1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወዳጅና ጠላት ያለየበት ጦርነት

ሰኞ፣ ሐምሌ 27 2007

ምዕራባዉያን መንግሥታት ISISን በምድር የሚወጉትን የኢራቅና የሶሪያ ኩርዶችን በቀጥታ፤የቱርክ ኩርዶችን ደግሞ በተዘዋዋሪ ያስታጥቃሉ።ቱርክ ኩርዶችን ትወጋለች፤ ኩርዶችም ቱርክን።ምዕራባዉን መንግሥታት፤ቱርክና አረቦች የደማስቆ ገዢዎችን የሚወጉ አማፂያንን ይደግፋሉ።ISISም የደማስቆ ገዢዎችን ይወጋል።

https://p.dw.com/p/1G9Aj
ምስል picture-alliance/AP Photo/B. Ozbilici

ወዳጅና ጠላት ያለየበት ጦርነት

የዋሽግተን፤ ብራስልስ ጥብቅ ወዳጆ፤የሪያድ፤ ዶሐ፤አማን፤ ኤርቤል ታማኞቻቸዉን አስቀድመዉ የቴሕራን-ደማስቆ ጠላቶቻቸዉን እየወጉ፤እያስወጉ፤ ደሞ በተቃራኒዉ ከቴሕራን፤ ደማስቆ፤ ጠላቶቻቸዉና ጋር እንደ ወዳጅ ባንድ አብረዉ ISISን ይዋጋሉ።ተቃራኒዎችን እንደ ጠላት እያዋጋ፤ እንደ ወዳጅ ባሳበረዉ ጦርነት አልተካፈለችም እንዳትባል ተዋጊዎችን እየረዳች፤ ተካፍላለች እንዳይባል ጦር አላዘምትም እያለች ስታቅማማ የነበረች አንድ ያካባቢዉ ሐገር ነበረች።ቱርክ።ባለፈዉ ሳምንት ግራ-አጋቢ አቋሟን ቀይራ፤ከግራ አጋቢዉ ጦርነት በሁለት ተቃራኒ ግንባር ተሞጀረች።

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ዳብሊዉ ቡሽ እንደ ፊት አዉራሪ፤ የያኔዉ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር እንደ አጋፋሪ ኢራቅን ሲወርሩ አንድ የቱርክ ፖለቲከኛ ጠይቀዉ ነበር።« ሳዳም ሁሴን በርግጥ ከሥልጣን ይወገዳሉ፤ ግን አዲሱ ለዉሬንስ ማን ይሆን?» ብለዉ።

ጀላቢያ፤ ጥምጣም፤ ቁድራቸዉን ለብሰዉ፤ ሴሞ (ጎራዴያቸዉን) ታጥቀዉ አረብኛዉን ሲንያቆረቁሩት-አረብ፤ ሱፍ-ከራባት ለብሰዉ-በእንግሊዝኛ ነገር ሲቆላልፉ-ዲፕሎማት፤ ሸሚዝ፤ ቁምጣቸዉን አጥልቀዉ መሬት ሲቆፍሩ-የሥነ-ዕብን ተመራማዊ (አርኪዎሎጂስት)፤የጦር መለዮ፤ ማዕረጋቸዉን ሲያጠልቁ-ሻምበል ይመስሉ ነበር።ቶማስ ኤድዋርድ ለዉሬንስ።ወይም ለዉሬንስ-ዘ-አረቢያ። ሁሉንም ነበሩ።ከሁሉም በላይ ብሪታንያዉ።

ታላቅዋ ብሪታንያ መካከለኛዉ ምሥራቅን በተለይም ዛሬ እስራኤል፤ ፍልስጤም፤ ዮርዳኖስ፤ ሶሪያ፤ ሳዑዲ አረቢያ፤ ኢራቅ ተብለዉ የሚጠሩትን ሐገራት ከቱርክ እጅ ፈልቅቃ ለመዉሰድ ለነበራትን የረጅም ጊዜ ዕቅድ ገቢራዊነት አረቦችን ከጎኗ ያሰለፉ ብልጣ-ብልጥ ሰላይ፤ በሳል ዲፕሎማት፤ የጦር መኮንን ነበሩ።

PKK Kämpfer
ምስል picture-alliance/dpa/Y. Renoult

በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ወቅት በለዉሬንስ አግባቢነት ከብሪታንያ ቅኝ ገዢ ጦር ጋር የዘመተዉ የአረብና የኩርዶች ጦር የቱርክን ጦር በየሥፍራዉ ሲገዘግዝ ቆይቶ ጥቅምት 1918 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ደማስቆን ሲቆጣጠር የአረብ-ቱርኮች ጠብ ከረረ።አረቦች ለአዲስ ገዢዎቻቸዉ አደሩ። የዚያኑ ያክል የፍልስጤም እና የኩርድ ሕዝብ የነፃነት ሕልም ቢያንስ እስከ ዛሬ እንደበነነ ቀረ።

አረቦችን ከቱርክ ቀምቶ ለብሪታንያ በብሪታንያ በኩል ለዩናይትድ ስቴትስ ያስረከበዉ ጦርነት ባበቃ በ85ኛ ዓመቱ-በ2003 የቱርኩ ፖለቲከኛ እንደዘበት የወረወሩት ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ በርግጥ የለዉም።መልዕክቱ ግን ኢራቅን ከኢራቃዊዉ ገዢ ቀምቶ ለዋሽግተኖች ለማስረከብ፤ አረብን ሐይማኖት፤ ባሕል፤ ከሚጋሩት ቱርኮች ቀምቶ ለብሪታንያዎች፤ በብሪታንያ በኩል ለአሜሪካኖች ያስረከበዉን አይነት ሴራን-የሚያቀነባብረዉ ማነዉ ነዉ-ነበር።ላሁኑ አላወቀንም።

የዋሽግተንና የለንደን መሪዎች በ2003 ኢራቅ ላይ የለኮሱት ጦርነት ግን እስከያኔ-አረብን ከኩርድ፤ ሱኒን ከሺዓ፤ ክርስቲያንን-ከያዚዲ ቀይጣ ታኖር የነበረችዉን ሐብታም፤ ሥልታዊት፤ታሪካዊት ሐገርን የአሸባሪዎች መፈልፈያ፤ የሽብር ቋት፤ የእልቂት አብነት እንዳደረጋት መቀጠሉ ግልፅ-እርግጥም ነዉ።የኢራቅ መጥፋት፤ አንድነቷ መሸራረፍ፤ ሕዝቧ ማለቅ የጀመረበት ስምንተኛ ዓመት ሲዘከር ሶሪያ ላይ የተቀጣጠለዉ የእልቂት ቋያ የመካከለኛዉ ምሥራቅን የታሪክ ጎተራ፤ የዕዉቀት፤ ሥልጣኔ ምድር፤ የአረብ ብሔረተኞችን ማዕከል ከትቢያ እየቀየጣት ነዉ።

ከአምና ጀምሮ ዓለም አቀፍ አሸባሪነቱ ዕለት በዕለት የሚዘገብበት የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS በምሕፃሩ) የፕሬዝደንት በሽር አልአሰድን መንግሥት ያስወግዳል በሚል እምነት በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ፤ በማወቅ ይሁን ባለማወቅ ከሪያድ ዶሐዎች ገንዘብ፤ ከቱርኮች መሰልጠኛ ምድር፤ ከምዕራባዉያን ዲፕሎማሲና የጦር ሜዳ ቁሳቁስ ያገኛል ይባል ይባል ነበር።

ቡድኑ የ«ረዳቶቹን» ዜጎችና ወዳጆች «መንደፍ» ሲጀምር ግን በይድረስ ይድረስ የተደራጀዉ ተዘዋዋሪ ትብብር በተቃራኒ ጎዳና ይሾር ያዘ።

ዩናይድ ስቴትስ ዓለምን አስተባብራ አሸባሪዉን ቡድን በጄት መደብደብ ከጀመረችበት አምና ጀምሮ-ቱርክ እንደ አብዛኛዉ ዓለም በተለይም እንደ ሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባልነቷ ድጋፍዋን አልነፈገችም።ድጋፏ ግን የአንካራ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ አጥኚ ሁሴይን ባግቺ እንደሚሉት በማለዘብ መርሕ ላይ የተመሠረተ ነበር።

«መንግሥት (የቱርክ)ISISን እንደሚዋጋ አስታዉቋል።ይሕ በምዕራባዉያንና በኔቶ ዘንድ ላለፈዉ ዓንድ ዓመት በግልፅ የሚታወቅ የቱርክ መንግሥት መርሕ ነዉ።ይሁንና በተጨባጭ ቱርክ ባለፉት ሁለት ዓመታት የምትከለዉ የማለዘብ መርሕ ነበር።ምክንያቱም ISIS 49 የቱርክ ዲፕሎማቶችን ከአንድ መቶ ቀናት በላይ አግቶ ነበር።በዚሕም ምክንያት ቱርክ አስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ነበረች።ይሁንና ዲፕሎማቶቹ ከተለቀቁ በሕዋላ የቱርክ ፀረ- ISIS አቋም በጣም ተጠናክሯል።»

NATO berät über Lage der Türkei
ምስል Reuters/F. Lenoir

የአንካራ መሪዎች ISISን በመዉጋትና ባለመዉጋት መሐል ቢቃረጡም የደማስቆ ገዢዎችን ለማስወገድ የሚደረገዉን ዉጊያ ከመደገፍ ግን አልቦዘኑም።የረጅም ጊዜ ጠላታቸዉን የኩርድ ሰራተኞች ፓርቲ (PKK) ሲሆን በድርድር፤ ካልሆነም በሐይል፤ የነፍጥ ዉጊያዉን ለማስቆም መጣራቸዉንም አላቋረጡም ነበር።

በቅርቡ ቱርክ በተደረገዉ ምርጫ PKKን ይደግፋል ተብሎ የሚታማዉ የቱርክ ኩርዶች ፓርቲ ያልተጠበቀ ድጋፍ ማግኘቱ፤ ምዕራባዉያን ለኢራቅና ለሶሪያ ኩርዶች በሚሰጡት ሁለንተናዊ ድጋፍ ላይ ሲታከል የኩርድ ነፃነት አቀንቃኞችን የሚያነቃ-ነዉ የሆነዉ።

የቱርክ መንግሥትና ከ1980ዎቹ ጀምሮ በደማስቆና በባግዳድ ገዢዎች እየተረዳ ቱርክን የሚወጋዉ PKK ለሰወስት ዓመታት ያደረጉትን ድርድር በምርጫዉ ማግስት ሲያፈርሱ ከኢራቅ ኩርዶች የተሰማዉ የአንካራን መሪዎች አያሰጋም ማለት አይቻልም።

ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በምዕራባዉያን መንግሥታት ድጋፍ ሰሜን ኢራቅ ኬርቤላ ላይ መንግሥት አከል-አስተዳደር የመሠረቱት የመስዑድ ባርዛኒ ማስጠንቀቂያ «ጌታዋን የተማመነች----» የሚያሰኝ፤ ከጠንካራ ሐገር መሪ ያልተናነሰ ነበር።«ቱርክ የሠላም ስምምነት ሐሳብ አቅርባ PKK ሐሳቡን ዉድቅ ካደረገዉ PKKን ለመቃወም ዝግጁ ነን።ቱርክ PKKን ለማጥፋት በሚል በኛ ላይ ጥቃት ከሰነዘረች ግን እራሳችንን ለመከላከል ዝግጁዎች ነን»

በዚሕ መሐል ነበር የISIS አባል እንደሆነ የታመነ አንድ አጥፍቶ ጠፊ ቱርክን ከሶሪያ ጋር በሚያዋስነዉ የድንበር ከተማ 32 የቱርክ ዜጎችን አጥፍቶ የጠፋዉ።ዛሬ ሁለት ሳምንቱ።እርምጃዉ አንካራ ከጦርነቱ እንድትገባ፤ ዘላቂ ስልቷንም እንድታጤን፤ ለምዕራባዉያን ግፊት እጇን እድትሰጥም ጥሩ ምክንያት ነዉ የሆነዉ።

ይሁንና የአንካራ መሪዎች ለዘላቂ ጥቅማቸዉ የሚበጀዉን ሳያሰሉ ተንደርድረዉ ከጦርነቱ አልተሞጀሩም።የቱርክ ባለሥልጣናት PKKን ለመቅጣት የሐይል እርምጃ ቢወስዱ ምዕራባዉያን ወዳጆቻቸዉ «እንዳይንጫጩ» በተለይ ከዋሽግተን መተማመኛ መያዝ ነበረባቸዉ።

አንካራዎች የሁለት ግንባር ዘመቻ ለማወጅ እንዲመቻቸዉ የPKK ሸማቂዎችም ሳይተባበሯቸዉ አልቀረም-ቢያንስ በተዘዋዋሪ።የቡድኑ ታጣቂዎች አፈነዱት በተባለ ቦምብ ሰወስት የቱርክ ወታደሮች ተገደሉ።የግድያዉ ለቱርኩ ፕሬዝደንት ለሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻን «ሳይደግስ አይጣላም» አይነት ነበር።«ብሔራዊ ፀጥታችንንና ወንድማዊ አንድነታችንን ከሚያጠቁ ሐይላት ጋር የሠላም ድርድር መቀጠል አይቻልም።»

NATO berät über Lage der Türkei
ምስል picture-alliance/dpa/J. Warnand

ወትሮም የፈረሰዉ ድርድር ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ።ጦርነቱ ቀጠለ።የቱርክ የጦር ጄቶች ኩርዶችን ለመምታት ወደ ሰሜን ኢራቅ፤ ISISን ለመዉጋት ወደ ሶሪያ ይከንፉ ያዙ።የቱርክ መንግሥት በቱርኮች ላይ የከፈተዉን ጥቃት አቁሞ ድርድሩን እንዲቀጥል ጀርመንና አንዳድ የአዉሮጳ መንግሥታት መጠየቃቸዉ አልቀረም።ዩናይትድ ስቴትስ ግን የቱርክን እርምጃ ደግፋለች።

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሐገራት ዲፕሎማቶችም ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ ባደረጉት ስብሰባ የቱርክን እርምጃ ደግፈዋል።ዋና ፀሐፊ የንስ ሽቶልተንበርግ ከተባባሪያችን ቱርክ ጎን አንቆማለን ነዉ-ያሉት።ያዉም በፅናት።

«ቱርክ ደጃፍ ላይ እና ኔቶ ድንበር አጠገብ ሥላለዉ አለመረጋጋት ለመነጋገር ዛሬ መሰብሰባችን ተገቢ ነዉ።ኔቶ ሁኔታዉን በቅርብ እየተከታተለ ነዉ።ከአባላችን ቱርክ ጎን በፅናት እንቆማለን።»

PKK ጀርመንን ለመሳሰሉ ሐገራት አሸባሪ ድርጅት ነዉ።ጀርመንን ጨምሮ ምዕራባዉያን መንግሥታት ISISን በምድር የሚወጉትን የኢራቅና የሶሪያ ኩርዶችን በቀጥታ፤የቱርክ ኩርዶችን ደግሞ በተዘዋዋሪ ያስታጥቃሉ።ቱርክ ኩርዶችን ትወጋለች፤ ኩርዶችም ቱርክን።ምዕራባዉን መንግሥታት፤ቱርክና አረቦች የደማስቆ ገዢዎችን የሚወጉ አማፂያንን ይደግፋሉ።ISISም የደማስቆ ገዢዎችን ይወጋል።ሁሉም ፀረ-ደማስቆ ናቸዉ።

የባግዳድ ገዢዎች የሳዳም ሁሴንን ቤተ-መንግሥት የተረከቡት ከዋሽግተኖች ነዉ።ዋሽግተን የቴሕራን ጠላት ናት።የባግዳድ ገዢዎች የቴሕራን፤ በቴሕራን በኩል የደማስቆ ወዳጆች ናቸዉ።በዚሕም ሰበብ ባግዳዶች-ደማስቆን አይነኩም።ዋሽግተን፤ ብራስልስ፤ የአረብ ነገስታት፤አንካራ፤-ቴሕራን፤ ደማስቆ፤ባግዳድ፤ ሒዝቦላሕ፤ ኩርዶች ISIS ን ይወጋሉ።ሁሉም የISIS ጠላት ናቸዉ።አንካራ ኩርዶችን ትወጋለች።ዋሽግተን፤ ብራስልስ፤ አረቦች ኩርዶችን ያስታጥቃሉ።የተሳከረ ጦርነት።ግን ሚሊዮኖች ያልቃሉ።ይሰደዳሉ።እስከመቼ-አይታወቅም።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ