1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣት ሙስሊሞች እስልምናና ምኞታቸው

ዓርብ፣ ጥር 27 2008

በተለይ በሰሜን አፍሪቃ እና በመካከለኛው ምስራቅ ካለፉት አመታት አንስቶ በርካታ ሀገራት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ። ተስፋ ላጡት በእነዚህ ሀገራት የሚኖሩ በርካታ ወጣቶች መፅናኛቸው እምነታቸው ብቻ ነው። ይሁንና የትኛውን እስልምና አቅጣጫ ይምረጡ? ከዚህ በፊት የሚያውቁትን ወይስ አክራሪዎች የሚሰብኩትን?

https://p.dw.com/p/1HqKL
Afrikaner in Brasilien Senegalesische Migranten
ምስል DW/L. Nagel

ወጣቶች ሙስሊሞች እስልምናና ምኞታቸው

በየትኛውም የአለማችን ክፍል ይሁን በአሁኑ ሰዓት ከሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ የአንድ ሐይማኖት ስም በተደጋጋሚ ይጠራል። እስልምና። ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ነጻነታቸው እየተገፈፈ እንደሆነ ይናገራሉ። በስራ አጥነት፣ በጦርነት እና በቀውስ ተስፋ ለቆረጠው ሙስሊም ወጣት ምንም እንኳን የመጨረሻ መፅናኛው ቢሆንም፤ ከሀይማኖቱ ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎች ተደቅኖበታል። « ብዙ ጊዜ ስለ ወጣቶች እናወራለን፤ ከእነሱ ጋር የምንነጋገርበት ጊዜ ግን ውስን ነው»

ሲሉ አቡ ዳቢ ውስጥ የሚገኘው የታባህ ተቋም ኃላፊ አባስ ዩናስ ይወቅሳሉ። እንደ ዩናስ በርካታ ሙስሊም ወጣቶች በእምነት ላይ መልስ ያላገኙላቸው ወይም ግልፅ ያልሆኑላቸው እና ከሌሎች መልስ የሚያፈላልጉበት ጥያቄዎች አሏቸው። ስለሆነው ወጣት አረቦች ሐይማኖታቸውን በሚመለከት ምን እንደሚሰማቸው ለማወቅ ተቋሙ መጠይቅ አዘጋጅቶ ነበር። በዚህ መጠይቅ እድሜያቸው ከ 15 እስከ 34 የሆኑ የስምንት የአረብ ሀገራት ዜጎች ተካፍለዋል። ከሀገራቱ መካከል ሞሮኮ፣ ግብፅ እና ሳውዲ አረቢያ ይገኛሉ። ከሞላ ጎደል ሁሉም በመጠይቁ የተሳተፉት ወጣቶች ሀይማኖታቸውን የሚያጠብቁ እንደሆነ ገልጸዋል። ይሁንና አሁን አሁን ከእስልምና ጋር ተያይዞ ያለው እውነታ ብዙም አያስደስታቸውም። ተሳታፊዎቹ ከቀረበላቸው አንዱ ጥያቄ ፤ አሁን ያለው ዘመናዊ አኗኗር እንደ አንድ ሙስሊም በእምነታቸው ላይ ግራ መጋባት ፈጥሮ እንደሆነ ነበር።
« በአራት ሀገራት አብዛኞቹ ይህንን ጥያቄ አዎ! ሲሉ መልሰዋል። እንደዚህ አይነት ግራ መጋባት ይሰማቸዋል። ሶስት ሀገራት ግን አይ! ሲሉ ነው የመለሱት እንደዚህ አይነት ግራ መጋባት አይሰማቸውም።»
Tunesien Salafistische Jugendliche (Symbolbild)
የቱኒዚያ ወጣት ሳላፊስቶችምስል picture-alliance/ZUMA Press
ራሷን ከውጪው አለም ገለል አድርጋ በምትገኘው ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ከተጠየቁት ወጣት ሙስሊሞች ከአስሩ ስምንቱ ሐይማኖታቸውን በተመለከተ ብዙም የውጭ ጫና አይሰማቸውም።« ይህ የአዕምሮ ግጭት አብዛኛውን ጊዜ በማህበረሰቡ ዘንድ ታዋቂ እየሆነ ከመጣው የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዘ ነው።»
ሲሉ አባስ ዩናስ ያብራራሉ። ዘመናዊው የአኗኗር ዘቤው እና የምዕራቡ ባህል ተፅዕኖ በተወሰነም ደረጃ ቢሆን አንዳንዶች እስልምናን ከሚረዱት ተቃርኖባቸዋል ይላሉ። አብዛኞቹ ተጠያቂዎች ስለ እምነቱ ያላቸውን አስተሳሰብ ወይም ግንዛቤ ዝም ብለው ማለፍ አይፈልጉም። እምነቱ ከዘመናዊው አኗኗnር ጋር አብሮ የሚሄድ እና የተጣጣመ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል። እንደውም በሶስት ሀገራት በተደረገው መጠይቅ በእስልምና ላይ ለውጥ ቢደረግ ይመርጣሉ። በሁሉም ሀገር ማለት ይቻላል አብዛኞቹ በእስልምና ህግ ወይም ይዘት ላይ ብቻ ሳይሆን የእምነት ሰበካው ላይም ለውጥ እንዲደረግ ፈልገዋል። እስካሁን ወንድ የሀይማኖት ሰባኪዎች በሚያመዝኑበት ሐይማኖት ፤ ወደፊት የበለጠ ሴት ኢማሞች እና ሰባኪዎች ይሹ እንደሁ ለወጣቶቹ ሌላው የቀረበላቸው ጥያቄ ነበር።« በሁሉም ሀገሮች ይህን ጥያቄ አዎ ሲል የመለሰው አብላጫው ህዝብ የበለጠ ሴት ኢማሞች እና ሰባኪዎችን ይሻል። ወንድና ሴቱን በእኩል ነው የሚያዩት። ይህ የሚያመላክተው በአረቡ ማህበረሰብ ዘንድ የሴቶችን ሚና መልሶ ማስተማር እንደሚያስፈልግ ነው። ይህ ደግሞ ቀደም ሲልም በአካባቢው የሚታወቅ ነገር ነው።
ይህ ደግሞ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ሲል የሚጠራው አክራሪ ቡድንም ይሁን የአል ቃይዳ አቋምን ይንፃረራል። አባስ ዩናስ እንደሚሉት የሴቶች ሚና ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የቡድኖቹ አመለካከት በተጠያቂዎቹ ዘንድ ተቀባይነት የለውም።« ከተጠያቂዎቹ 90 በመቶ በላይ እስላማዊ መንግሥትም ሆነ አል ቃይዳ የሚያራምዱትን ሐይማኖታዊ አስተሳሰብ በአጠቃላይ ወይም በይበልጥ ከእስልምና ጋር የማይገናኝ እንደሆነ ነው የተናገሩት፤ እና ማንኛውንም አክራሪ ቡድን ያወግዛሉ።።»
Youtube Webseite Videoportal
ምስል picture-alliance/dpa
ሰባት ከመቶ የሚሆኑት ተጠያቂዎች በአንጻሩ በአክራሪዎቹ ቡድን አቋም ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ። ለአክራሪው ቡድን አሸባሪዎች ለመመልመል አሁንም እድሉ ሰፊ ነው። እንደተጠያቂዎቹ ከሆነ ወጣቶች አሸባሪ ቡድኖችን የሚቀላቀሉበት ሶስት ምክንያቶች አሉ። እነሱም ጠንካራ የአክራሪዎች ሰበካ፣ የግንዛቤ ማነስ እና በሀገራቸው ያለው የፖለቲካ ጫና እና ሙስና ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ አብዛኞቹ ተጠያቂዎች ለአክራሪዎች መስፋፋት የምዕራቡ ፖለቲካም ይሁን ራሱ እስልምና ምክንያት አይደሉም ባይ ናቸው። ለእነሱ በዋነኛነት ተጠያቂዎቹ የሀገራቸው ፖለቲካ እና የሐይማኖት ሰባኪዎች ናቸው።
ወደ ጀርመን ስንመለስ ከታዋቂ የ You Tube አዘጋጆች ጋር በመተባበር የጀርመን የፖለቲካ ትምህርት ማዕከል አክራሪነትን ለመታገል ቪዲዮ አዘጋጅቷል። ጂሀድ ምንድን ነው? ካሊፋትስ? ቁራን ሰውን ለሽብር ይጠራል ወይ? እና ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት ማዕከሉ በኢንተርኔት የሚሰራጭ የማብራሪያ ቪዲዮ ነው የተዘጋጀው። የጀርመን የሀገር አስተዳድር ሚኒስትር ቶማስ ዴ ሚዚዬር « የኢንተርኔት መረቡን ለአሸባሪዎች ብቻ ልንተውላቸው አይገባም » ሲሉ ተናግረዋል። 16 በ ታዋቂ የYou Tube አዘጋጆች የተቀናበሩት ቪዲዮዎች ኢላማ ያደረጉት ነበሮቹን የመገናኛ ብዙኋን ለማይጠቀሙ ወጣቶች ነው። ለፕሮጀክቱ ደግሞ ድጋፍ የሚያደርገው የጀርመን መንግሥት ነው። ቪዲዮው ባለፉት ሳምንታት ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ጊዜ ተጎብኝቷል።
USA Baltimore Besuch Obama bei Islamic Society Moschee
ምስል Reuters/J. Ernst
በተለይ በምዕራቡ ዓለም ሙስሊሞች ላይ ያለው ጥርጣሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ጎልቶ የሚታየው ወደ አውሮፓ በተሰደዱ ሙስሊም ተገን ጠያቂቆች ላይ ነው። በፌስ ቡክ የተቋቋመ አንድ ጸረ እስልምና ቡድን ቼክ ሪፖብሊክ ውስጥ የቀኝ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች አግኝቷል። በዚህ ሳምንት መጨረሻም ቡድኑና ቡድኑን የሚደግፉ ከትምህርት ቤት በኋላ ከጎረቤት ሀገራት ጭምር አደባባይ እንዲወጡ ሰልፍ ጠርቷል።«በርካታ ተመሳሳይ ነገር አለን። በአውሮፓ የእስልምና መስፋፋትን ስለምንቃወም ይህንን ማስቆም እንፈልጋለን። የህዝቡ ነፃነት እና መብት እንዲከበር የፔጊዳን አላማ እንጋራለን።»
ባለፈው ወር ብቻ ጀርመን ውስጥ በሚንቀሳቀሰው የጸረ እስልምና ቡድን ፔጊዳ አነሳሽነት ከ 14 ሀገራት የተውጣጡ የጸረ እስልምና ተወካዮች ፕራግ ላይ ተነናኝተዋል። እዛም ቀኝ ፅንፈኞቹ በአውሮፓ ደረጃ ተጣምረው የሚሰሩበትን ስምምነት ፈፅመዋል።
ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ያመራን እንደሆን የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፕሬዚዳንት ከሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ዕሮብ ዕለት ቧልቲማር ውስጥ የሚገኝ አንድ መስጊድ ጎብኝተዋል። ኦባማ በሀገራቸው ሙስሊሞች ላይ ያለውን ጥላቻ እና ስጋት ክፉኛ በማውገዝ፤ አንዳንድ ሙስሊሞች እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ እንደሚሰማቸው የጻፉት ደብዳቤዎች ይጠቁማሉ ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። በተመሳሳይ ጊዜ ኦባማ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚፈጠረው መጥፎ ነገር ሁሉ ተጠያቂዋ ዩናይትድ ስቴትስ ናት የሚለውን አስተሳሰብ የሙስሊም መሪዎች መቃወም አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሀገሪቱ አንድ ከመቶ ህዝብ ማለትም ሶስት ሚሊዮን ገደማ ሙስሊሞች እንደሆኑ ይታመናል።
ሙሉውን ዝግጅት በድምፅ ያገኙታል።
ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ