1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣቶቹ እና አደገኛው የጭነት መኪና

ዓርብ፣ ሚያዝያ 14 2008

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የግንባታ ኢንዱስትሪ ተመራጭ የሆኑት የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች በሚያደርሱት አደጋ 'ቀይ ሽብር' እስከመባል ደርሰዋል። በጎርጎሮሳዊው 2014 የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ ባደረገው ዘገባ ኢትዮጵያ ዉስጥ በትራፊክ አደጋ 15,015 ሰዎች በየዓመቱ ለሞት እንደሚዳረጉ አስታውቆ ነበር።

https://p.dw.com/p/1Ib1f
Äthiopien Addis Ababa LKW
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ወጣቶቹ እና አደገኛው የጭነት መኪና

ጥር 9/2008 ዓ.ም. ማለዳ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ አዲስ በተገነባው የፍጥነት መንገድ ላይ ይጓዝ የነበረ አሽከርካሪ መኪናውን መቆጣጠር ተስኖታል። የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪው በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዘ ነው። ከተቃራኒ አቅጣጫ አንድ መለስተኛ አዉቶቡስ አስራ ስድስት ሰዎች ጭኖ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ ነው። የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪው የሚጓዝበትን መንገድ ስቶ የመንገድ አካፋይ በመጣስ የመንገደኞች ማመላሻው ላይ ወጣበት። በአደጋው አስራ አንድ ሰዎች ወዲያውኑ ሲሞቱ ዘጠኙ ቆሰሉ። በህይወት ከተረፉት መካከል አምስቱ ህይወታቸውን የሚያሰጋ ጉዳት ነበር የደረሰባቸው። ከአደጋው በኋላ መካከለኛው የመንገደኞች ማመላለሻ በቀድሞ ቅርጹም ይሁን መጠኑ አልነበረም። ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ በመጓዝ ላይ የነበረው ሲኖ ትራክ የተሰኘ ቻይና ሰራሽ መኪና ነበር።

ይህ በቅርብ ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰቱ አሰቃቂ አደጋዎች መካከል አንዱ ነው። አሽከርካሪዎቹ ወጣቶች፤ ተሽከርካሪዎቹ ደግሞ በአገሪቱ በተስፋፋው ግንባታ ተመራጭ የሆኑት ሲኖ ትራኮች ናቸው። የደረቅ ማመላለሻዎቹ ተሽከርካሪዎች ባደረሷቸው አሰቃቂ አደጋዎች ቅጽል ስም ሁሉ ወጥቶላቸዋል። አንዳንዶች 'ቀይ ሽብር' ሌሎች ደግሞ ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን የእንግሊዘኛ የአፅህሮት ስያሜን በመዋስ 'አይሲስ' ብለው ይጠሯቸዋል።

Äthiopien Addis Ababa Bushaltestelle
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ኢሳያስ ጎሳዬ ሲኖትራክ የደረቅ ጭነት መኪና ማሽከርከር ከጀመረ ጥቂት ወራት ብቻ አስቆጥሯል። እንደ ኢሳያስ በተመሳሳይ የግድብ ግንባታ ስራ ውስጥ ሲኖ ትራክ ከሚያሽከረክሩ አስራ አራት የስራ ባልደረቦቹ መካከል አስራ ሶስቱ ወጣቶች ናቸው።

ከአራት አመታት በላይ ሲኖትራክ ያሽከረከረው ዮናስ አስናቀ ከዚህ ቀደም የጣልያን መኪና ይሾፍር ነበር። ዮናስም እንደ ኢሳያስ ሁሉ በኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ የሲኖትራክ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች መብዛታቸውን ይስማማል። እንደ ዮናስ ከሆነ በአሽከርካሪነት ስራ ለመሰማራት ወጣቶች ያላቸው አማራጭም ይህው መኪና ነው።

ድንገቴው የግንባታ መስፋፋት ለኢትዮጵያ ካስተዋወቃቸው አዳዲስ ነገሮች መካከል ሲኖትራክ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ይጠቀሳሉ። ተሽከርካሪዎቹ በቀጥታ ከቻይና ለኢትዮጵያ ገበያ የሚቀርቡ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲሕ በከፊል በአገር ውስጥ መገጣጠም ተጀምሯል።

ኢሳያስ እና ዮናስን መሰል ወጣቶች በስራቸው የሚያገኙት ገቢ አከፋፈል በሰሩበት ሰዓት ልክ አልያም በወር አይደለም አይደለም። ገቢያቸው የሚወሰነው በቀን በየዕለቱ በጫኑት ልክ የሚወሰን በመሆኑ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ቶሎ ቶሎ መመላለስ እንደሚኖርባቸው ዮናስ ይናገራል።

ኢሳያስ አሁን የሚያስሸከረክረውን ሲኖትራክ ከፍተኛ ፍጥነት እንዳለው ይናገራል። ከፍተኛ ጉልበት ያለው ይህ ተሽከርካሪ የፍጥነት መቀነሻ አሊያም መቆሚያ ፍሬን ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል።

ዮናስ ወጣት አሽከርካሪዎች የመኪናውን ባህሪ ጠንቅቀው ማወቅ እንዳለባቸው ይናገራል። በተደጋጋሚ ለሚከሰቱት አሰቃቂ አደጋዎች የተሽከርካሪዎቹ ባለቤቶች ግፊትም አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ያምናል።

እንደ ሲኖትራክ ሁሉ የጃፓኑ ቶዮታ ምርት የሆነው መካከለኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በወጣቶች ተመራጭ ከሆኑት እና ተደጋጋሚ አደጋ ከሚገጥማቸው መካከል ይጠቀሳል። በኢትዮጵያ ከሚከሰቱት ተደደጋሚ አደጋዎች መካከል የወጣት አሽከርካሪዎች ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑን የሚናገረው ኢሳያስ የአደጋዎቹ መንስዔ የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑን ይተቻል።

በተሻሻለው የኢትዮጵያ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ መሰረት እድሜያቸው 24 አመት የሞላ ወጣቶች ሲኖትራክን ጨምሮ የከባድ ጭነት መኪኖች የማሽከርከር ፈቃድ ያገኛሉ። ዮናስ ወጣቶች ያለበቂ ልምድ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ጭነት መሸከም የሚችሉ እና ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸው መኪኖች የማሽከርከር ፈቃድ ማግኘታቸው ለአደጋ መባባስ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይናገራል።

Äthiopien Addis Ababa Bushaltestelle
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥን ለመከለስ አዲስ አበባ ላይ ባለሙያዎቹን ሰብስቧል። በጉባዔው መካከል ያነጋገ,ርናቸው የኢትዮጵያ ተሽከርካሪ ፈቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማሉ ጀንበር መስሪያ ቤታቸው የሚያስፈጽመው የፌዴራል መንግስት ያወጣውን መመሪያ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኃላፊው እድሜው 24 ዓመት የደረሰ ወጣት ለድርጊቶቹ ኃላፊነት መውሰድ ከሚችልበት የእድሜ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የከባድ ደረቅ ጭነት መኪና ለማሽከርከር ብቁ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

የቻይናዎቹ መኪኖች ባደረሷቸው ዘግናኝ አደጋዎች አይሲስም ይሁን ቀይሽብር ተብለው ይጠሩ እንጂ ገበያው ላይ ተፈላጊነታቸው አልቀነሰም። ኢሳያስ ርቀት ጠብቆ ማሽከርከር እና የፍሬንን ነገር በአግባቡ መቆጣጠር አስፈላጊ ነው ብሏል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ