውቋል ።

https://p.dw.com/p/1GGsr
Südsudan-Verhandlungen vorerst gescheitert
ምስል Reuters/Tiksa Negeri

[No title]

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የሰላም ስምምነት ሳይፈርሙ እንደቀረ ተዘገበ ። የደቡብ ሱዳን አደራዳሪዎች እንደተናገሩት ኪር የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ኢጋድ ያቀረበው የሰላም ስምምነት ያልፈረሙት ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል ሲሉ ነው ። አደራዳሪው አምባሳደር ስዩም መስፍንን ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው የኪር ቡድን የሰላም ውሉን ከመፈረሙ በፊት የሁለት ሳምንት ጊዜ እንደሚያስፈልገው አስታውቋል። የሰላም ውሉን የደቡብ ሱዳን አማፅያን መቀበላቸው ተዘግቧል ።ስዩም የመንግሥት ተደራዳሪዎች ከ15 ቀን በኋላ አዲስ አበባ ተመልሰው እንደሚመጡም ስዩም ተናግረዋል። ዛሬ ከቀትር በኋላ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተቀናቃኝ መሪ ሪክ ማቻርና የደቡብ ሱዳን ገዥ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ፓጋን አሙም የሰላም ስምምነት ተፈራርመው ነበር ። ሆኖም ሸምጋዮች እንዳሉት አሙም መንግሥትን አይወክሉም ።ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የፊርማዉን ሥነ ስርዓት ከተከታተሉ በኋላ ከተቀናቃኛቸዉ ከሪክ ማቻር ጋር መጨባበጣቸዉ ተመልክቶአል።

Südsudan Friedensverhandlungen Addis Abeba
ምስል DW/G. T. Hailegiorgis

በሌላ በኩል በ 20 ወራት የርስ በርስ ጦርነት ሰበብ ወደ 200 ሺ ሲቪል ደቡብ ሱዳናዉያን በተመድ ማዕከል ተጠልለዉ እንደሚገኙ የመንግሥታቱ ድርጅት ዛሬ ገለፀ። 199,602 የደቡብ ሱዳናዉያን ሲቪሎች በተመድ በሚገኝ ስምንት የሰላም አስከባሪ ማዕከሎች ዉስጥ ደህንነታቸዉ የተጠበቀ ሲሆን በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ቁጥራቸዉ በሶስት እጥፍ መጨመሩ ተመልክቶአል። ይህ የተመድ ዘገባ ይፋ የሆነዉ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ላይ ለድርድር በተቀመጡበት በአሁኑ ወቅት መሆኑ ነዉ። የመንግሥታቱ ድርጅት የደቡብ ሱዳን 70 በመቶ ነዋሪ ወደ 12 ሚሊዮን ሕዝብ ርዳታ እንደሚያስፈልገዉ ገልፆአል። በእርስ በርሱ ጦርነት ሰበብ 2,2 ሚሊዮን ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎአል፤ 600 ሺ የደቡብ ሱዳን ነዋሪ ደግሞ በጎረቤት ኢትዮጵያ፤ ኬንያ፤ ሱዳንና ዩጋንዳ ዉስጥ በሚገኙ የስደተኛ መጠለያዎች እንደሚገኝም ተገልፆአል።

Südsudan Präsident Salva Kiir
ምስል picture-alliance/dpa/P. Dhil

ሁለቱ ወገኖች፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያስቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ዛሬ እኩለ ሌሊት ሳያበቃ በፊት ለውዝግባቸው ዘላቂ መፍትሔ የሚያስገኘውን የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማዕቀብ እንደሚጣ ማሳሰቢያ ተስጥቷቸው ነበር ። ድርድሩ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የአዲስ አበባውን ወኪላችንን ስቱድዮ ከመግባታችን በፊት ጠይቀነዉ ነበር።

ጌታቸው ተድላ ኃይለጊዮርጊስ

አርያም ተክሌ

ኂሩት መለሰ