1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣቶች እና የመረጃ ምንጫቸው

ዓርብ፣ ጥቅምት 21 2012

እንደ ባለፈው ሳምንት አይነት ግጭቶች እና ጥቃቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቀሰቀሱ የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታን ያንፀባርቃሉ የተባሉ ቪዲዮዎች ፣ ፎቶግራፎች፣ ፁሁፎች  በፍጥነት እንደ ፌስቡክ ያሉ የመገናኛ ብዙኃንን ያጨናነቃሉ። የመረጃውን ትክክለኛነት የማጣራቱ ድርሻ ደግሞ ለተጠቃሚው የተተወ ነው።

https://p.dw.com/p/3SCTc
Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ከተካሄዱ ግጭቶች እና ጥቃቶች ጋር በተያያዘ እንደ ፌስ ቡክ እና ዩቱይብ በመሳሰሉት የማህበራው የመገናኛ ዘዴዎች በርካታ መረጃዎች ተሰራጭተዋል። ከነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ የአንድ እውነት ጫፍ ላይ ተሞርክዘው ብቻ ወይም ጨርሶ የተሳሳተ መረጃ የሚያስተጋቡ እንደነበሩ ብዙዎች ትዝብታቸውን አካፍለውናል። ወሎ የሚኖረው ጀማል በፌስኩክ ላይ አመኔታ ስላጣሁ ሰሞኑን የሆነውን የተከታተልኩት ከመደበኛ የመገናኛ ብዙኃን ነው ይላል።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ፣ ፌስቡክ ላይ የማያቸው ያልተጣሩ ወሬዎች ያሳስቡኛል የሚለው ሌላው ወጣት ደግሞ ሀለላ ነው። የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆን ዕውነታዎችን የሚያጣራው በራሱ መንገድ ነው።  « በአካባቢዬ ያለውን ነገር ራሴ ሄጄ ለማጣራት እሞክራለሁ። ክፍለ ሀገር የሚሆነውን ደግሞ ስልክ ደውዬ አጣራለሁ። ሌላውን በጥርጣሬ ነው የማየው። »ይላል።

Äthiopien Notstände in Amhara
ምስል DW/J. Jeffrey

በኦሮሚያ ክልል የሚኖረው ጀማል ሰዎችን በአሁን ሰዓት ስሜታዊ እያደረገ ያለው ከፌስቡክ የሚያገኙት መረጃ ነው ይላል። እሱ እንደሚለው ወጣቶች ከእውነተኛ መረጃ አሁንም ርቀዋል። «  ከኛ የበለጠ ወሬ ያለው እና ፖስት እያደረገ ያለው ሀገር ውስጥ ያለው ሳይሆን ውጭ ሀገር የሚኖረው ነው።»ጀማል በተለይ በሐይማኖት እና በብሔር ላይ ያተኮረ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰት ወሬ እንዲቆም ለተጠቃሚዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ መፍትሄ ነው ብሎ ያምናል። የህግ ባለሙያው አቶ ሳሙኤል ጌታነህ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ናቸው።ተጠቃሚው በትክክለኛ ስም እና ምስሉ ተመዝግቦ ቢገለገል ኖሮ የተጠያቂነት ስሜት በተፈጠረ ነበር ይላሉ። ከህግ አንፃርም ህጉ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና እየፀደቀ ስለሆነ ክትትሉን ከባድ ያደርገዋል ይላሉ የህግ ባለሙያው። ይህ የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የተረቀቀው ሕግ ቢፀድቅም እንኳን ስለ ተግባራዊነቱ  ስጋት አላቸው። « ያወጣው አካልም መልሶ ሲያፈርሳቸው ወይም ተግባራዊ ሳይሆኑ ነው የሚቀሩት»  አሁን ባለው ሁኔታም መንግሥት አቅም ኖሮት ከሀገር ውጪ ያሉትን እንዴት ተጠያቂ እንደሚያደርግ ግልፅ እንዳልሆነላቸው ያስረዳሉ።   

Äthiopien Jungen unter Satellitenschüssel
ምስል picture-alliance/dpa/T. Schulze

በርካታ ወጣቶች ፌስቡክ ውስጥ መረጃ የሚያፈላልጉት ሀገር ውስጥ በቂ መረጃ ስለማያገኙ እንደሆነ በመግለፅ መደበኛ የመገናኛ ብዙኃንን ይወቅሳሉ። በጅማ ዩንቨርስቲ የሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ዶክተር ጌታቸው ጥላሁን « ከአዲሱ ለውጥ ጋር በተያያዘ ለዘመናት ይዞት የነበረው አፈና ተነስቷል። በመጀመሪያዎቹ የለውጡ መራት አካባቢም ሚዲያው በጥሩ መልኩ ይሄድ ነበር። » በማለት አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ በመገናኛ ብዙኃን ዘንድ ውስንነት እና ሚዛናዊ አለመሆን እንዳለ ያስረዳሉ። ለዚህም ሰሞኖን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ። « ጉዳዩን ፈልፍሎ እውነቱ የቱ ጋር ነው የሚለውም ከማጠያየቅ አንፃር መልስ የለም።» ይላሉ።

በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት የእውነትም ይሁኑ የሀሰት መረጃዎች በቀላሉ ከመገናኛ ብዙኃን ቀድመው ይደርሳሉ። ስለሆነም የተከማቸውን ያልተረጋገጠ ጥሬ መረጃ የሚያጣራው ወይም የሚያመዛዝነው ራሱ ተጠቃሚው ይሆናል። ስለሆነም  ተጠቃሚው አብዛኛው ወጣት፣በራሱ መንገድ መረጃን እንዴት  ማጣራት ይኖርበታል ? ዶክተር ጌታቸው ጥላሁን። »ወጣቱ ሰከን ማለት ይገባዋል» ይላሉ። « የግራውንም የቀኝኑም ቆም ብሎ የመመርመር ልምምድ ቢያደርጉ ይጠቅማል።»

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ